የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ጳጉሜን 5 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ጳጉሜን 5 ቀን 2011 ዓ.ም

ቀሲስ በላይ ማሸበራቸውን ቀጥለዋል፤ አዲሱን ዓመትም በማስመልከትም መልዕክት አሰተላለፉ

ከጀርባቸው ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ጽንፈኛ የኦሮሞ ብሔርተኞች እንዳሉ የሚነገርላቸው ቀሲስ በላይ የቅዱስ ሲኖዶስን ውግዘት እና ማስጠንቀቂያ ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት የአዲስ ዓመት መልዕክት አስተላልፈዋል::

እያራመዱት ካለው ርካሽና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የመበታተን ተግባር ለመታቀብ ያልመረጡት ፖለቲከኛ በኦሮሚያ ቤተ ክህነት አደራጅ ኮሚቴ ስም እንኳን አደረሳችሁ የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል:: ይህንን ድፍረት የተሞላበት ምዕመናን የመናቅ ተግባራቸው ዕውን እንዲሆን ደግሞ ዋነኛ የጥፋት አጋራቸው የሆነው የጃዋር መሐመድ ኦኤም ኤን ተባብሯቸዋል::

በቤተክርስቲያን ደረጃ የመጨረሻው ወሳኝ አካል የሆነውን ቅዱስ ሲኖዶስን ያላከበሩትና ከቤተክህነት በሙስና ተባረው በኦሮሚያ ዕንባ ጠባቂ መቤት ውስጥ በሓላፊነት የተሾሙት የብሔር ፖለቲካ አቀንቃኞች ተላላኪ ቀሲስ በላይ በልበ ሙሉነት ሚዲያ ጠርተው የሠጡት መግለጫ መላው ኢትዮጵያውያን አማኞችን አስቆጥቷል:: ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ቤተ መንግሥት ድረስ በመሄድ በጉዳዮ ላይ ለመከሩት ጳጳሳት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድርጊቱን ለማስቆም የገቡትን ቃል አለመጠበቁም ሕዝብ በመንግሥት ላይ ጥርጣሬን እንዲይዝ አድርጓል።

በማክስ 8 የሞቱ ሰዎችን ማንነት የመለየት ሥራ ከ6 ወር በኋላ ተጠናቀቀ

ከኢትዮጵያ ወደ ኬኒያ ሲያመራ በተከሰከሰው ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን አደጋ ሕይወታቸው ያለፈው ሰዎችን ማንነት የመለየት ሥራ ሙሉ ለሙሉ መጠናቀቁ ተገለጸ::

ከ6 ወር በፊት ከኢትዮጵያ ወደ ኬኒያ ሲያመራ የነበረውና በኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር ኢቲ 302 የሆነው ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ተከስክሶ በውስጡ የነበሩ መንገደኞች በሙሉ ሕይወታቸው ማለፉ አይዘነጋም::

አደጋው ከተከሰተ በኋላ የጉዳቱን አጠቃላይ ሁኔታ ለማጥናት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የቅርብ ክትትል የሚመራ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ሥራ ገብቶ ነበር:: ይህ ኮሚቴ አራት ንዑስ ኮሚቴዎች አሉት:: ከዚህ ውስጥ በፌደራል ፖሊስ የሚመራው እና 8 መስሪያ ቤቶችን ያጣመረው ፣ የጉዳቱ ሰለባ የሆኑ ሰዎችን ማንነት ለማጣራት የተቋቋመው ንዑስ ኮሚቴ ቀዳሚው ነው፡፡

ንዑስ ኮሚቴ ዛሬ በሰጠው መግለጫ አደጋው ከደረሰበት ስፍራ፥ የሰው ቅሪተ አካል፣ ቦርሳዎች፣ የመንገደኞች ማስረጃዎች እና ሌሎች ቁሳቁሶች መሰብሰባቸውን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር እንደሻው ጣሰው ተናግረዋል።

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በተሰራ ጊዜያዊ የላቦራቶሪ ማዕከል መረጃዎቹን በጥንቃቄ በማስቀመጥም በተለያየ ምርመራ ማንነታቸውን የመለየቱ ስራ መሰራቱን እና በዚህም በዘረመል፣ በጣት እና መዳፍ አሻራ እንዲሁም በጥርስ ኦዶንቶሎጂ በመጠቀም ማንነታቸውን መለየቱን አስታውቀዋል::

የሟች ቤተሰቦችም በቀጥታ ኢትዮጵያ በመምጣት እና ካሉበት ሀገር የማመሳከሪያ የዘረመል ናሙና በመሰብሰብ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ማንነታቸውን ለመለየት ተችሏልም ነው ያሉት፡፡ በተለይም በዘረመል እና በጣት እና መዳፍ አሻራ በተሰበሰቡ 8 ሺህ 185 ናሙናዎች የተደረገው ምርመራ ውጤታማ ነበር ተብሏል፡፡

ከእንግሊዝ ሃገር ተወዳድሮ ከመጣው ሴልማክ ከተባለ የላቦራቶሪ ተቋም፣ ከኢንተር ፖል እንዲሁም ከፌደራል ፖሊስ ጋር ምርመራው በቅንጅት ተካሂዷል:: በፌደራል ፖሊስ የሚመራው አይ ዲ ቦርድ ኮሚቴ የቀረበውን የምርመራ ሪፖርት ውይይት ካደረገበት በኋላ ተስማምቶበት ተቀብሎታል።

መቀሌ ያሉትን ጀቶች ማስመለስ ያልቻለው አየር ኃይል የማዕረግ ዕድገቶችን ሰጠ

በትግራይ ክልል መቀሌ የሚገኙ የጦር አውሮፕላኖቹን ከአፈነገጠው ሕወሓት መዳፍ መንጠቅ ያልቻለውየኢትዮጵያ አየር ኃይል በ2011 ዓ.ም በጀት ዓመት ከፍተኛ አፈፃፀም አሳይተዋል ያላቸውን  አባላቱን ዕውቅና ሰጥቷቸዋል::

ዛሬበተካሄደው ስነ ስርዓት ላይም በ2011 በጀት ዓመት ከፍተኛ የስራ አፈጻጸም ካሳዩ የስራ ክፍሎች እና በተሰጣቸው የስራ ምድብ የሚያስመሰግን ስራ ከሰሩ የዕውቅናው ተቋደሾች በሻገር ፤ በስራ ገበታቸው ላይ ውጤታማ ሆነዋል ለተባሉ የአየር ኃይል አባላትም የማዕረግ እድገት ተሰጥቷል::

የማዕረግ እድገት የተሰጣቸው የኢፌዴሪ አየር ሀይል አባላት 735 ሲሆኑ ፣ ከዚህም ውስጥ 10ሩ የከፍተኛ መኮንንነት የማዕረግ እድገት አግኝተዋል። በዕውቅና አሰጣጥ ስነ ስርዓቱ ላይ በኢፌዴሪ አየር ሀይል ለረጅም ዓመት ላገለገሉ አባላት የክብር ሽኝት ተደርጓል። በጡረታ የተሰናበቱት 56 የቀድሞ የኢፌዴሪ አየር ሀይል አባላት የእውቅና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል::

አየር ኃይል በዚን ያህል ሰፊ መጠን ለአባላቱ የማዕረግ ሹመት መስጠቱ ከሞላ ጎደል ተቋሙ በኢንተርናሽናል አየር ኃይል መንገዶች ለመጓዝ ብዙ የሚቀረው መሆኑን የሚተቹም አልጠፉም::

በተለይ መቀሌ በሚገኘው አየር ኃይል ግቢ ውስጥ ወሳኝ የሆኑ የጦር ጀቶቾ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅተም ሆነ ከዛን በኋላ በነበሩት ዓመታት እንዲቀመጡ መደረጉንና ለውጡን ተከትሎ ያፈነገጠው ሕወሓት ለመመለስ ፍቃደኛ አለመሆኑ ዛሬ በማዕረግ ዕድገት ሲንበሻበሽ የዋለውን የኢፌዲሪ አየር ኃይል ጥርስ የሌለው አንበሳ ሆኖ ታይቷል።

የመስከረም 4ቱ ሰልፍ ከኦሮሚያ ቤተክህነት ጥያቄ ጋር አይገናኝም ተባለ

ስለ ቤተክርስቲያን ዝም አንልም በሚል መስከረም4 ቀን የተጠራው ሰልፍ ከኦሮሚያ ቤተክህነት የማቋቋም ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው ማኅበረ ቅዱሳንና አጋሮቹ ገለጹ::

የመስከረም 4 ሕዝባዊ ትዕይንት በቤተክርስቲያን በይዞታዎቿ፣ በካህናቶቿ እና በምዕመናኖቿ ላይ በተደጋጋሚ የደረሰባትና የሚደርስባት ጥቃት እንዲቆም ለማሳሰብ ብቻ ነው ያለው አስተባባሪ ኮሚቴው ሠሞኑን በማህበራዊ ሚዲያዎች እየተራገበ ያለው የኦሮሚያ ቤተክህነት  ጥያቄ ጋር የተያያዘ እንዳልሆነ  አስታውቋል::

የሰ/ት/ቤቶች አንድነት፤ የመንፈሳዊ ኰሌጅ ተማሪዎችና ምሩቃን፤ በሰ/ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን፤ የወጣቶችና ጎልማሶች ማኅበራት ኅብረት፤ የሠለስቱ ምዕት ማኅበራት ኅብረት፤ የአእላፋት ድምፅ የካህናትና ምእመናን ተናሥኦት ኅብረት፤ የጽዋ ማኅበራት ሙሴና ደርገ ሙሴዎች የሰልፉ አሰተባባሪዎች፤ አጠቃላይ የሰልፉን ሂደት በተመለከተ ዛሬ በኅብረት ጋዜጣዊ መግለጫ የሚሰጡ ሲሆን፤ ከዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ ወጪ ሰልፉን በተመለከተ ከሌላ ወገን የሚሰጥ ማናቸውም አይነት መግለጫ አግባብነት አይኖረውም ብለዋል:: የሰልፉን ዋነኛ ዓላማ ተረድቶ ምዕመኑ በታሰበው መንገድ እንዲጓዝ ጥሪ አቅርበዋል።

የሚያርርቁ ሀሳቦችን በአዲሱ ዓመት በውይይት ሊፈቱ ይገባል ተባለ

አዲሱ ዓመት የሚያራርቁ ሀሳቦችን በውይይት ለመፍታት ሀገራዊ የዕርቅ ዕሴቶችን በመጠቀም ለህዝቦች ሰላምና አንድነት ለመስራት መዘጋጀት ያስፈልጋል ተባለ::

የኢትዮጵያ እና የኢጋድ አባል ሀገራት በንግድ የተሰማሩ ሴቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ወይዘሮ እንግዳዬ እሸቴ፥ ከሚያራርቁ ሀሳቦች ይልቅ በሚያቀራርቡን ዕሴቶች ላይ መስራትን በመሸጋገሪያው ጳጉሜን ወር ላይ ቆመን ማሰብ እንደሚያስፈልግና በየማህበረሰቡ መሰረት የሆነው ቤተሰብ በልጆቹ ላይ መስራት ይኖርበታልም ሲሉ መክረዋል::

የኢትዮጵያ ሙዚቃ ዘርፎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ዳዊት ይፍሩ የኋልዮሽ ማረም የማይቻሉ ክስተቶች በመጭው አዲስ አመት ኑረት ውስጥ የሚከተቡ እንደማይሆኑ እምነታቸውን የገለጹ ፤ ፖለቲከኛው አቶ ገብሩ አስራት ደግሞ መንግስት ህግና ስርዓትን ማስጠበቅ የአዲሱ አመት የመንግስት ቀዳሚው የቤት ስራ መሆን አለበት ብለዋል::

ሌላኛው ፖለቲከኛ አቶ መርሻ ዮሴፍ በበኩላቸው የሀገሪቱን ሰላም ያናጋውና መረጋጋትን ህዝቦች እንዲናፍቁ ያደረገው 2011፥ ለዘርፈ ብዙ ክስረትና የሀገሪቱን አንድነት በመፈታተን በጥላቻ የተደፈቁ ፖለቲከኞችም እርስ በእርስ ህዝቦችን ለማጋጨት የተንቀሳቀሱበት እንደነበር ያስረዱ ሲሆን፣ ገጣሚ ኤፍሬም ስዩም በበኩሉ በመጭው አመት አለመግባባት እንኳን ድንገት ቢከሰት በኢትዮጵያዊ የእርቅ ዕሴቶች መፈታትን በመለማመድ ልንሻገርው ጫፍ ላይ በደረስንበት አመት የተከሰቱ ጥፋቶች ሊታረሙ ይገባል ብሏል።

LEAVE A REPLY