የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ነሐሴ 19 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ነሐሴ 19 ቀን 2011 ዓ.ም

ዶ/ር ዐቢይ ደቡብ ኮሪያ ገብተው ከኢትዮጵያዊያን ጋር እየተወያዮ ነው

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝትደቡብ ኮሪያ ገብተዋል። ዶ/ር ዐቢይ ከኢትዮጵያዊያን ጋር በዛሬው ዕለት በተለያዮ ጉዳዮች ላይ ተነጋግረዋል። በደቡብ ኮርያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የእራት ግብዣ በማዘጋጀት ነው የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አባላትን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር እንዲገናኙ ያደረገው።

የኮሚኒቲ አባላቱ በመደመር እሴቶች ላይ በማተኮር ባሉበት ሆነው አገራቸውን እንዲረዱ ጥሪ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን ከገባችበት ጊዜያዊ ችግር በማውጣት ወደ ቀደመ ክብሯ መመለስ የሁላችንም ሓላፊነት እና የዜግነት ግዴታ መሆኑን አሳስበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለኹለት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት በዛሬው ዕለት ደቡብ ኮሪያ የገቡ ሲሆን በደቡብ ኮሪያ ጉብኝታቸው ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሙን ጄ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮጀክት ይፋ አደረገች

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ምጣኔ ሀብታዊ እድገትን ያስመዘገበች ቢሆንም በተለያዩ ውጫዊና ውስጣዊ ፈተናዎች ሳቢያ ዕድገቱ ላይ የተጋረጡበት አደጋዎች ወደ ኋለ እየጎተቱት መሆኑ ተነገረ። ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የብር የመግዛት አቅም መውረድ፣ የዕዳ ጫና እና የሥራ አጥነት የምጣኔ ሀብቱ ተግዳሮቶች ናቸው።

ለመጪዎቹ ሶስት ዓመታት ተግባራዊ የሚደረገው አገራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ፕሮጀክት እነዚህን ችግሮች በመጋፈጥ የምጣኔ ሀብታዊ ዕድገቱን ቀጣይነት ማረጋገጥ ዋነኛ ግቡ መሆኑን የብሔራዊ ባንክ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ይናገር ደሴ አስታውቀዋል።

አዲሱ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ የተጀመረው ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ቀጣይነት እንዲኖረው ከማድረግ ባሻገር በዘርፉ ልማትን በማሳደግ የሥራ ዕድልን ለመፍጠር እንደሚያግዝም ነው ዶክተሩ ያስረዱት።  የአገሪቱ ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ የተረጋጋ እንዲሆንና የዜጎች ገቢ እንዲጨምርም ፕሮጀክቱ ከፍተኛ ሚና አለው።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ሬይኖር በበኩላቸው ኢትዮጵያ የምታካሂደው ምጣኔ ሀብታዊ ማሻሻያ ፕሮጀክት እንዲሳካ መንግስታቸው የሚያደርገውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንደሚቀጥል እና በሀገራቱ መካከል ያለውን ምጣኔ ሀብታዊ የትብብር ግንኙነት ማጠናከር፣ የልምድ ልውውጥ ማድረግ ለልማትና ብልጽግና ትልቅ ድርሻ እንዳለውም ጭምር ተናግረዋል። የአሜሪካ መንግስት ይፋ ለሆነው የማክሮ ኢኮኖሚ ፕሮጀክት ትግበራ የሚውል የአራት ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚያደርግም አምባሳደሩ ይፋ አድርገዋል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የሥራ ሓላፊዎች ከአሜሪካ ሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ከመጡ፣ በጥናትና ምርምር ሥራ ከተሰማሩ ፕሮፌሰሮች ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆንበዚሁ ወቅት የዩኒቨርሲቲው የልማትና እድገት ምርምር ማዕከል የቡድን መሪ ፕሮፌሰር ሪካርዶ ሁስማን የኢትዮጵያ ምጣኔ ዕድገትን ዘላቂ ማድረግ እንዲቻል ምጣኔ ሀብታዊ መሰረቶችን ማስፋት እንደ አንድ ስልት መወሰድ አለበት የሚል አቋም ወስደዋል።

የካንሰር ሕመምተኞች ጥቁር አንበሳ ሆስፒታልን ልቀቁ ተባሉ

አንጋፋው የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በአሠራር ወጥነት ክፍተት እየታየበት መሆኑ ተነገረ። ህክምና የሚከታተሉ እናበቀጠሮ ወደ ሆስፒታሉ የሚሄዱ የካንሰር ታካሚዎች ደግሞ የበለጠ ለችግሩ ተጋላጭ እንደሆነ ነው የተገለጸው።

በቀጠሮአቸው መሠረት ስልክ ተደውሎላቸው በሆስፒታሉ የተገኙ የካንሰር ህመምተኞች “የካንሰር መድሃኒት ስላለቀ ሆስፒታሉን ልቀቁ ተብለናል” ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡ በብዙ ድካም ከሆስፒታሉ ውጭ መድሃኒት ቢገኝም የ60 ብር ዋጋ ያለው መድሃኒትን በ6 ሺህ ብር እንዲገዙ መጠየቃቸውን እና  አብዛኞቹ ታካሚዎች ይህንን ለማድረግ ደግሞ የአቅም ችግር እንዳለባቸው ምሬት በተሞላበት መልኩ ይናገራሉ።

በጉዳዮ ላይ ምላሽ የሰጡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥቁር አንበሳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የክሊኒካል ሰርቪስ ዳይሬክተር ዶክተር ይርጉ ገብረህይወት፤ ሆስፒታሉ ያልከፈለው የ5 አመታት እዳ 151 ሚሊዮን ብር ስላለበት የመድሃኒት አቅርቦት ችግር ሊከሰት ችሏል ብለዋል።

ሆስፒታሉ በአንድ አመት ብቻ ግማሽ ሚሊየን ታካሚዎችን ያስተናግዳል። ከዚህም ውስጥ 80 በመቶ የሚሆኑት በነጻ ታካሚ በመሆናቸው በየጊዜው የበጀት ችግር እንዲከሰት አድርጓል።

70 የካንሰር መድሃኒት ዓይነቶችን ሆስፒታሉ የሚፈልግ ቢሆንም ለታካሚዎች እያቀረበ የሚገኘው ግን 30 ብቻ መሆኑን ያመላከቱት ዳይሬክተሩ፤ ሆስፒታሉ ያጋጠመው የመድሃኒት እጥረት የካንሰር መድሃኒት ብቻ አይደለም ሲሉ ተደምጠዋል።

የሆስፒታሉ ዕዳ እንዲከፈል ከጤና ሚኒስቴር፣ ከገንዘብ ሚኒስቴርና ከሌሎችም ጋር እየተሰራ ሲሆን ለካንሰር ህክምና አገልግሎት መስተጓጎል ጊዜያዊ መፍትሄ እየተፈለገ ነው።

ታንዛኒያ በተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ውስጥ ያሉ ሰዎችን የሚያስር ግብረ ሀይል አቋቋመች

ታንዛኒያ ውስጥ  በተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ውስጥ ያሉ ሰዎችን አድኖ የሚያሥር ግብረ-ኃይል ተቋቋመ። ይህንን ፀያፍ ድርጊት ለማስቆም የቆረጡት ደግሞ አንድ አገረ ገዢ ናቸው። የዋና ከተማዋ አስተዳዳሪ የሆኑት ፖል ማኮንዳ የግብረ ኃይሉን መቋቋም ይፋ ባደረጉበት ወቅት አሰሳው በቀጣዮ ሳምንት ይጀምራል ብለዋል።

ማሕበራዊ ሚድያውን ዋና መሳሪያ በማድረግ ከሕዝብ በሚመጡ ተጨባጭ መረጃዎች በተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ውስጥ ያሉ ሰዎችን አድኖ ለማሰር  ግብረ ሀይሉ ተዘጋጅቷል ብለዋል።

በአገሪቱ ከተመሳሳይ ፆታ ጋር የፍቅር ግንኙነት መመስረት በሕግ ያስቀጣል።  ይህ ጉዳይ ጥብቅ እየሆነ የመጣው ከፕሬዝደንት ጆን ማጉፉሊ መመረጥ በኋላ ነው። በዚህ ምክንያት የተመሳሳይ ፆታ ጋር ግንኙነት ያላቸውና ፆታቸውን በቀዶ ህክምና የቀየሩ (ትራንስጀንደር) ግለሰቦች መደበቅ ብቸኛ ምርጫቸው ሆኗል።

የከንቲባማጉፉሊ ቀኝ እጅ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ፖል ማኮንዳ «ምንም እንኳ በዚህ ጉዳይ ትችት ሊገጥመን ቢችልም፤ እግዚአብሔር ከሚቆጣ ሕዝብ ቢቆጣ ይሻላል» ብለዋል። ማኮንዳ የተፈላጊዎቹን ስም ስጡኝ ማለታቸውን የዘገበውአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ግብረ ኃይሌ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ማደኑን ይጀምራል በማለትሲሉ ቁርጥ ያለ አቋም መያዛቸውን ይፋ አድርጓል።

«እርቃናችሁን ያላችሁበት ፎቶ ካለ ከተንቀሳቃሽ ስልካችሁ ላይ አጥፉት፤ የብልግና ቪድዮም ካላችሁም ዋ!» በማለት ያሳሰቡት አገረገዢ ወንጀሉን ለሚፈጽሙ ምህረት አይኖረንም ብለዋል። በአገሪቱ የሚገኙ የኤችአይቪ ክሊኒኮች የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት እያስፋፉ በመሆኑ እንዲዘጉ ግፊት እየተደረገ ይገኛ።

LEAVE A REPLY