ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ || ነአምን ዘለቀ

ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ || ነአምን ዘለቀ

ስለ እውነት እላችኋለሁ ይህ በአገራችን በኢትዮጵያ የመጣው ለውጥ ትልቅ ነን ብለው ራሳቸውን የሰቀሉ ሰዎችን ጨምሮ የራስን ድርሻና የታሪክ አሻራ አግዝፎ ማሳየት፣ ለሌላው እውቅና አለመስጠት፣ በርካታ ሃቆችንም በመደፍጠጥ “እውነትም እውቀትም እኔ ጋር ብቻ ናት” የትግሉም አልፋና ኦሜጋ እኛ ነን የሚል ከሃቁ የራቀ ሚዛናዊም ያልሆነ፣ ግብዝነት የተጠናወተው ለእኔነት፣ (ego ) ለራስ ስብዕና መገንቢያ በሚመች መልክ አጣሞ የማቅረብ፣ ከዚያም አልፎም የሌላውን ድርሻ፣ ድካምና፣ መስዋዕትነት ለማራከስ የመሞከር በጣም የሚያሳዝን ርካሽ ባሕልን እያሰፈነ መጥቷል።

የኢትዮጵያን ሕዝብ አምባገነኑን የወያኔ አገዛዝ ወደ ለውጥ የገፋውን ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ የፈጀ ዘርፈ ብዙ ትግል አንዱ ወይንም ሌላው እሱ ብቻውን ያመጣው መሆኑን የሚያምን በመሆኑ፣ የፓለቲካም ሆነ የሞራል ልዕልና እኔ ጋር ብቻ ነው ብሎም ያለማፈርና ራሱን ወደ ላይ ስለሰቀለ ፣ በዚህም ሳቢያ በግብዝነት የሚኮፈስ መሆኑ እየታየ ነው።

በአገራችን ኢትዮጵያ ያ ሁሉ መስዋዕትነትና ትግል የእውነትና የትግሉ ባለቤት እኔ ነኝ፣ ከራስ በላይ ነፋስ በሚሉ ፣ ነገር ግን ስለኢትዮጵያ ሕዝብ ነጻነትና ፍትህ ጧት ማታ ሲምሉ፣ ሲገዘቱና እኛም በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ አብረናቸው ባሳለፍናቸው ግብዞችና ከንቱዎች ተሞልቶ ኖሯል በሚያሰኝ ደረጃ ላይ መደረሱ እጅግ ያሳዝናል። የኢትዮጵያ ህዝብ ላደረጉት አስተዋጽኦና ትግል የሰጣቸውን ክብርና ሞገስ ፡ የእነሱና የእነሱ ትግል ውጤት ብቻ አድርገው ብዙዎችን የማያካትት ከእነሱም የላቀ ድርሻ ያላቸው እንዳሉም የረሱና፣ ህዝብ ያለፈውን ይቅር ብሎ እንዳቀፋቸው የረሱ፣ እዩን እዩን ስለተባለ ብቻ የትግሉ ባለቤት ከእኛ በላይ ላሳር ያሉ በሕዝብ ጭብጨባ የሰከሩ ብዙ ብዙ ግብዞችን ስንታዘብ እስካሁን ቆይተናል።

እስከ ለውጡ ዋዜማ ድረስ ፣ እንደ አሁኑ የብዙዎች እውነተኛ ማንነት ሳይገለጥልንና ወደ ገሃድ ሳይወጣ ፣ ተከባብሮ ፣ ተቻችሎ፣ ተቀባብሎ በአመዛኙ ለማለት ይቻላል፣ ተዋውጦም ሙሉ በሙሉም ባይሆን፣ በየሕልሙና (ራዕዩ) ጭምር ሁሉም በየፊናው ፣ ለመጣው ለውጥ የድርሻውን ለማበርከት በመቻሉ ነበር ይህ ለውጥ ዕውን ሊሆን የቻለው ። ይህ ለውጥ በአሰርት ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ያደረጉት አስተዋጽዖና መስዋዕትነት ድምር ውጤት ነው። ዛሬ ላይ ያደረሰን ይህ መንፈስ ነበር ለማለት ይቻላል። በአንጻሩ ደግሞ የሌላውን ድካምና መስዋዕትነት ለማኮሰስ መሞከር፣ የራስን የትግል ድርሻና መስዋዕትነት ብቻ ከሚገባው በላይ ለጥጦና አግዝፎ በየመድረኩ መናገርና መጻፍ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የመጣውንም ለውጥ በአንድ እካል ወይንም በጥቂቶች ጥረት ብቻ የተደረሰበት አስመስሎ ማቅረብ እንደ ባሕል እየተወሰደ መጥቷል፡፡ ለትግሉና ለለውጡም የአንበሳውን ድርሻ የእኔ ነው ማለትን የሚመስል ግብዝነት በብዙዎች ዘንድ ሰፍኖአል።

በውጭም በውስጥም የሚገኘው አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ገንዘቡን፣ ጊዜውን፣ እውቀቱንና የልጆቹን ሕይወት ጭምር እንዳልገበረበት፣ ምንም ድምርምር (ሲነርጂ /synergy) እንዳልነበር አስመስሎ በተለያዩ ወገኖች ከሁሉም ጎራ የሚነገር ፣ በየጊዜው እንዱ ሌላውን ለማኮሰስ የሚወረወሩ የቃላት ፍላጻዎች፣ በየመድረኩ የሚደረጉ የተንሸዋረሩ፣ ሚዛናዊ ያልሁኑ፣ ሃቀኝነት እጅግ የሚጎላቸው፣ የእውነትና የእውቀት፣ እንዲሁም የትግል ሞኖፓሊ እኛ ጋር ብቻ ነው በሚል መንፈስ በተወጠሩ ግለሰቦች ጭምር የሚደረጉ ዲስኩሮችና ጽሁፎችን ስናጤን ትልቅ ግምትና ክብር የሰጠናቸው፣ ተስፋም ጥለንባቸው የነበርነውን የበርካታ ሰዎችን ማንነት ለመታዘብ ችለናል።

ያለፍንበትን ሁሉ በዝርዝር የምንጽፈው፣ እያንዳንዱ ጉዳይና ተዋናይንም አስመልክቶ፣ ከየት እስከየት ድረስ እንደሆነ የምናውቀው ብዙ ብዙ በእጃችን ስላለ፣ በታሪክነቱና ለትምህርት ሰጨነቱ ወደፊት ጊዜና ዕድሉ ሲገኝ እንጽፈዋለን። ለአሁኑ ግን በርካታ ዝርዝር ሁኔታ ውስጥ መግባቱ ጠቃሚም አስፈላጊም ስላልሆነ ለጊዜው ሌላውን እንተወውና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ ተቋማት የሚንጸባረቀው ይህን መሰል በዕልህ ከሚደረግ አሳፋሪ ልፊያና እርግጫ ማንም ተጠቃሚ እንደማይሆን በፍጹም አለማወቅና በብዙ ድካምና ልፋት የተገነባን ተቋም ለማፍረስ ቀላል መሆኑን ነው። አስተዋይነት ከጎደለ፣ እኔ ብቻ ባይነት ከተጠናወተ፣ ሁሉም ባለድርሻ ተከባብሮ፣ ተቀባብሎ ፣ በጋራ ሆኖ ለተቀመጠ አላማ ወደ መሃል ካልተመጣ፣ ጽንፍ ይዞ በእልህና እኔ ብቻ እውቃለሁ፣ እኔ ብቻ ነኝ የደከምኩበት ፣ እኔ ብቻ ለፋሁ “አንተ የኔ ሰራተኛ ነህ ” በሚል የሌላውን ክብር የሚነካና ሌላውን ልፋትና ዋጋ በሚያሳጣ መልክ በተለይም ይህን አይነቱን ሃሳብ በየሚዲያው ከሚጽፉ ግለሰቦች የበለጠ የታጋይነት ድርሻና እጅግ የገዘፈ አስተዋጽኦ ያላቸውን ወገኖች ጭምር ክብር በሚነካና ከመልካም ስብዕና በወረደ አመለካከት ተወጥሮ የሚደረግ ሽኩቻ ዞሮ ዞሮ ውጤቱ ወደ ስብራት የሚያመራ መሆኑ አይቀሬ ነው።

በአንጻሩም “እኔ ነኝ ፣ አንተ እዚህ ከጅምሩም አልነበርክ፣ ለተቋሙ/ለሕንጻው ግንባታ የረባ ድርሻ የለህም” ባዩም ለማየት ያልቻለው ከላይ ያልኩትን የሕንጻውም ግንባታ ያለሕብረት፡ ያለመሰረትም ሊሆን እንዳልቻለ ባለማስተዋል የሌሎችን ድርሻና አስተዋጽዖ በመናቅ ፣ እሱ ብቻ በአየር ላይ እንደገነባው በማስመሰል የራሱን ድርሻ ከልኩ በላይ ማግዘፍም ሌላው ጽንፍ ነው። ሁሉም ጎራ ከዚህ አይነቱ አካሄድ እንዲጸዳ ሁሉንም ወገን ተዉ እባካችሁ ስንል፣ ስንዳረቅ የከረምንበት እጅግ ኣድካሚና አሰልቺ ጉዳይ ሆና ቆይቶአል። ያለመታከት ሁሉንም ወገን ስንማጸን፣ ሁሉንም ወገን ስንመክር ቆይተናል። መደማመጥና መከባበርም ተኖ ጠፍቷል፡፡በተቋማት ውስጥም በውጭም ።

ይህ መከረኛ የኢትዮጵያ ሕዝብ ስንቱን ጊዜ አርቀው በማያዩ ልጆቹ ልቡ ይሰበር? እንደ ዕውነቱ ከሆነ ይህ ለውጥ በሀገር ውስጥም በውጭው የብዙዎችን ስብዕናና ዕውነተኛ ማንነት ተገልጦ ለማየት፣ ለመታዘብም የቻልንበትና “ሰው መሳይ በሸንጎ“ የሚለውን የአበው ብሂል በስፋት እንድናጤን ያስገደደን ጊዜ ነው ። አዙሮ የሚያይ አንገት፣ ሚዛናዊ ህሊና፣ ሌላውም ጋር እውነት ሊኖር ይችላል የሚል ትንሽ መጠራጠር እይሰተዋልም፣ ስለሁሉም ጉዳይ እኔ ጋር የእውነትና የእውቀትም ሞኖፖሉ የለም፣ የትግሉም ባለቤት እኔ ጋር ብቻ ሊሆን አይችልም የሚል መንፈስ ጠፍቶእል፣ ስለሌላው ጉድፍ ስናገር የእኔም ጉድፎች ግንዶች ሊሆኑ እንደሚችሉ ግንዛቤም የለም።

የትግሉም ባለቤትና ስኬቱም የኢትዮጵያ ሕዝብ መሆኑን፣ ልዩ ልዩ ተቋማትና ድርጅቶችም ብዙዎች ሕይወት፣ ደም፣ ገንዘብ፣ ንብረት ጭምር የገበሩበት ብዙ ሺ የኢትዮጵያ ልጆች ዘርፈ ብዙ አስተዋጽኦ ያደረጉበት፣ የአስርቱ ሺዎች አይተኬ የህይወት መስዋእትነት ጭምርም እንደሆነ በቅጡና በጥልቀት አንገት ኖሮን ወደ ኋላ ሂደን እመጣጣችንን የሚያገናዝብ፣ ትንሽ ትህትና (humility) እንዲኖረን እጸልያለሁ። ጀርመናዊው ፈላስፋ ኒቼ እንዳስቀመጠው “ጦጣው ጎንበስ ብሎ በፊዝ ይስቅብሃል”። የሰው ልጆች የሚጠናወናቸውን ከንቱነት ለመግለጽ ነበር፣ ሰውም በእርግጥም ሰው “Human all too Human”።

LEAVE A REPLY