የወሎ አይነ ኩሌ!!!!! || በመንግስቱ ዘገዬ

የወሎ አይነ ኩሌ!!!!! || በመንግስቱ ዘገዬ

ወንዛችን ቦርከና ፤ እርሻችን ታች ቃሉ ፤
የወሎየን ፍቅር ፤
እንኳን ያደም ልጆች ፤ ወፎቹም ያውቃሉ ።

መገን ጃኖ ሙሄ ፤
መድሃኒቴ እኮ ናት እንደዳማ ከሴ ፤
ባይሆን ተቸገርኩኝ ፤
ቤቷ ጨፋ ሆኖ ፤ አልጋዋ ከሚሴ ።

አገሯ ወሎ ነው ፤ ደወይ ራህማቶ ፤
ልዘይር እያለ ፤
ሁሉም ቀልጦ ቀረ ፤ ከማጀቷ ገብቶ ።

በአንቻሮ በገዳም ፤
ካንጀቴ የገባች ፤ አንዲት ኮረዳ አለች ፤
ሃርቡ ተሜዳው ላይ፤
ልቤን ወሰደችው ከረሚሌ ዳማ ሽቱ ብሬ እያለች ።

ይሻለኝ እንደሆን ፤
ይቀለኝ እንደሆን ፤
በደዋ በጨፋ ፤አምጧት ፈልጋችሁ ፤
አልከጀለች እንደሁ ፤
ሶደቃ ላኩልኝ ከንፈሯን ቆርሳችሁ ፤
አለበለዚያማ ፤
ካቲማየ ፈርሶ ፤
ጅስሜ ተደባልቆ እንዳልሞትባችሁ ።

ስንቱን በውጅግራ ፤
ስንቱን በምንሽር ፤ ገድለን ስናበቃ ፤
ጃኖየ መሃመድ ፤
እኛን ገደለችን ፤
በእርጎ ዳማይ ጥርሷ ፤ ከምከም ብላ ስቃ ።

በዚህ በኛ መንደር፤
ኸልቁን የሚፈጀው ረሃብ ነበረ ፤
ጉድ አጃኢብ በሉ፤
በቃሉ በአንቻሮ ከንፈር ሰው ገደለ ።

ሞይዘሬን ባነግት ፤
ዝናሬን ብታጠቅ ፤
ፊትም አልሰጠችኝ ፤ ኧረ መቼ ሰምታ ፤
እኔም መለኛ ነኝ ፤
መዳኒት አውቃለሁ ለመውደድ በሽታ፤
በገታ በመጂት ፤
ወዳጃ አስገብቼ ፤ ወሰድኳት ባንዳፍታ ።

ኧረ መጂት መጂት ፤ ኧረ ገታ ገታ ፤
ታስሮ የከረመው ፤ በመውደድ በሽታ ፤
ዱኣ ያስደረገ፤
ቱፍታ የደረሰው ስንቱ ጎበዝ ሻረ ስንት ሰው ተፈታ ።

ጃኖ መንግስቱ ዘገየ

LEAVE A REPLY