የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ነሐሴ 20 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ነሐሴ 20 ቀን 2011 ዓ.ም

በመቀሌው ዱለታ አየለ ጫሚሶ እና ትዕግስቱ አወል የሕወሓት ታማኝነታቸውን አሳዮ

“ሕገ መንግሥት እና ሕብረ ብሔራዊ ፌዴራላዊ ሥርዓትን የማዳን አገር አቀፍ መድረክ” በሚል ርዕስ ዛሬ በመቀሌ ሕወሓት አባላቱን እና ደጋፊዎቹን ይዞ ለምክክር መቀመጡ ተሰማ።

ሕገ መንግሥቱ የደም ስሬ ነው በሚለው የሕወሓት ስብሰባ ላይ ለዓመታት በተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት ስም ሲነግዱ የኖሩት ግለሰቦችም በፓርቲዎቻቸው ስም ታድመዋል። ከወያኔ ቀለብ እየተሰፈረላቸው የአምባገነኑን ሥርዓት ለማስቀጠል አስነዋሪ ሥራዎችን ሢሠሩ እንዲኖሩ የሚነገርላቸው ተለጣፊዎች ከተገፋው የህወሀት ቡድን ጎን ሆነው ሕገ መንግሥቱ ፍፁም እንደሆነ ሲመሰሰክሩ ውለዋል።

ዶ/ር ደብረፂዮን በከፈቱትና ሁለት ቀን በሚቆየው ውይይት ላይ ከወያኔ የደሕንነት ቡድን ለታማኝነታቸው ድጎማ ይደረግላቸው እንደነበር የሚያረጋግጥ ሰነድ በለውጡ ማግሥት ይፋ የሆነባቸው አየለ ጫሚሶ የዱለታው ታዳሚ ሆነዋል። በተመሳሳይ አቶ ትዕግስቱ አወልም ጥሪ ተደርጎላቸው መቀሌ ገብተዋል።

ሕወሓት ሕገ መንግሥቱን እና ፌደራላዊ ሥርዓቱን በተመለከተ እወያያለሁ ቢልም ቀኑን ሙሉ ተሳታፊዎቹ በመሰዋዕትነት ያፀደቅነውን ሕገ መንግሥት እንደዘበት አይሻሻልም በማለት ሲፎክሩ መዋላቸው ታውቋል።

የዳኞች የሥራ አፈጻጻም ምዘና ረቂቅ መመሪያ ተዘጋጀ

የፌዴራል ዳኞች የሥራ አፈጻጸም ምዘና ረቂቅ መመሪያ መዘጋጀቱ ተሰማ። የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከዩኤስ ኤድ ፍትህ አክቲቪቲስ በኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ነው ወጥ የሆነውን እና ከዳኝነት መርህዎች ጋር የተጣጣመ የተባለለትን መመሪያ ያዘጋጀው።

የተዘጋጀው መመሪያ የዳኝነት ስርዓቱን ውጤታማነትና ዳኞች ለሙያቸው ያላቸውን ተገዥነት በማሳደግ ረገድ ሚና ከመጫወቱም በላይ ለተገልጋዩ ማህበረሰብ ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል ይጠቁማል፤ ብቃትን በማሳደግ ተገቢ ያልሆነ አሠራርን ለማስቀረት ያግዛልም ተብሏል።

በተጨማሪም ዳኞች በሙያውና በሥራቸው ላይ ያላቸውን ተነሳሽትና እርካታ ለማሳደግ፣ የአመራር አቅም በማሳደግ፤ የተጠያቂነት ሥርዓት እንዲዘረጋ በማድረግ የፍርድ ቤቶችንን የህዝብ አመኔታ ከማሳደግ ባሻገር የዳኞች የሥራ አፈጻጸም መመሪያ አስፈላጊ እንደሆነ ተገልጿ።

በሀዋሳ በሞተር ሳይክሎች ላይ ተጥሎ የነበረው እግድ ተነሳ

በሀዋሳ ከተማ በሞተር ሳይክሎች ላይ ተጥሎ የነበረው ገደብ መነሳቱ ታወቀ። በከተማዋ በባለ ሁለት እግር ሞተር ሳይክሎች ላይ ላልተወሰነ ጊዜ እንዳይንቀሳቀሱ ተጥሎ የነበረው እገዳ መነሳቱ ዛሬ ይፋ ተደርጓል::

የሀዋሳ ከተማ ፖሊስ መምሪያ እና የደቡብ ፖሊስ ከሚሽን ጉዳዮን አስመልክተው የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል። የከተማዋ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር መስፍን ዴቢሶ በሞተር ሳይክሎች ላይ ተጥሎ የነበረው ገደብ መነሳቱን እና ህጋዊ አሽከርካሪዎች እንዲያሸከረክሩ መፈቀዱን ይፋ አድርገዋል።

ከጧቱ ከ12፡00 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12፡00 ሰዓት ድረስ ማሽከርከር እንደሚቻል የተናገሩት ኮማንደር መስፍን፥ ልዩ ፈቃድ ያላቸው አሽከርካሪዎች ከምሽት 12፡00 ሰዓት በኋላም ማሽከርከር እንደሚችሉ እና ቀደም ሲል በከተማዋ ተይዘው የነበሩ ሞተር ሳይክሎች ባለቤቶቹ ህጋዊ ሰነዶቻቸውን በማቅረብ እየተመለሰላቸው መሆኑን አስታውቀዋል።

የደቡብ ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል እና ትራፊክ አደጋ ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮማንደር ታደለ ዋሪዮ በበኩላቸው በሃዋሳ ከተማ አሁን ላይ እየታየ ካለው አንፃራዊ ሰላም አኳያ ኮማንድ ፖስቱ ገምግሞ ውሳኔውን እንዳሳለፈ ገልፀዋል።

ለፋና ራዲዮና ቲቪ ሌላ ኢሕአዴግ በሓላፊነት ተሾመለት

የኢህአዴግ የጀርባ አጥንት ሆኖ የመንግሥት ፕሮፐጋንዳን በማስተጋባት የሚታወቀው “ፋና” አዲስ ሓላፊ ተሹሞለታል። በሕወሓት ብአዴን ሰዎች ለዘመናት እንደልብ ሲሽከረከር እንደቆየ የሚነገርለት ፋና ከምሥረታው ጀምሮ ከኢቲቪም በላይ የሥርዓቱ ታማኝ አገልጋይ እንደነበር የአደባባይ ሚስጢር ነው።

ከለውጡ ማግሥት አንስቶ በፋና ራዲዮ እና ቴሌቪዥን ላይ መጠነኛ የሆነ መሻሻል እና የትክክለኛ ሚዲያ ባሕሪ የታየበት ቢመስልም ኢህአዴግ ይህንን ሚዲያ ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ ከማድረግ ይልቅ የፓርቲው ልሳን ሆኖ እንዲቀጥል ፍላጎት ያለው መሆኑን የሚታዮ እንቅስቃሴዎች ይጠቁማሉ።

ይህን መሰሉ ክፍተት በሚስተዋልበት በአሁኑ ወቅተ አቶ በቀለ ሙለታ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስፈፃሚ ሆነው ተሹመዋል። አቶ በቀለ የእክስዮን ማህበሩ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሆነው የተሾሙት በድርጅቱ የሥራ አመራር ቦርድ ነው።

ቀደም ሲል የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስፈፃሚ የነበሩት አቶ ወልዱ ይመሰል፤ ከዚህ በፊት ጀምረውት የነበረውን የሶስተኛ ድግሪ ትምህርታቸውን ለመቀጠል የስራ አመራር ቦርዱን በጠየቁት መሠረት ፍቃድ በማግኘታቸው በቦታቸው አዲስ ሰው መሾሙ ግድ ሆኗል።

አቶ በቀለ ከሪፖርተርነት እስከ ዋና አዘጋጅነት በተለያዩ ሚዲያዎች ያገለገሉ ሲሆን፥ በጋዜጠኝነትና በአመራር የካበተ ልምድ ያላቸው፤  በትምህርት ረገድም የመጀመሪያ ድግሪ በጋዜጠኝነትና ከሙዩኒኬሽን፣ ሁለተኛ ድግሪያቸውን በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ተቀብለዋል። ተሰሰናባቹ አቶ ወልዱ ይመሰል ከጋዜጠኝነት እስከ ዋና ሥራ አስፈፃሚነት ከምስረታው ጀምሮ ያገለገሉ ናቸው።

አዲሱ የፋና ብሮድካስት ሥራ አስኪያጅ ላለፉት አምስት ዓመታት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሠርተዋል።

ኹለቱም ሓላፊዎች የኢህአዴግ አባል መሆናቸውን የጠቆሙት ምንጮቻችን አቶ ወልዱ ይመስል ከመንበረ ሥልጣኑ የተገፋው የሕወሓቱ ኢህአዴግ ታማኝ ነበሩ ይላሉ። ያልተረጋገጠ ሥልጣን በነበራቸው በአቶ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ አመራር ዘመን የኦህዴድ አባል በመሆናቸው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሓላፊ ሆነው የተሾሙት አቶ በቀለ በእነ በረከት ስምኦን ቅኝት ውስጥ ሆነው ተቋሙን ከፖለቲካ ተፅዕኖ ባልራቀ መልኩ ሲመሩ ቆይተዋል የሚሉት ታማኝ ምንጮቻችን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ማዕከልን ኦሮሚያ ለማድረግ እየሠራ እንደሚገኝ የሚነገርለት ኦዴፓ ፋናን ዋነኛ መገልገያው ለማድረግ ይረዳው ዘንድ ግለሰቡን በቦታው ላይ ሾሟቸዋል ተብሏል።

LEAVE A REPLY