ዜና ኢትዮጵያ ነገ ሐምሌ 1 ቀን 2011 ዓ.ም

ዜና ኢትዮጵያ ነገ ሐምሌ 1 ቀን 2011 ዓ.ም

በጀነራል አሳምነው ጽጌ ስም አራት መኖሪያ ቤቶች የተገኙ መረጃዎች እያወዛገቡ ነው

ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ የተሞከረውን መፈንቅለ መንግስት መርተዋል በተባሉት በብ/ጀነራል አሳምነው ጽጌ ስም አራት የተለያዩ መኖሪያ ቤቶች መገኘታቸው ተገልጿል፡፡ የፀጥታና ፍትህ የጋራ ግብረኃይል ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ጀነራል አሳምነው ጽጌ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ የተለያዩ መኖሪያ ቤቶች አሏቸው ብሏል፡፡
“ብርጋዲየር ጀነራል አሳምነው ጽጌ ቀድሞም ቢሆን ራሱን ከወንጀል ለመደበቅ በማሰብ የግል መኖሪያ ቤቶች እያሉት በአዲስ አበባ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 የቤት ቁጥር 288 በሆነው፤ በአቶ ወዳጆ ማሞ ባለቤትነት በተመዘገበ ቤት፣ 17ኛው የቤቱ ነዋሪ በመምሰል የከተማዋ ነዋሪ መታወቂያ በማውጣት የወንጀል ቡድኖችን ሲያደራጅ ነበር” የሚለው የግብረኃይሉ መግለጫ በቡራዩ ከተማ ገፈርሳ ኖኖ ቀበሌ የሚገኘው የጀነራሉ የግል መኖሪ ቤት ሲበረበር አንድ ክላሺንኮቭ ጠመንጃ፣አንድ ራቫ ፎር ተሽከርካሪ (መኪና)፣ የተለያዩ ሰነዶችን ጨምሮ የከበሩ ማዕድናት የተቀመጡበት የባንክ ደብተር በማስረጃነት እንደተያዙ ይፋ አድርጓል፡፡
በዚሁ በጀነራል አሳምነው ጽጌ መኖሪያ ቤት ሃምሳ አለቃ ፈቃዱ ሀብታሙ የተባለ የቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት አባል የነበረ እና የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አሰልጣኝ ሆኖ የሰራና ከጀነራል አሳምነው ጋር የቅርብ ወዳጅነት ያለው ሰው፤ ከጀነራል አሳምነው ባለቤት ከወይዘሮ ደስታ አሰፋ ግርማይ ጋር ተሸሽጎ እንደተገኘም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሁለቱም ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በምርመራ እየተጣራ ይገኛል፡፡
በቡራዩ ከተማ “በላኩ ከታ” ቀበሌ በብርጋዲየር ጀነራል አሳምነው ጽጌ ስም የተመዘገበ ሌላ ቤት፣ በአዲስ አበባ በተለምዶ ሐያት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ባለ ሶስት መኝታ ኮንዶሚኒየም (በጀነራል አሳምነው ስም የተመዘገበ) መኖሪያ ውስጥ የተለያዩ ሰነዶችና ክላሺንኮቭ መሳሪያ ተገኝቷል፡፡ በተጨማሪም ሰበታ በሚገኘው የጀነራል አሳምነው ጽጌ መኖሪያ ቤት አንድ ማካሮቭ ሽጉጥ ከበርካታ ጥይቶችና በአዲስ አበባ የፈጠረሩትን የአደረጃጀት ትስስር በአስረጂነት ከሚጠቅሱ ሰነዶች ጋር በቁጥጥር ስር ማዋሉን የጋራ ግብረኃይሉ ካወጣው መግለጫ መረዳት ተችሏል፡፡
ቀረቡ የተባሉት ማስረጃዎች በከፈተኛ ዝግጅት መፈንቀለ መንግስት ለማደረግ አስበዋል የተባሉት ጀነራል አሳምነው ቤት ተገኙ ከተባሉት ጥቃቅን ማስረጃዎች ጋር ሲታይ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግስት የአዲስ አበባውን ግድያ ከባህርዳሩ ውዝግብ ጋር ለማቆራኘት የሚያደርገው ዝግጅት ውጤት አለማምጣቱን አመላካች ነው የሚሉ አስተያየት ሰጭዎች መንግስት በሁለቱ ከተሞች የተከሰተውን ግድያ በተናጠል በመመልከት ትክክለኛ የምርመራ ውጤት ለሀዝብ ማሳዎቅ እንደሚገባ ገልጸዋል::
ምረመራው በአጭር ጊዜ ለህዝብ ለማሳዎቅ ብሁለቱ ከተሞች ላይ የተፈጸመውን ግድያ ነጣጥሎ ማየት ብቸኛ መንገድ ነው የሚሉ የዛኢስ አበባ ነዋሪ ጌነራሉ ብይተ ተገኙ የተባሉ ቀሳቁሶችም ሆኑ በውል ያልተብራሩ ሰነዶች በምንም አይነት መለኪያ መንግስትን ለመገልበጠ የታሰበ ነው ለማለት አያስቸሉም ብልዋል::
አዴፓ መደበኛ ስራውን በአግባቡ በመቀጠል እየሰራ መሆኑን ያሳዎቁት የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮነን ዛሬ ባስተላለፉት መልእክት የአማራን ህዝብ ሰላም ዙሪያ እና ወደፊት ልናከናውን በምንችላቸው ጉዳዮች ዙሪያ ግምገማ አድርገን በእሳቸው በዶክተር አምባቸውና በጄነራል አሳምነው መካከል ምንም አይነት ልዩነት እንዳልነበረ ከግድያው ሶስተ ቀናት ቀደም ብሎ ባካሄዱት ውይይት ተረድተው እንደነበር አውስተዋል::

የፋሲል ከነማ ተጫዋቾችና ደጋፊዎች ዛሬ በትግራይ ተደበደቡ: የፋሲል ደጋፊዎች ሰላማዊ ሰልፍ ተከለከሉ

ግልፅ የሆነ የዳኝነት ስህተትና በደል የተፈፀመበት፣ ዋንጫውንም በግፍ የተነጠቀው የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ቡድንና ደጋፊዎቹ ዛሬ ከትግራይ ሊወጡ ሲሉ ድብደባ ተፈፅሞባቸዋል፡፡
የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊን ለመለየት ትናንት በተለያዩ ከተሞች በተደረገው ውድድር ዋንጫውን ሊወስድ ይችላል ተብሎ የተገመተው ፋሲል ከነማ፣ ከሽሬ እንደስላሴ ጋር ባደረገው ጨዋታ አቻ መለያየቱን ተከትሎ “አወዛጋቢው መቐለ 70 እንደርታ” ሻምፒዮን ለመሆን ችሏል፡፡
ዓመቱን ሙሉ በተለያዩ ውዝግቦችና ስህተቶች እንዲሁም በበርካታ የብሔር ተኮር ነውጦችና ግጭቶች ታጅቦ የዘለቀውን የ2011 ዓመታዊ የመጨረሻ ውድድሩን ለማድረግና ሻምፒዮንነቱን ለማረጋጥ ወደ ትግራይ የተጓዘው ፋሲል ከነማ፤ ክለቡና ደጋፊዎቹ ክልሉን
ከረገጡበት ቀን ጀምሮ ከፍተኛ በደል እንደደርሰባቸው ተነግሯል፡፡
በአስር አውቶቢስ ተጭነው ከቡድኑ ጋር ወደ ትግራይ የተጓዙት የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች፤ በሜዳ ላይ ድል ሳይቀናቸው በመቅረቱ ዋንጫውን መቐለ 70 እንደርታ ሲወስደው ለመመልከት ተገደዋል፡፡ በመቐለ 70 እንደርታ ሻምፒዮንነት የተደሰቱ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች፣ ውጤቱ ከቀኑ 11፡00 ሰዓት ላይ ተግልጿል::
የፋሲል ከነማ ደጋፊዎችና ተጫዋቾች እስከ ምሽቱ 3፡00 ድረስ ከስታዲየም እንዳይወጡ ከመጠን ያለፈ የደስታ አገላለለፅ በማሳየት ችግር እንደፈጠሩባቸው ከደረሰን ዜና መረዳት ተችሏል፡፡ በጨዋታ እስከ 75ኛው ደቂቃ ድረስ ሽረ እንደስላሴን አንድ ለባዶ ሲመራ የቆየው ፋሲል ከነማ ያለ አግባብ በተሰጠ ፍፁም ቅጣት ምት ዋንጫውን ለማጣት እንደተገደደ፣ በሜዳ ላይም ግልፅ የሆኑ የዳኝነት በደሎች እንደደረሱበት የገለፀው የፋሲል ከነማ አሰልጣኝ ውበቱ አባቱ፤ የቡድኑ ተጫዋችና ደጋፊዎች ዛሬ ከትግራይ ክልል ሊወጡ ሲሉ በበርካታ የክልሉ ነዋሪዎች ድብደባ እንደተፈፀመባቸው ተናግሯል፡፡
“ገና ወደ ክልሉ ከገባንበት ጊዜ አንስቶ በከተማው ውስጥ የነበረው ድባብ ፍፁም ደስ የማይልና አሳዛኝ ነበር” ያለው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ፣ “በአስር መኪኖች ተጭነው ከጎንደር የመጡት ደጋፊዎች የደረሰብንን ግፍና በደል ተቋቁመው ወደ ቤታቸው ለመመለስ
ባደረጉት ሂደት ውስጥ በነዋሪዎች የድንጋይ እሩምታ ክፉኛ ተደብድበዋል” ብሏል፡፡
ዛሬ ሐምሌ 1 ቀን 2011 ዓ.ም ከትግራይ ወደ ጎንደር እየተመለሱ በነበሩ በርካታ የፋሲል ከነማ ደጋፊዎችና ተጫዋጮች ላይ የመፈንከት አደጋ፤ እንዲሁም የመኪኖች መሰባበር የደረሰ መሆኑን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ አስታውቋል፡፡
የ2012 የፌደራል መንግስት ከፍተኛ በጀት ጸደቀ: የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ በአዲስ መልክ ተቀርጿል
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለ2012 በጀት ዓመት የቀረበውን 386 ቢሊየን 954 ሚሊየን 965 ሺህ 289 ብር የፌዴራል መንግስት በጀት አጸደቀ። የጸደቀው በጀት ለተለያዩ የመንግስት ስራዎች የሚውል ነው:: የጸደቀው በጀት 109 ቢሊየን 468 ሚሊየን 582 ሺህ 456 ብር ለመደበኛ ወጪዎች ይውላል ተብሏል። ለካፒታል ወጪዎች ደግሞ 130 ቢሊየን 710 ሚሊየን፣ 876 ሺህ 568 ብር የሚውል ይሆናል። በተጨማሪም 140 ቢሊየን 775 ሚሊየን 506 ሺህ 265 ብር ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ እና 6 ቢሊየን ብር ደግሞ ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈፅሚያ ድጋፍ እንደሚውል የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
በተጨማሪም የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት በ48ኛ መደበኛ ስብሰባው የተጨማሪ እሴት ታክሰ አዋጅን በሙሉ ድምፅ አጽድቋል፡፡ አዋጁ በገቢ አሰባሰቡ ላይ ችግር ፈጥረዋል የተባሉ የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ድንጋጌዎችን በማሻሻል ሥራውን በተቀላጠፈ ሁኔታ ለማስኬድ የሚያስችል እንደሆነም ተነግሯል፡፡
የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ለምለም ሀደጎ ለም/ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ላይ ከዋለ አስራ ሰባት ዓመታትን ያስቆጠረ በመሆኑ ረቂቅ አዋጁን አሁን ካለው ነባራዊ የኢኮኖሚ የእድገት ደረጃ ጋር ማጣጣም አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ብለዋል፡፡
ም/ቤቱ በዚህ 48ኛ መደበኛ ስብሰባው የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ሪቂቅ አዋጅንም አፅድቋል፡፡ አዋጁ የኢንዱስትሪ ሰላምን በማስፈን የምርታማነት የገቢያ ተወዳዳሪነት አቅም ለመፍጠር ያስችላልም ተብሏል፡፡ በም/ቤቱ የሴቶችና የወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ አበባ ዮሴፍ አዋጅ ከመፅደቁ በፊት ከኢትዮጵያ አሰሪዎችና ሰራተኛ ማህበራት ፌደሬሽኖችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ሲደረግበት ቆይቷል ብለዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮምና ስድስት ስኳር ፋብሪካዎች ወደ ግል ይዘዋወራሉ
በመንግስት ቁጥጥር ስር የሚገኙ ግዙፍ ተቋማትን ወደ ግል ለማዞር በሚደረገው ጥረት ኢትዮ ቴሌኮምን ለሁለት በመክፈል 49 በመቶውን ወደ ግል ድርጅት ለማዞር አቅጣጫ መቀመጡ ታወቀ፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም አንድ ኩባንያ ሆኖ የተወሰነ ድርሻው ወደ ግል ሲዞር፣ አደረጃጀቱ በአገልግሎትና በመሰረተ ልማት (መስመር ዝርጋታ) ዘርፍ ይከፋፈላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በጨረታ ሁለት ኩባንያዎች ብቻ ራሳቸውን ችለው የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት
እንዲሰጡ የሚያስችል የፈቃድ አሰጣጥም ይዘረጋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ለሁለት ሲከፈል የመስመር ዝርጋታው ዘርፍ ዓለም አቀፍ መገናኛዎችን፣ ሀገር አቀፍ ፋይበር ኦፕቲክ፣ የኔትወርክ ማማ ዓይነት መሰል ግንባታዎችን የመከወን ድርሻና ኃላፊነት ይኖረዋል፡፡ የአገልግሎት ዘርፉ ደግሞ የሁሉንም የስልክ፣ የኢንተርኔት እና ተጨማሪ አገልግሎቶችን፣ የችርቻሮ ሽያጭ ኃላፊነትን ይወስዳል፡፡
ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ከሚሰራው የግል ኩባንያ በተጨማሪ ሁለት የግል ተቋማትን ብቻ የሚጋብዝ የገበያ አመራር እንዲተገበር የታሰበው፤ ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚና የዘርፉ ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት መንግስት አስፈላጊውን ቁጥጥር ለማድረግ እንዲቻል ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የስኳር ዘርፉንም ወደ ግል ድርጅቶች ለማዞር በሚደረገው እንቅስቃሴ ስደስት የስኳር ፋብሪካዎች በቀጣይ ዓመት ለሽያጭ እንደሚቀርቡ ታውቋል፡፡
በአገሪቱ ካሉት አስራ ሶስት የስኳር ፋብሪካዎች ስድስቱ ሙሉ ለሙሉ ወደ ግል ድርጅቶች ይዛወራሉ:: የኢትዮጵያ መንግስት የስኳር ፋብሪካዎቹን ለመሸጥ ያለውን ፍላጎቱን ማሳወቁን ተከትሎ በኬንያ፣ በምዕራብና ሰሜን አፍሪካ እንዲሁም በሩቅ ምስራቅ የሚገኙ ድርጅቶች የተለያዩ የስኳር ፋብሪካዎችን ለመግዛት ከወዲሁ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
የጀጎል ግንብ ከዓለም የቅርስ መዝገብ ሊሰረዝ ይችላል
በታሪካዊው የጀጎል ግንብ ዙሪያ ሕገ ወጥ ቤቶች በስፋት በመገንባታቸውና የቅርሱ ይዞታም ለአደጋ በመጋለጡ የጀጎል ግንብ ከዓለም የቅርስ መዝገብ ላይ ሊሰረዝ ይችላል ተባለ፡፡
በተባበሩት መንግስታት የባህል የሳይንስና ትምህርት ማዕከል (ዩኔስኮ) መዝገብ የሰፈረው ጀጎል ግንብ፣ በአካባቢው ከተገነቡት ቤቶች መሀል ሰባ በመቶ ያህሉ ሕጉ ከሚፈቅደው ውጪ በብሎኬት የተሰሩ ናቸው፡፡ እኒዚህ ቤቶች መፀዳጃ ቤት የሌላቸው በመሆኑ፣ በርካታ ነዋሪዎች በአካባቢው በመፀዳዳት፣ (በፕላስቲክና በጠርሙስ ጨምሮ) የተለያዩ ቆሻሻዎችን በመጣል አካባቢውን ከፉኛ በመበከል ለጎብኚዎች ችግር ፈጥረዋል፡፡
በጀጎል ግንብ ዙሪያ የመኪና እጥበት ሥራ እየተከናወነ መሆኑ በራሱ ግንቡን ለመፈራረስ አደጋ እያጋለጠው ይገኛልም ተብሏል፡፡ ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ መዝገብ ዝርዝር ውስጥ የሰፈው 66 ሄክታር መሬት የሚሸፍነው የጀጎል ግንብ፤ ከሰው ሰራሽ ችግሮቹ ፀድቶ ቀድሞ ወደነበረው አስተማማኝ ይዞታው መመለስ ካልቻለ፣ ከዓለም ቅርስ መዝገብ ሊሰረዝ እንደሚችል የኢትዮጵያ ቅርስና ጥበቃ ባለስልጣን የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ም/ዳይሬክተር ነጃት ከማል ተናግረዋል፡፡

LEAVE A REPLY