“ኢህአዴጎች የአገራችንን ነገር በወግ በወጉ ያዙት” || ሙሼ ሰሙ

“ኢህአዴጎች የአገራችንን ነገር በወግ በወጉ ያዙት” || ሙሼ ሰሙ

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተፈናቃዮች ብዛትና ሰቆቃ ስንቆዝም ሰነበትን፣ ሃዘናችን ሳያልቅ የወገኖቻችን የእርስ በርስ ግጭት ልባችንን ሲያደማው ከርመናል። አሁን ደግሞ የፖለቲካው ትኩሳት ተራውን ወደ ኢኮኖሚ ሰቆቃ እያሸጋገረን ነዉ።

ሰሞኑን ባልተለመደ ሁኔታ ውሃ ለሳምንታት የመጥፋቱ አባዜ ፈተና መሆኑ ሊያባራ አልቻለም። በአናቱ ላይ ደግሞ አቅርቦትንና ጥራትን አሻሽላለሁ በሚል 300 % እጥፍ ድርብ ዋጋ የጨመረብን መብራት ኃይል ተቋሙ በህይወት መኖሩን እስክንጠራጠር ድረስ የጣድነውን ሻይ እንኳን ከምድጃ ለማውጣት ትዕግስት አሳጥቶናል። መብራት ሃይል ግማሽ ሃገራችንን ለቀናትና ለሳምንታት በመብራት እጦት ማወኩን በየሰከንዱ መብራት ማጥፋቱ ሳያንሰው ንብረት ማውደሙን ሙያው አድርጎታል።

የትየለሌ የናረው የአትክልትና የፍራፍሬ ዋጋ እሺ፣ ይሁን ጊዜውም የጾም ስለሆነ ነዉ ብለን ብናልፈውም፤ የዳቦ፣ የዘይት፣ የስኳርና የጤፍ ዋጋ ሰማይ መንካት መንስኤው ምንድን እንደሆነ ሊከሰትልን አልቻለም? ባልተለመደ ሁኔታ የስጋ ዋጋም ጾም ከመገባደዱ በፊት በዚህ ደረጃ መሰቀሉ ምክንያቱ ምን ይሆን ? ጾም ሲያበቃስ ምን እንጠብቅ?

ወይ ቅድመ ዝግጅት አድርገን በቁጠባም ሆነ እንደነገሩ በመኖር ወገባችንን ጠበቅ አናደርግ ዘንድ መረጃ የለንም ወይ አብረን አናለቅስ ነገር አጀንዳው ግራ የገባው “የፈናጅራ” ነዉ።

ኢህአዴጎች እረ እንዲያው በወግ በወጉ ሁኑ። ምን ይመጣልንና ሰቆቃን አቁመን፣ እኛም በወግ በወጉ ስራችንን እንድንሰራ አድርጉን። እኛም እንደ አቅሚቲ የስራ፣ የሃገር፣ የቤተሰብ ኃላፊነትና አደራ አለብን እኮ!?

እንዲያው በጥቅሉ የሰከረ ብሔረተኛ፣ የነጋበት ቢሮክራሲ፣ የደነበረ የለውጥ ሃይል፣ እኔ ብቻ ልኑሮ ባይ ነጋዴና መላ የጠፋው የጸጥታ ሃይል፣ የክላሽና የገጀራ ታጣቂ “ሰላማዊ” ሰልፈኛ መጫወቻ አታድርጉን። ” ውኃ ሲወስድ አሳስቆ ነው የሚባለው ንግርት የወዛ እንዳይመስለችሁ !”

LEAVE A REPLY