ሊያነቡት የሚገባ – የዶ/ር ነጋሶ ቤት || ጽዮን ግርማ

ሊያነቡት የሚገባ – የዶ/ር ነጋሶ ቤት || ጽዮን ግርማ

ጊዜውን አላስታውሰውም። ሰዓቱ ግን የሥራ መውጫ ነበር። ወደ ብስራተ ገብርኤል የሚወስደውን ታክሲ በመጠበቅ ላይ ሳለሁ ዶ/ር ነጋሶን አገኘኋቸው።

ሰላምታ ተለዋውጠን እኔና የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት በአንድ ታክሲ ውስጥ ገብተን ተቀመጥን። በጨዋታ መካከል የቤታቸው ሁኔታ የከፋ ደረጃ መድረሱን ነገሩኝ።

በወቅቱ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ አዘጋጅ ነበርኩ። ከምክትል አዘጋጁ እዮብ ካሳ ጋር ተነጋገርና በማግስቱ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሄድኩ።

ቤቱ ዘመናዊ ቪላ ነው። ግቢውም ደስ ይላል። የጣሪያው ሁኔታ ግን ከጠበኩት በላይ ነበር። ከውጭው ወፍራም ሰማያዊ ላስቲክ እንደ ድንኳን ለብሷል፣ ንፋስ ገልጦ እንዳይጥለው ደግሞ ዙሪያውን ያለው ጫፍ ድንጋይ ታስሮበታል። በአጭሩ ዶ/ር ነጋሶ በድንኳን ውስጥ እየኖሩ ነበር። ውስጥ ስገባ ፍሳሹ ብዙውን የቤቱን ክፍል አበላሽቶባቸዋል። ከላይ ከተሸፈነው ላስቲክ አምልጦ የወጣ ውሃ ቤቱን የባሰ እንዳያበላሸው የልብስ መዘፍዘፊያ ውስጥ በኩል ተደቅኗል። ዶ/ር ነጋሶ ይህንን ታሪክ ሲነግሩኝም ሆነ ቤቱን እያዞሩ ሲያሳዩኝ ፊታቸው ላይ ምንም ቁጡነት አይነበብም ነበር ። እንደውም ትዝ የሚለኝ ስስ ፈገግታቸው ነበር።

እርሳቸውን አነጋግሬ ሳበቃ ካሳንችስ ወደሚገኘው የኪራይ ቤቶች አስተዳደር አመራሁ።
የተሰጠኝ ምላሽ፤

👉”ቤቱን እንዲያስረከቡ እንጂ እንዲኖሩበት ስላልተፈቀደላቸው አይታደስም። ጉዳዩ ደግሞ በፍርድ ቤት ተይዟል።”

👉”ቤቱ የመንግሥት ስለሆነ በራሳቸው ለማሳደስም ሆነ ለመንካት አይችሉም።’

ይህ ከላይ የጻፍኩት ታሪክ በ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ከነፎቶው ታትሞ የወጣ ነው።
—–
ዛሬ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ የቀብር ስነ ስርዓት በክብር ተፈፅሟል። ፈጣሪ ነፍሳቸውን በሰላም ያሳርፈው።

LEAVE A REPLY