በባሕር ዳር አንዲት ሴት በመንግስት ባለስልጣን ላይ አሲድ ደፋች

በባሕር ዳር አንዲት ሴት በመንግስት ባለስልጣን ላይ አሲድ ደፋች

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ባሕር ዳር በሚገኘው የክልሉ የመንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ውስጥ በሚሰሩ አንድ ባለስልጣን ላይ አንዲት ሴት አሲድ በመድፋት ጥቃት ፈጽማ ጉዳት ማድረሷ ታወቀ::

ድርጊቱ የተፈጸመው ነሐሴ 02/2011 ዓ.ም ጠዋት ላይ ሲሆን ግለሰቧ ባሕር ዳር በሚገኘው የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የመንገድ ትራንስፖርት ቢሮ የስምሪት ዳይሬክቶሬት ዳይሬከተሩን ለማግኘት እንደምትፈልግ ጠይቃ ሓላፊው ስብሰባ ላይ እንደሆኑ ተገልጾላት ትመለሳለች።

  በድጋሚ በዚያኑ ቀን ከሰዓት በኋላ ተመልሳ ወደ ሓላፊው ቢሮ የመጣችው ይህችው ሴት በ2008 ዓ.ም በህጋዊ መንገድ ‘እፎይታ’ በሚባል ማህበር ስም የተመዘገበ ባጃጅ መግዛታቸውን እና በዚህም ለተወሰነ ግዜ የስምሪት መርሃ ግብር ወጥቶላቸው ባጃጁ በሥራ ላይ ተሰማርቶ መቆየቱን ትናገራለች።  በኋላ ላይ ግለሰቧ ምክንያቱን አላውቀውም በምትለው ሁኔታ የማህበሩ ታፔላ እንዲነሳ ተደርገ፤ ባጃጇም የወረዳ ንብረት ነው በሚል በፖሊስ ተያዘ::

  ንብረቷን ለማስመለስ ብዙ ብትደክም ከሕጋዊ ማህበር እንደገዛችው በመግለፅ ብትከራከርም ሰሚ ሳታገኝ ተቀራለች:: በሁኔታው የተበሳጨችው ይህቺ የባህር ዳር ነዋሪ ይህ እንዲሆን ያደረገው ቀደም ሲል የባሕር ዳር መንገድ ትራንስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት እና አሁን የክልሉ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ የስምሪት ዳይሬክቶሬት ዳይሬከተር የሆኑት አቶ ደመላሽ ስንሻው ናቸው ብላ በማሰቧ በተጠቀሰው ቀን ቢሮአቸው ድረስ በመሄድ በጆግ የያዘችውን አሲድ እንደደፋችባቸው ለፖሊስ ቃሏን በሰጠችበት ሰዓት ገልፃለች::

   ተጠርጣሪዋ ድርጊቱን ፈጽማ ለማምለጥ ብትሞክርም በአካባቢው በነበሩ ሰዎች ትብብር በቁጥጥር ሥር የዋለች ሲሆን ጥቃቱ የተፈጸመባቸው ግለሰብም ወዲያውኑ ወደ ሐኪም ቤት ተወስደው ህክምና እንዲያገኙ ተደርጓል።

    የተደፋባቸው አሲድ ሙሉ ለሙሉ ሰውነታቸው ላይ ስላላረፈ በግለሰቡ ላይ የከፋ ጉዳት እንዳላደረሰ የተገለጸ ሲሆን፤ ነገር ግን አሲዱ በተጎጂው ሁለት እጆች ላይ በማረፉ እጃቸው መጥቆር እና እብጠት፣ ሆዳቸው ላይ የመጥቆር ምልክቶች እንዲሁም በፊታቸው ላይም አልፎ አልፎ የመቃጠል ጉዳት አጋጥሟቸቸዋል::

LEAVE A REPLY