በስሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን ባህልና ስፖርት ፌዴሬሽን ማብራራያ || አድማስ ሬድዮ

በስሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን ባህልና ስፖርት ፌዴሬሽን ማብራራያ || አድማስ ሬድዮ

በስሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን ባህልና ስፖርት ፌዴሬሽን አመራሮች በአትላንታ ተገኝተው ማብራራያ ሰጡ። ይህ የሆነው ባለፈው ቅዳሜ በሂልተን አትላንታ ሆቴል ነበር።

በዚሁ ማብራሪያ ላይ፣ በመጪው የጁላይ ፌስቲቫል ላይ ሜዳ ውስጥ ምግብና ዕቃ የሚሸጡ ሁሉ ማድረግ ያለባቸውንና የሌለባቸውን ነገር እንዲያውቁ ተደርጓል። በሜዳው ውስጥ ብዙ ህጎች እንዳሉ የተጠቀሱት ሃላፊዎች፣ ከዚያ ውስጥ ጠላና ጠጅን ጨምሮ፣ ምንም ዓይነት የአልኮል መጠጥ ማቅረብ የተለከለከለ መሆኑ ይገኝበታል።

ታዳሚዎችን በተመለከተም በአትላንታ ውስጥ መደረግ ያለባቸውንና የሌለባቸውን ህጎች በማወቅ ራሳቸውን እንዲጠብቁ፣ በሚያድሩበት ሆቴልም ይሁን በሚዝናኑባቸው ቦታዎች፣ ከጸብና አጉል ነገሮች ራሳቸውን በመጠበቅ የኢትዮጵያን ስም በበጎ እንዲያስጥሩ አደራ ብሏል።

የዘንድሮው ፌስቲቫል ልዩ የሚያደርገው ሁሉም ሰውና ባለሥልጣን ደጋፊና ተቃዋሚ ሳይባባል በአንድነት በአንድ መንፈስ የሚገኝበት እንደሆነም ተወስቷል።

ጁን 30 የሚጀምረው ይኸው ፌስቲቫል የደመቀ እንዲሆን፣ መክፈቻውን የማሳመር ሃላፊነት የተሰጣቸው የአትላንታ አዘጋጅ ኮሚቲ እና የከተማው ነዋሪ በነቂስ በመውጣት ዝግጅቱን እንዲያደምቅ ጥሪ ቀርቧል።

በማያያዝም፣ ዝግጅቱ የሚደረግበት ሌክ ውድ ስቴዲየም ከዓመታት በፊት ጥሩ ስም ያልነበረው ቦታ ቢሆንም፣ አሁን ግን በጣም ያማረና ምንም ዓይነት ችግር የማይፈጥር ቦታ መሆኑን ቦታው ድረስ ሄደንና አይተን አረጋግጠናልም ብለዋል። 2ሺ መኪና የሚይዘው ማቆሚያ ለብቻው የታጠረ ሲሆን፣ አካባቢው በርካታ መዝናኛዎች ያሉትና አመቺ በመሆኑ ማንም ሰው ያለ ስጋት የሚንቀሳቀስበት ነውም ሲሉ አክለውበታል። በመሆኑም አካባቢው ጥሩ አይደለም የሚለው ወሬ ትክክል አይደለም ተብሏል።

የሰሜን አሜሪካ ስፖርትና ባህል ፌዴሬሽን 36 ዓመት የቆየ አንጋፋና ሁሌም እንደምንለው “ትልቁ የቤተስብ መገናኛ / The largest family reunion” ነው ማለት ይቻላል።

በዚህ የአትላንታ ዝግጅት፣ ቴዲ አፍሮን ጨምሮ፣ ጎሳየ ተስፋዬ፣ ሳሚ ዳን፣ ናቲ ማን እና ሌሎችም አርቲስቶች የየራሳቸው ዝግጅቶች ይኖሩቸዋል።

የመከፈቻውን ዝግጅት ማድመቅ ለክተማችን ክብር በመሆኑ መላው የአትላንታና አካባቢው ነዋሪ እንዲገኝ ጥሪ እናቀርባለን።

ውድድሩ የሚካሄደበው በሌክውድ ስቴዲየም ሲሆን፣ ማርየት ማርኪ እና ሂልተን አትላንታ ደግሞ በቅናሽ የተያዙ ሆቴሎች ናቸው።

LEAVE A REPLY