“ተፎካካሪ ፓርቲዎች” ለውጡን ከመደገፍ ባሻገር ማየት አለባቸው || ዶ/ር አክሎግ ቢራራ

“ተፎካካሪ ፓርቲዎች” ለውጡን ከመደገፍ ባሻገር ማየት አለባቸው || ዶ/ር አክሎግ ቢራራ

      በኢትዮጲስ ታትሞ ከቀረበ በኋላ ተሻሽሎ የቀረበ

የለውጡ ተግዳሮቶችና ፈተናዎች

ጠ/ሚ/ር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ሥልጣን ከያዙ አንድ ዓመት ተቆጥሯል። የእሳቸው የፖለቲካ ሥልጣን መያዝ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ በተለይ ወጣቱ ትውልድ፣ ጸረ-ህወሓት፤ ጸረ-አምባገነን አገዛዝ፤ ጸረ-ሌብነትና ሙስኛነት፤ ጸረ-ዘረኝነትና ጠባብ ብሄርተኝነት፤ ጸረ- አግላይነትና ጸረ-ኢሰብአዊነት ትግልና መስዋእት ውጤት ነው። ለግፉና በደሉ የአንበሳውን ድርሻ ይዞ የነበረው ህወኃት የነበረ ቢሆንም፣ ብቻውን ግን አልነበረም፤ ከዚህ ጋር የተያያዙ ጉዳዮቾ ገና አልጠሩም።  ለውጡ  ገና ብዙ ፈተናዎች ተደቅነውበታል።

እጅግ አስደናቂ እድገት አሳይታለች ተብላ በተጠራችው አገራችን፤ ዛሬ በጠቅላላ ሶስት ሚሊየን ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው “ስደተኞችና ለማኞች” እንዲሆኑ ተገደዋል። ይህ ግፍና በደል ከተፈጥሮ ሁኔታ የመጣ አይደለም። ከተመክሮ ጉድለትና ከአመራር ድክመት የመጣ ነው። እኛ ኢትዮጵያዊያን መቸ ነው ከልመናና ከአሳፋሪ ጥገኝነት ነጻ የምንወጣው? ብለን መጠየቅ አለብን። በኔ እምነት፤ በሕዝቡ ላይ በተደጋጋሚ የተከሰተውን ብሄር ተኮር ግፍና በደል ልንወጣው የምንችለው የችግሩን ስርዓት ወለድ መንስኤ በሃቅ ልናስቀምጠው ስንደፍር፤ ስንችልና የወደፊቱን ዲሞክራሳዊ ፍኖተ ካርታ ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ መብት በሚያስከብር ሁኔታ በተሻሻለ ሕገ መንግሥትና በዘውግና በቋንቋ ሳይሆን፤ በኢትዮጵያዊያን የትም ቦታ የመኖር፤ የመስራት፤ ኃብት የመያዝ፤ የመምረጥና የመመረጥ መብት ስኬታማ በሚያደርግ የፌደራል ስርዓት በመተካት ነው።

ኢትዮጵያ ዘመናዊና ዲሞክራሳዊ ለመሆን የምትችለው የአሁኑን ስርዓት ተሸክማና ንመሰረት አድርጋ ሊሆን አይችልም። ትንሽ ዞር ብለን እንመልከት!!

ትላንት የዐማራው ሕዝብ ከጉራ ፈርዳ፤ ከጋምቤላ፤ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ፤ ከልዩ ልዩ የኦሮሞ ክልል አካባቢዎች በገፍ ቀዩን እንዲለቅ ሲደረግ ዝም ብለን አየን። ትላንት ደፍረንና ተባብረን ለመነሳት ስላልቻልን ችግሩ ተለመደ። አዲስ አበባ ደረሰ። ዛሬ ችግሩ በየአካባቢው ተዛምቷል። በደቡብ ክልል፤ በጎንደር፤ በአዲስ አበባ (ለገጣፎ፤ ሱሉልታ) የሚታየው ጭካኔ ለእያንዳችን ውርደት እየሆነ ነው። የፈለገው ኑዛዜ ቢደረግ፤ ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ችግሩን ፈጥሮ መፍትሄ ሊያመጣልን አይችልም። የትም አገር ቢሆን ችግሩን የፈጠረ ቡድን ችግሩን ሊፈታው አይችልም። የተሻለ  አማራጭ ያስፈልጋል ማለት ነው።

የፖሊሲ፤ የመዋቅር፤ የተቋማት፤ የአገዛዝና ተመሳሳይ ተግዳሮቶች ብሄራዊ የሆነ የድርጅትና የአመራር አንቅስቃሴ የስፈልጋቸዋል። ወቅቱ ግን ጠንካራ የፖለቲካ ድርጅቶቾ የሚፈልግበት ግዜ ነው። በዚህ ክፍት ሳቢያ፣ በአጭሩ፣ ኢትዮጵያ የብዙ ችግሮች አገር መሆኗ ቀጥሏል።

ከእነዚህ ፈተናዎችና ተግዳሮቶች መካከል ከፍተኛ ቦታ ያለው፤ በየዘውጎቹ ልሂቃን መካከል ያለው የማያኮራ ፍክክር ነው። የዚህ ችግር ምንጭና ሁኔታውን እያባበባሰ ወደማይመለስበት ደረጃ እየገፋው የሚገኘው፣ በቋንቋና በዘውግ ላይ የተመሰረተው ሕገ መንግሥትና የክልል አስተዳደር ነው፡፡

የኢኮኖሚውንና የፖለቲካውን ተግዳሮቶች ዘላቂነት ባለው ደረጃ ለመፍታት ከተፈለገ፣ ቋንቋንና ዘውግን መሰረት ያደረገው ሕገ-መንግሥትና “የክልል” አገዛዝ ለሰከነ ውይይትና ድርድር መቅረብ አለበት። የዚህ ውይይትና ድርድር ውጤት፣ ከምንም በላይ፣ ኢትዮጵያዊያን፣  በየተኛውም የሀገሪቱ ክልል ያለ ምንም ፍርሃትና መሸማቀቅ የመኖር፤  ንብረትና ሀብት የማፍራት፤ ማንኛውንም የሲቪክ፤ የሙያና የፖለቲካ ፓርቲ የመቀላቀል፤ የመመረጥና የመምረጥ  መብታቸውን የሚያጎላ ህገ-መንግሥት መሆን ይገባዋል።ይህን መሠረት በማያሻማ ሁኔታ ሳንጥል፣ሰለሀገር ማውራት አንችልም።

ጠ/ሚ/ር  ዐብይ አህመድ ሥልጣን ሲይዙ  በአስርት ሚሊየኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ተስፋ የሰነቁት፣ “ከዘውግ፤ ከግልና ከቡድን ጥቅም በላይ፣ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የሚያስቀድም መሪ አገኘን” በሚል እምነት ነበር። በንግግራቸው ላይ፤  “ኢትዮጵያ” የሚለውን ቃል 63 ጊዜ ጠቅሰው፤ “ብሄር፤ ብሄረሰብና ሕዝቦች” የሚለውን የህወሓት “የከፋፍለህ ግዛው” መርህ ግን ትኩረት መንፈጋቸውን ያ ሁሉ ህዝብ አስተውሏል።

ሌሎች የጥቁር አፍሪካ አገሮች (ቦትስዋና፤ ናምቢያ፤ ጋና፤ ሴኔጋል፤ ታንዛንያ፤ ሩዋንዳ ወዘተ፣)   የማንነት መለያቸውን ወደ አገራዊ ብሄርተኛነት ከለወጡት ዓመታት ሆኗቸዋል። የተገላቢጦሽ ሆኖ፣   እኛ አሁን ከነሱ መማር ሊኖርብን ነው።

እኛ ኢትዮጵያዊያን አሜሪካ፤ እንግሊዝ አገር፤ አውስትራልያ ወዘተ ተሰደን ከማናውቃቸው ጋር ተከባብረን ለመኖር ችለናል። ለማንም ሊገባው የማይችለው ክስተት ግን በራሳችን አገር ስንኖር እንዴት የሌላውን ወንድማችን፤ የሌላይቱን እህታችን መብት ለማክበርና ለማስከበር አንችልም?

ከለውጡ ቦኋላ፣ ኢትዮጵያ ብዙ ያልተጠበቁና ተከታታይ የሆኑ ተግዳሮቶች ተከስተውባታል። ከሶስት ሚሊየን በላይ የአገር ውስጥ ስደተኞች መኖራቸውን እንደ ምሳሌ ሊጠቀስ ይችላል። በጎንደር  90,000 ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፤ ብዙ ሽህ ሰዎች ወደ ሱዳን ተሰደዋል፤  በ አስር ሽህ የሚቆጠሩ ቤቶች ተቃጥለዋል።  ይህን ሁሉ በመጠለያ የሚኖር ሕዝብ መልሶ ለማቋቋም፣ ቢያንስ ቢያንስ ሁለት ቢሊየን ብር ኢንቨስትመንት ያስፈልጋል፤ የብሄር ፌደራሊዝሙ መዘዝ በደምም በገንዘብም እያስከፈለን ይገኛል፡፡

“የፌዴራል ሥርዓቱና የድርድር አስፈላጊነት

በቋንቋና በዘውግ ዙሪያ የተመሰረተው የፌደራል ስርዓት፤ ጠ/ሚ/ር  ዐብይ የመንግስታቸው ማውጠንጠኛ ይሆናል ካሉት ኢትዮጵያዊነትን ያማከለ እሴትና መርህ ጋር (Ethiopa and Ethiopian citizenship centered narrative) ፈፅሞ ሊሄድ አይችልም፤ ከሁለት አንዱን መምረጥ የግድ ይላል።

ይህ በሆነበት ሁኔታ፣ የኦዴፓ አመራር በቅርቡ “በፌደራል ስርዓቱ ላይ ከማንም ጋር ለድርድር እንደማይቀመጥ እናስታውቃለን፤ . . . የአዲስ አበባ እና የአፋን ኦሮሞ ጉዳይም እየተሰራበት ያለ ጉዳይ ነው” ያለው፤ ከጠ/ሚ/ሩ ራዕይ ጋር በቀጥታ የሚጣረስ ነው።   በመቀሌ የመሸገውና  “ለጦርነት” በመዘጋጀት ላይ ያለው ህወሓትም የሚለው፣ “የፌድራል ሥርዓቱና ህገ-መንግሥቱ ለድርድር አይቀርቡም” መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። ። ይባስ ብሎ፤ ሁለቱም ድርጅቶች፣“አብዮታዊ ዲሞክራሲ” የሚለውን የአንድ ፓርቲ የበላይነት መስመር እንከተላለን ስለሚሉ፣ ሁለቱ ድርጅቶቾ፤ ከስልጣን ሹኩቻ ባሻገር የሚለያዩበት መስመር ምን እንደሆነ  ለብዙ ሚሊየን ኢትዮጵያዊያን ግልጽ አይደለም።

“ስንኖር ኢትዮጵያዊ፤ ስንሞት ኢትዮጵያ እንሆናለን እና “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው”  የተባለውና፣  ኢትዮጵያን የነገዋ ዩጎስላቭያ ሊያደርግ የሚችለው የፌደራል ስርዓት “ለድርድር አይቀርብም” የተባለው እርስ በእርሳቸው ይጋጫሉ፤ አብረው መጓዝ አይችሉም።  ይህ ተቃርኖ አየፈጠረ በሚገኘው ክፍተት፣  ሀገር አደጋ ላይ እየወደቀች ነው።

በኔ እምነትና ጥናት፤ ህብረ ብሄራዊም ሆኑ ዘውጋዊ የፖለቲካ ልሂቃን፣ በአንድ ድምጽ ለታሪካዊቷ ሀገራችን ከቆሙ ኢትዮጵያ አትፈርስም። ዛሬ ቆርጠውና ደፍረው ካልተነሱ ግን፣ ሁኔታው ከማይመለስበት ደረጃ ይደርሳል፤ የዚች ሀገር አፍራሾችም አዳኞችም ራሳችን ነን። ይህን ታሪካዊ ኃላፊነት ለመወጣት፣ የብዙዎችን ደም እያፋሰሰ ከሚገኘው የፌድራል ሥርዓቱና፣ ህወሓት ሰራሹ  ህገ መንግስት መጀመር አለብን፡፡

ተፎካካሪ ፓርቲዎች

“ተፎካካሪ ፓርቲ ነን” የሚሉ ክፍሎች፣ ለለውጡ ከሚሰጡት ጭፍን ድጋፍ ባሻገር፣ ሀገሪቱና ሕዝቡ የደረሱበትን አሰቃቂና አደገኛ ሁኔታ በአንክሮ መመልከት የሚገባቸው ጊዜ ላይ ደርሰናል፤ አይቶ እንዳላዩ የሚሆኑበት ጊዜ አልፏል፤ በዚህ መንገድ የአንድ ዓመት ጉዞ ተደርጓል። ወደኋላ ተመልክቶ አካሄድን ለመፈተሽ በቂ ግዜ አልፏል።

ተፎካካሪ ማለት አማራጭ የሚሰጥ፤ በመርህ ደረጃ ልዩነቱን ለሕዝብ አቅርቦ በጨዋነት የሚታገል፤ “እኔ ከገዥው ፓርቲ የተሻለ ራእይና ፕሮግራም አለኝ” ብሎ ሕዝብን የሚያሳምን አካል ነው፤ በቁልፍ ብሄራዊ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ አቋም የሚወስድ ነው። በማንኛውም ጊዜ፣ ወገን ወይንም ዘውግ ሳይለይ፣ ለሕዝብ ድምጽ የሚያሰማ ነው፤ አለያ ከገዥው ፓርቲ የሚለየው ምንድን ነው?

ተፎካካሪ ፓርቲዎች ነቃ ብለው የሀገሪቷን ፖለቲካ መከታተልና አመርቂ የሆኑ አማራጮችን ማቅረብ መጀመር የሚገባቸው ጊዜ ላይ መድረሳቸውን ሊያውቁት ይገባል፡፡ ስብሰባ ማድረጋቸው በቂ አይደለም!!

በእኔ እምነት፣ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ፣ ተቀዳሚ ሀገራዊ ስራችን ኢትዮጵያንና ዜጎቿን ከባሰ አደጋ መታደግ ነው፤ በየቦታው በየጊዜው የሚቀሰቀሰው ሁከትና ብጥብጥ በእጅጉ አሳሳቢ ነው፡፡ በኢትዮጵያ መቃብር ላይ የሚጠቀም ዜጋ፤ ፓርቲ ወይንም ዘውግ የለም። የትኛውም ህዝብ  በግጭትና በእርስ በእርስ ጦርነት ተጠቃሚ ሊሆን አይችልም፤ ከሶማሊያ፣ ከሶሪያና ከሊቢያ ለመማር ብስለቱ የሌለን ህዝብ አይደለንም፡፡

የአድዋን መቶ ሃያ ሶተኛ የድል በዓል አክብረን ታሪክና እውቅና ያላትን ታላቅ አገር ልክ እንደ ተራ ነገር ችላ ብለን ብትፈራርስ እኛ ብቻ ሳንሆን የልጅ ልጆቻችን ሳይቀሩ ይፈርዱብናል፤ የዓለም ሕዝብ ይስቅብናል። ለም መሬት፤ ወንዝና ሌላ የተፈጥሮ ኃብትና 110 ሚሊየን ለማምረትና ራሱን ለመቻል የሚያበቃ እምቅ አቅም ያለው ሕዝብ በሰው ሰራሽ እርሃብ ቢሞት መሳቂያዎቹ ራሳችን ነን።

የዚህችን ሀገር ውስብስብ ችግሮች “ድርድር አይታሰብም” እየተባለ ልንፈታቸው አንችልም፤ ለድርድር የማይቀርበው ኃይማኖት ብቻ ነው፡፡ የኃይማኖት እምነት የግል ስለሆነ!!

የፖለቲካ እሳቢዎች ከእግዚአብሄር የወረዱ ቃላቶች አይደሉም፤ ጠቃሚ ሆነው ከተገኙ፣ ተግባር ላይ ሊውሉ ይገባል፤ ካልሰሩ ደግሞ፣ የማይጣሉበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ በኔ እምነት “አብዮታዊ ዲሞክራሲ” አይሰራም።

LEAVE A REPLY