የዛሬ ሐሙስ አበይት ዜናዎች || ዋዜማ

የዛሬ ሐሙስ አበይት ዜናዎች || ዋዜማ

1. ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ለወሰንና ማንነት ኮሚሽንና ለብሄራዊ ዕርቅ ኮሚሸን ኮሚሽነሮችን ሾሟል፡፡ ዶክተር ጣሰው ገብሬ የወሰንና ማንነት ኮሚሸን ኮሚሽነር፣ ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ ደሞ ምክትል ኮሚሽነር ሆነው ተሹመዋል፡፡ ሹመቱ የጸደቀው በ25 ተቃውሞ ነው፡፡ የካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ ካርዲናል አቡነ ብርሃነ እየሱስ ኮሚሸነር፣ የትነበርሽ ንጉሴ ደሞ ምክትል ኮሚሸነር ሆነው ተሹመዋል፡፡ ሹመቱ በ10 ድምፀ ተአቅቦና በ4 ተቃውሞ ነው የጸደቀው ፡፡

2. በጊቤ ሸለቆ ብሄራዊ ፓርክ ከሳምንታት በፊት የሞቱት ጉማሬዎች በበሽታ ምክንያት አለመሞታቸው ተረጋግጧል፡፡ ከሚያዚያ 6 እስከ ግንቦት 2 የሞቱት ጉማሬዎች 40 ደርሷል፡፡ ከእነዚህ መካከል 6ቱ ጉማሬዎች ባለፈው ዐርብ ነው በድንገት ሞተው የተገኙት፡፡ ባለሙያዎች የጉማሬዎችን ሞት መንስዔ ለማወቅ ናሙና ወስዶ ምርመራ እያደረገ ሲሆን ውጤቱ ግን ገና አልተገለጸም፡፡ በጉማሬ በሽታ አለመሞታቸው ግን ታውቋል፡፡ ተጨማሪ ጉማሬዎች ወደፊትም ባልታወቀው ምክንያት እንዳይሞቱ ስጋት መኖሩን ሸገር ዘግቧል፡፡

3. የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዛሬ ስብሰባውን ማካሄድ ጀምሯል፡፡ ኮሚቴው በብሄራዊ ደኅንነትና ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ እየተወያየ መሆኑን ፋና ብሮድካስት ዘግቧል፡፡

4. ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የማዕድን ፍቃድ መስጠትና ማስተዳድር እንዲችሉ እንደተፈቀደላቸው ኢቢሲ ዘግቧል፡፡ ዛሬ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀደም ፌደራል መንግሥት ይዞት የነበረውንና አንዳንዴም ለክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በውክልና ይሰጥ የነበረውን የማዕድን ግብይት አዋጅ አሻሽሏል፡፡ ከዚህ በኋላ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ያለ ውክልና ማዕድን ፍቃድ የመስጠትና ማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን ይኖራቸዋል፡፡ የተሻሻለው አዋጅ የማዕድን ላኪነት ፍቃድና የብቃት ምስክር ወረቀት ሲሰጥ እንደ ማዕድኑ ዐይነት እየለየ ይሆናል፡፡ የቀድሞው አዋጅ ግን የማዕድን ላኪነት ፍቃድ ያለው ሰው ሁሉንም የከበሩ ማዕድናት ለውጭ ገበያ እንዲልክ ይፈቅድ ነበር፡፡

5. የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አስተዳደር የሐኪሞች ሥራ ማቆም አድማ የሕግና ሞራል ጥያቄ ያስነሳል ሲል ገልጧል፡፡ ሐኪሞች የሚያነሷቸው ጥያቄች ግን ትክክል ናቸው- ብለዋል የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዛሬ በሰጡት መግለጫ፡፡ ሆኖም ሐኪሞቹ ከሥራ ገበታቸው የቀሩት ቀኑን ሳያሳውቁ፣ ስማቸውን ጽፈው ሳይሰጡና ቀድመው ማስጠንቀቂያ ሳይሰጡ ነው፡፡ በሆስፒታሉ ምን ያህል ሐኪሞች አድማ እንደመቱ ግን አልተገለጸም፡፡ በሥራ ገበታቸው የማይገኙ ከሆነ ግን አስተዳደሩ ወደፊት በሕግ የመጠየቅ ሃሳብ አለው መባሉን ሸገር ዘግቧል፡፡

LEAVE A REPLY