የዘር አወቃቀሩና ፖለቲካው ከቀጠለ አገር ትፈርሳለች፣ ደም ይፈሳል (ግርማ ካሳ)

የዘር አወቃቀሩና ፖለቲካው ከቀጠለ አገር ትፈርሳለች፣ ደም ይፈሳል (ግርማ ካሳ)

የክልሉ ባለስልጣናት ከተናገሩትና እንደ ቢቢሲ፣ ሮዮተርስ ያሉ የአለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ፣ እንዲሁም እንደ ኢሳት ያሉ ሜዲያዎች ከዘገቡት ለመረዳት እንደሚቻለው፣ ኢጄቶ የተባለው ቡድን፣ ሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም፣ በጀመረውና ባልተሳካለት የሲዳማ ክልልን በጉልበት የማወጅ እንቅስቃሴ፣ ከሃያ በላይ ዜጎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። በአዋሳ አንድ ወጣት ግንባሩ ላይ በጥይት ተመቶ ወዲያው እንደሞተ፣ ሶስት ቆስለው የሕክምና እርዳታ ቢደረግላቸው መትረፍ እንዳልቻሉ ኢሳት ዘግቧል። ቢቢሲ በወንዶ ገነት ሶስት ፣ ሮይተርስ ደግሞ በዋተራ ካሳ አስራ ሶስት ኢትዮጵያውይን መገደላቸውን ዘግበዋል።

እነዚህ በግልጽ የታወቁና የተረጋገጡ ሲሆኑ የሟቾች ቁጥር ከመቶ ፣ የቆሰሉ ደግሞ ከአራት መቶ በላይ እንደሆኑ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በሃገረ ሰላም 26፣ በወንዶገነት 8፣ በዳሌ 5፣ በላኮ 6፣ በአገታ ጉኮ 5፣ በአፋራራ 2፣ በአለታ 2 ዜጎች መገደላቸውን ሲዳማ ፔጅ የተሰኘው ገጽ አስፍሯል።

የተወሰኑት ሕይወታቸው ያለፈው ከታጣቂዎች በተተኮሰ ጥይት ሲሆን፣ ኤጄቶዎች በግፍ የገደሉዋቸው የሌሎች ማህበረሰባት አባላትም ቁጥር ብዙ ነውና በንዴትና በበቀል፣ በጥላቻ፣ ሲዳማ ባልሆኑ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የደረሰውም ዘር ተኮር ጥቃት ጥቃት በጣም አስከፊ ነበር። ለምሳሌ በሃገረ ሰላም አቶ የንዬ የሚባሉ ግለሰብ በኤጀቶዎች በተፈፀመባቸው ድብደባ ተጎድተው ጤና ጣቢያ ገብተው የነበረ ቢሆንም፣ በነጋታው፣ ልጃቸው ሊጠይቃቸው ሄዶ ሳለ፣ አጄቶዎች በድንገት ጠያቂ መስለው፣ ጤና ጣቢያ ውስጥ ገብተው አባትና ልጅን በቀርቀሃ ዱላ ቀጥቅጠው መግደላቸውን ከስፍራው የደረሱ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በድንጋይ ተወግረው የሞቱም ብዙ ናቸው።

በዜጎች ሕይወት ላይ ከደረሰው አሳዛኝ ጥፋት በተጨማሪ በርካታ ሱቆች፣ ቢዝነሶች የግሎ መኖሪያ ቤቶች፣ እንዲሁም ቤተ እምነቶች ተቃጥለዋል። ቢያንስ ሰባት ቤተ ክርስቲያናትና እውን መስኪድ ወድሙዋል። ኢጄቶዎች ቤት ለቤት እያሰሱ ሲዳማ ያልሆኑ ኢትዮጵያዉያንን ላይ ኢሰብአዊ ድርጊት በመፈጸም ብዙዎችን ቤት አልባ አድርገዋል። በሐዋሳ ዙሪያ ሪፈራል፣ዶሮ እርባታ፣ትንባሆ ሞኖፖል ተብለው በሚጠሩት አካባቢዎች ቤቶች ፈርሰዋል። የንግድ ተቋማት ወድመዋል። ይርጋለም የሚገኘው ታዋቄ የአረጋሽ ሎጅ ወድሟል።

ከኢጂቶ ጋር ያብሩ ነበር በሚል በርካታ ፖሊሶች የታሰሩ ሲሆን ሌሎች ብዙዎች መሳሪያቸውን እንዲያስረክቡ ተደርገዋል።

የሲዳማ ዞን በአሁኑ ወቅት ሙሉ ለሙሉ ማለት ይችላል በፌዴራል የመከላከያ ቁጥጥር ስር ያለች ሲሆን፣ በአዋሳ ከተማና በዞኑ መረጋጋት እየሰፈነ እንደሆነ እየሰማን ነው።

ይሄ ሁሉ ግን ለምን ???? እስከ መቼ በአገራችን እንደዚህ የሰው ልጅ ክብር አጥቶ ደም በቀላሉ ይፈሳል ?

የሲዳማ ዞን ምክር ቤት ያቀረበውን የዞን ጥያቄ በተመለለተ ምርጫ ቦርድ በአምስት ወር ውስጥ ሕዝብ ዉሳኔ እንደሚያደርግ፣ ከዚያ በፊት ግን በአስር ቀናት ውስጥ በአዋሳ ጉዳይና በሲዳማ ዞን በሚኖሩ ሲዳማ ባልሆኑ ሌሎች ማህበረሰባት ዙሪያ የክልሉ መንግስት ማብራሪያ እንዲሰጥ መጠየቁ ይታወቃል።

በርካታ የሲዳማ አባቶችና ሽማግሌዎች “ከአምስት ወር በኋላ ተብለናል። ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ ጥያቄዎቻችንን ማስኬድ አለብን” በሚል አላስፈላጊ፣ ሰላምን የማወክ ተግባራት እንዳይፈጸሙ ጥሪ ቢያቀርቡም፣ በኦሮሞ ጽንፈኞች የሚደገፈው፣ ራሱን ኢጂቶ ብሎ የሚጠራው ቡድን ግን ለመስማት ፍቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። እንግዲህ አንዱ ትልቁ ችግር ፖለቲካችን የግትርነት ፖለቲካ መሆኑ ነው። ኢጄቶ ባለመስማቱ በአካባቢው አላስፈላጊ ጥፋት ሊከሰት ፣ የብዙ ሰዎች ደም ሊፈስ ችሏል። በመሆኑም በአዋሳና በሲዳማ ዞን ለፈሰሰው ደም ኢጄቶና በሐሳብና በገንዘብ ከኋላ ሆነው ቅስቀሳ ሲያደርጉላቸው የነበሩ የኦሮሞ ጽንፈኞች መጠየቅ አለባቸው።

ኢጄቶዎች ሰሞኑን የፈጸሙት የዘር ጥቃትና ሽብር የመጀመሪያው አይደለም። ከአንድ አመት በፊት ብዙ ጊዜ በሌሎች ማህበረሰባት አባላት ላይ ሰቆቃን ፈጽመዋል።። በተለይም ወላይታዎች ላይ። ዜጎችን በሕይወት እያሉ በእሳት በማቃጠል፣ የጭካኔ ጥግን አሳይተዉንም ነበር። በአዋሳ ከተማ ገዢው ፓርቲ ደሃዴን ራሱ ስብሰባ እንዳያደረግ እስከመረበሽ የደረሱ ሲሆን፣ ደሃዴን በኢጂቶዎች ምክንያት በክልሉ ዋና ከተማ በአዋሳ መስብሰብ አቁሟል። በቅርቡ ያደረገውን ስብሰባ ያደረገውን በአዲስ አበባ ነበር። ኢጄቶ በአዋሳና በሲዳማ ዞን መንግስት ሆኖ ፣ አባሯቸው ማለት ነው። (በነገራችን ላይ ይሄ ነበር መፈንቅለ መንግስት ሊባል ይገባው የነበረ)

ሃላፊነታቸው መወጣት ያልቻሉ፣ ሕግን ማስክበር የተሳናቸው፣ በአቶ ሚሊዮን ማቴዎስ የሚመራው የደቡብ ክልል መስተዳደርና በወ/ሮ ሙፈሪያት የሚመራው ደሃዴን፣ የአዋሳ ከተመ መስተዳደርና የሲዳማ ዞን አመራrኦችም ለፈሰሰው ደም ተጠያቂ ናቸው። ሃላፊነታቸውን ሙሉ ለሙሉ ለኢጂቶ በማስረከባቸው።

በአዋሳና በሲዳማ ዞን ኢጂቶዎች ከቁጥጥር ውጭ እየወጡ መሆናቸውን፣ የፊዴራል መንግስት ሃላፊዎች አያውቁም ነበር ማለት አይቻልም። ነገሮች ከመባባሳቸው በፊት አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ፣ ችግሮች እንዲባባሱ የሚያደርጉ ጸረ-ሰላም ሃይላትን ከወዲሁ በመቆጣጠር ፣ ከኢጄቶዎች ጋር በጥቅም ታያይዘው እያበሩ ያሉ የክልሉ፣ የዞንና የወረዳ ታችኛው የደሃዴን አመራሮችን መስመር በማስያዝ ችግሩን ከወዲሁ እንዳይፈጠር ማድረግ ይችሉ ነበር። ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና የፌዴራል መንግስቱ ተጠያቂ ለሆነው ነገር ተጠያቂ ናቸው። በዚህ አጋጣሚ ኢጂቶዎችን ከበስተጀርባ ሲገፋፉ የነበሩት እንደ ጃዋር ያሉ ግለሰቦች፣ ከዶር አብይ መስተዳደር ሙሉ ድጋፍና ጥበቃ እየተደረገላቸው የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን መርሳት የለብንም።

በአራተኛ ደረጃና እንደውም በዋናነት ተጠያቂ መሆን ያለባቸው ኦነግና ሕወሃት ናቸው። እነዚህ ሁለት ቡድኖች ከሃያ ስምንት አመታት በፊት በአገራችን የዘር ፖለቲካ ሕጋዊ ማእቀፍ እንዲኖረው ያደረጉ ናቸው። ይሄ የጎሳ ክልል የሚሉትን እርግማንና የሲዳማ፣ የወልያታ የአማራ፣ የትግሬ …መሬት እያሉ ዜጎችን የሚከፋፈል አወቃቀር ያመጡብን እነዚህ ቡድኖች ናቸው። ሲዳማና ወላይታ፣ ሶማሌና ኦሮሞ፣ ሶማሌና አፋር፣ አማራና ኦሮሞ፣ አማራና ትግሬ፣ ጌዴኦና ኦሮሞ፣ ጉራጌና ቀቤና፣ ቡርጂና ቦረና፣ ጉሙዝና ኦሮሞ፣ ጋሞማ ጎፋ፣ ኦሮሞና አዲስ አበቤ …እየተባባልን የምንጋጨው ያንተና የኔ የሚል ከዘር ጋር የተገናኘ አሰራር በመዘርጋቱ ነው። ሁላችንም የአንድ አገር ልጆች ሆነን፣ በጋራ አገራችንን ከማሳደግ፣ “የኔ የሆነ ያንተ ነው፣ ያንተ የሆነ የኔ ነው” ብለን ከመያያዝ፣ እርስ በርስ እንድንከፋፈል፣ በመካከላችን አጥር እንዲኖር ተደርጓል። አሁን ባለው የፌዴራል አወቃቀርና ኢትዮጵያዊነትን የማያጎላው ሕግ መንግስት ።

በሲዳማ የሆነው በስፋት መቀጣጠሉ አይቀርም። ተመሳሳይ አሳዛኝ ክስተት እንዳይፈጸም ምን ይደረግ ?

አሁንም መፍትሄዎቹ ፍቃደኝነት ካለ ውስብስብ አይደሉም፡

1. ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ኢመደባዊ የሆኑ፣ ከመንግስት መዋቅር ውጭ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ያደረጉ ቡድኖች ላይ በአስቸኳይ እርምጃ መዉሰድ አለባቸው። በተለይም በኦሮሞ ክልል ራሳቸውን ቄሮ ብለው የሚጠሩ ፣ ሌላው ማህበረሰብን የሚያንገላቱ፣ ግብር ሁሉ የሚጠይቁ ቡድኖች አሉ።፡ የኢጂቶዎች ታላቅ ወንድሞች የሆኑ። እነርሱን በቶሎ አደብ ማስገዛት ያስፈለጋል። በአማራ ክልል ራሳቸውን ፋኖ ብለው የሚጠሩ ከክልሉ መስተዳደር ሕጋዊ ማእቀፍ ውጭ ያሉ ለህግ እንዲገዙ መደረግ አለበት። በትግራይ ያለው ሕገ ወጥነት መቆም አለበት። ሕግ መከበር ይኖርበታል። ማንም ቡድን ወይም ግለሰብ፣ ከየትኛውም ጎሳና ብሄረሰብ ይሁን፣ ከሕግ ውጭ እየተንቀሳቀሰ ህዝብን እንዲያውክ ሊፈቀድለት አይገባም።

2. በሲዳማ የታየው ችግር ጨዋታው ዘር በመሆኑ ነው። የአገሪቷ ሲስተም፣ ሕግ መንግስቱ ከዘር ጋር ስለተገናኘ ነው። ከላይ በአጭሩ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ለአንዱ ተፈቅዶ ሌላውን መከልከል አይቻልም። ሃረሬዎች፣ አፋሮች፣ ኦሮምዎች፣ አማራዎች፣ ሶማሌዎች.. የራሳቸው ክልል ካላቸው፣ ሲዳማዎችም የሚከለከሉበት ምንም ምክንያት የለም። ሲዳማዎች ከተፈቀደላቸው ወላያታዎች፣ ሃዲያዎች፣ ጉራጌዎች በምን ያንሳሉ። በጉራጌ ዞን ውስጥ ያሉ ቀቤኔዎችም ክልል መሆን ከፈለጉ መብታችው አይደለም ወይ ? በደቡብ ክልል ብቻ ወደ 56 በአገር አቀፍ ወደ መቶ ክልሎች ሊፈጠሩ ይችላሉ።

ያ ብቻ አይደለም፣ ሕብረ ብሄራዊ የሆኑ፣ አንዱ ጋር አንዱ ብሄረሰብ፣ እልፍ ብሎ ሌላው የሚኖሩባቸው አካባቢዎች ብዙ ስላሉ፣. የይገባኛል ጥያቄዎች ስፍር ቁጥር አይኖራቸውም። ድሬዳዋ፣ አዲስ አበባ፣ ሞያሌ፣ ወልቃይት፣ ራያ፣ ሸዋ፣ ጉርሱም፣ ባቢሌ፣ ሻሸመኔ፣ ወሎ፣ መተከል፣ ሃረር…ብዙ አካባቢዎች የይገባኛል ጥያቄ ያለባቸው ናቸው። እነዚህን ሁሉ ለአንዱ ሰጥቶ ፣ ለሌላው እየነፈጉ እንዴት ነው ማስተናገድ የሚቻለው ? ስለዚህ የጎሳ ግጭቶች በሽ በሽ እንደሚሆኑ መገመት አያስቸግርም። በሶማሌና በኦሮሞ ክልል መካከል ከ400 በላይ ቀብሌዎች የይገባኛል ውዝግ እንዳለ መጥቀሱ ብቻ ይበቃል።

ስለዚህ አሁን ያለው በዘርና ቋንቋ ላይ የተመሰረተው ፣ የኔና የናነተ መሬት የሚል የፌዴራል አወቃቀር ቀርቶ፣ ዘመናዊ፣ ለአስተዳደር አመች የሆነ፣ የሁሉንም ባህል፣ ቋንቋ የሚያከብር፣ በእኩልነትና በአንድነት ላይ የተመሰረተ የፌዴራል አወቃቀር ያስፈልገናል።

ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ የወሰንና ማንነት ኮሚሽን አቋቁመዋል። ይሄ ኮሚሽን ስራውን እየሰራ አይመስልም። በመሆኑም ራሳቸው ዶ/ር አብይ አህመድ በአስቸኳይ አገራዊ ጉባዬ ጠርተው ይሄ አገርን ወደ ገደል እየከተተ ያለውን፣ የዘር አወቃቀር እንዲቀየር ቢያደርጉ መልካም ነው እላለሁ። አማራ፣ ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ ሲዳማ …መባባል መቆም አለበት።

LEAVE A REPLY