የኢትዮጵያ ተቃርኖ፤ ከሃይማኖት ወደ ብሔር፣ ከብሔር መልሶ ወደ ሃይማኖት? | በፍቃዱ ዘ....

የኢትዮጵያ ተቃርኖ፤ ከሃይማኖት ወደ ብሔር፣ ከብሔር መልሶ ወደ ሃይማኖት? | በፍቃዱ ዘ. ኃይሉ

(ክብ ልፋት)

አንዳንዴ እውነቱ መራር ስለሆነ መጎንጨት ይኮመጥጠናል። ስለሆነም በምቾት ክበባችን ውስጥ እርስ በርስ እየተወዳደስን ከክበባችን ውጪ ያሉትን በጋራ እየረገምን የይስሙላ መደላደል እንፈጥራለን። አንዳንዴ ግን ቆራጥ ሆነን እውነቱን አጮልቀንም ቢሆን ለማየት መሞከር ይኖርብናል። ይህንን የምናደርግበት አንዱ መንገድ ከማይመሥሉን ሰዎች ጋር ሳይቀር መነጋገር ነው። ምክንያቱም ዕጣ ፈንታችን የጋራ ነው፤ we are condemned to live/perish together.

ማውራት ከሚገቡን ጉዳዮች አንዱ የሃይማኖት ቅራኔ ነው። ብሔር የሥልጣን እና የአገር ሀብት መቆጣጠሪያ መሰላል ከመሆኑ በፊት ሃይማኖት ነበር መሰላሉ። በኢትዮጵያ ረዥም ዕድሜ የገዛው ክርስቲያናዊው መንግሥትም ይሁን፣ የክርስቲያኑን መንግሥት ለአጫጭር ጊዜ የነቀነቁት በክርስትናው መንግሥት አጠራር ይሁዲት ጉዲትም፣ ግራኝ መሐመድም ሃይማኖትን ነው መወጣጫ እና ቅቡልነት ማግኛ አድርገው የተጠቀሙበት።

አማራነት ብሔር ከመሆኑ በፊት የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታይነት ማረጋገጫ እንደነበር ብዙ ጊዜ የተጨቃጨቅንበት ነው። በዚያን ጊዜ አሁን አስነዋሪ የሆነው “ጋላ” የሚለው አጠራር በተለይ የዋቄፈና እምነት ተከታዮችን የለየ አጠራር እንደነበር በታሪክ ሰነድ መሥመሮች መሐል ማንበብ ይበቃል። የእስልምና እምነት ተከታይ የነበሩ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ከአካባቢ መጠሪያቸው ውጪ “እስላም” ነበር የሚባሉት።

ተቃርኖው የሃይማኖት እንደነበር ለማሣየት እንደ አብነት የዳግማዊ ምኒልክ የአድዋ ጦርነት አዋጅን መጥቀስ ይቻላል፦ “ሃይማኖት የሚለውጥና አገር የሚያጠፋ ጠላት መጥቷል” ነበር ያሉት፤ ብሔርህን የሚያጠፋ ብለው የሚያስቡበት ጊዜ አልነበረም። የቋራውን መይሳው ካሣ እና የትግሬውን ወሬሳው ካሣ የሚያመሳስላቸው ኹለቱም ለክርስትና ያላቸው “ታማኝነት” እና ለእስልምና የነበራቸው ጥዩፍነት ነበር።

ይህ የሃይማኖት ተቃርኖ በ20ኛው ክፍለ ዘመን በሆነ መንገድ ወደ ብሔር ተቃርኖ ተቀነበበ። ፖለቲከኞች የሃይማኖት ግንቦችን እየሰበሩ በቋንቋ ጥላ ሥር ብሔርተኝነት እየፈጠሩ ገሰገሱ። ተሳክቶላቸው መንግሥታዊ አስተሳሰብ ሆነ። ይሁን እንጂ ይህ የቋንቋ ብሔርተኝነት በውስጠ ታዋቂነት ሃይማኖታዊ ንዑስ ቅንጣት የታጀበ ነበር። ይህ ዓለም ዐቀፍ እውነታ ነው። የእሥራኤሎች ብሔርተኝነት (ፅዮናዊነት) ለምሳሌ የአይሁድ እምነትን በውስጠ ታዋቂነት ያነገበ ንቅናቄ ነበር። ወደ አገራችን ስንመጣም ይኽንኑ ይመሥላል።

የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ሲመሠረት በክርስቲያኑ መንግሥት እንደመሆኑ የሳባ ትርክት ላይ መንጠልጠሉ አይገርምም። የኦሮሞ ብሔርተኝነት ዋቄፈና እምነትን እንደ አንድ የኦሮሙማ መሠረት አድርጎ ጥሎታል፤ ለዚህ ነው በመሠረቱ ሃይማኖታዊ የሆነውን የኢሬቻ በዓልን ለማክበር የክርስትናም የእስልምናም እምነት ተከታዮች ወደ ቢሾፍቱ በየዓመቱ ሲጎርፉ የምናየው። በሌላ በኩል የኦሮሞ ፖለቲከኞች (ኦነግን ጨምሮ) ከሚከፋፈሉባቸው ምክንያቶች አንዱ እና ዋነኛው ሃይማኖት የኾነው በዚህ ምክንያት ነው። የአማራ ብሔርተኝነት ንቅናቄ ‘ግዮናዊነት’ የሚል ሥያሜ ሲይዝ በውስጠ ታዋቂነት ሃይማኖት አለኝ እያለ መሆኑ ነው።

ይህንን ለመጻፍ ያነሳሳኝ ሰሞኑን ያየኋቸው ሃላፊነት የጎደላቸው የፌስቡክ እና የመጽሔት ትንታኔዎች ናቸው። ሐበሻዊ ወግ የተባለው መጽሔት ጃዋር መሐመድን የጅሀድ መሪ አድርጎ አቅርቦታል። ጃዋር በስርዓቱ እስልምናውን የማያጠብቅ፣ ለብሔርተኝነት ፖለቲካው ግብ ብቻ ጠቃሚ መሥሎ ሲታየው የሚያነሳሳው መሆኑ ይፋዊ ምስጢር ነው። በብሔርተኝነቱ መውቀስ ሌላ ነገር ነው፤ ኀላፊነት በሚጎድለው የተቃውሞ ቅስቀሳውን መውቀስም እንዲሁ ሌላ ነገር ነው። ነገር ግን የጅሐድ መሪ አድርጎ መሣል የተኛውን የሃይማኖት ተቃርኖ መቀስቀስ ነው። የመልዕክቱ ይዘትም “ክርስቲያን ሆይ ሙስሊም መጣብህ” የሚመሥል ነገር አለው። በፌስቡክ ላይም ያሬድ ጥበቡ የሱሉልታዋ ከንቲባ “ታደርገዋለች” ተብሎ የተወራውን ወሬ አላግባብነት ለመጥቀስ የተጠቀመበት መሣሪያ ሃይማኖቷን መጥቀስ ነበር፤ ሱሉልታ እስልምና ተከታይ የማይኖራት ይመስል።

ብዙ ሃይማኖት ተኮር ነን የሚሉ የፌስቡክ ገጾች አሉ፤ አልከታተላቸውም። ነገር ግን ተፅዕኗቸው በጣም ከፍተኛ እና ብዙ ተከታይ ለማፍራት ስለራሳቸው እምነት ከሚያወሩት ይልቅ ሌሎቹን የሚወቅሱበት እንደሚበዛ በተለያዩ አጋጣሚዎች ስረዳ ግን አስደንግጦኛል፤ እኔም ከምቾት ክበቤ መውጣት እንዳለብኝ አስታውሶኛል። የሐበሻ ወግ ስለ “ጃዋር የጅሃድ ጦርነት…” ከመጻፉ በፊት 300 ሺሕ ተከታዮች ያሉት ዘመድኩን በቀለ የሚባል “የክርስቲያን ሰባኪ ነኝ” ባይ ተመሣሣይ ይዘት ያለው ጽሑፍ ጽፎ ነበር (ይህንን ጽሑፍ ከአንድ ሺሕ በላይ ሰዎች [ተስማምተውበት ይመሥለኛል] አጋርተውታል)። መጽሔቱ እና ይህ የፌስቡክ ገጽ ትርክት አልተመጋገቡም ብሎ ማሰብ ይቸግራል።

በዚህ ከቀጠልን ምናልባት ወደ ፊት ደግሞ በሃይማኖት ተቧድነን የምንቧቀስበትን ክፍፍል አሁን መጋገር ጀምረናል ማለት ነው። ከብሔር ክፍፍል የሃይማኖት ክፍፍል ይሻላል ወደሚል ቅጣንባሩ የገባ ክርክር መግባት አልፈልግም። ነገር ግን ኀላፊነት የጎደለው ነገር በጻፍን ቁጥር የምንቆሰቁሰው ያልሻረ ቁስል እዚህም እዚያም ስላለ፣ እየተስተዋለ!

LEAVE A REPLY