“የዶ/ር አብይ አስተዳደር ዝምታን መምረጡ አሳዝኖናል” || በታምሩ ገዳ

“የዶ/ር አብይ አስተዳደር ዝምታን መምረጡ አሳዝኖናል” || በታምሩ ገዳ

ለትላንትናዋ ሆነ ለዛሬው እንዲሁም ለመጻኢዋ ኢትዮጵያ ማንነት እና ምንነት መንገድ ከጠረጉ ተቋማት መካከል በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀሰው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን (ኢ/ኦ/ተ/ቤ/ን በቅርቡ በይፋ ላቀረበቻቸው አቤቱታዎች ከመንግስት በኩል ተገቢውን እና አፋጣኝ ምላሽ መነፈጓ እንዳሳዘናቸው አንድ የቤተክርስቱያኒቱ ከፍተኛ ሀላፊ ተናገሩ።

በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በአየአመቱ ከቤተክርስቲያን ቅጥር ውጪ ከሚከበሩ ታላላቅ ክብር በዓላት መካከል አንዱ የሆነው የመስቀል ደመራ ክብረ በአል በማስመልከት የቤተክርስቲያኒቱ አስተባባሩ የሆኑት አክሊል ዳምጠው ለፈረንሳይ የዜና አገልግሎት (ኤኤፍፒ) በሰጡት አስተያየት”

የጠ/ሚ/ር አብይ አህመድ አስተዳደር በቤተክርስቲያኒቱ፣ በካህናቶቿ እና በምእመናኖቿ ላይ የሚደርሱት ጥቃቶችን እንዲያስቆም፣ የጥፋት ሀይሎች እና ወንጀለኞችም ተይዘው ተገቢውን ምድራዊ ፍርድ እንዲገኙ ቢጠየቅም ” የዶ/ር አብይ አስተዳደር ለጥያቄዎቻችን ተገቢውን እና አፋጣኝ ምላሽ ከመስጠት ዝምታን መምረጡ በእጅጉ አሳዝኖናል፣መንግስት በቤተክርድቲያኒቱ ጥያቄዎች እና ስጋቶች ዙሪያ ለምን ዝምታን መረጠ?”ሲሊ አንደ ዜጋ አንደ አማኝም የተሰማቸውን ቅሬታ ገልጸዋል፣ ጥያቄም አቅርበዋል።

እንደ ኤኤፍፒ ዘገባ በአሁኑ ወቅት በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ን አባቶች እና በጠ/ሚ/ር አብይ አሕመድ አስተዳደር መካከል የሚታየው የተካረረ ውጥረት አፋጣኝ እልባት ካልተሰጠው አገሪቱ በአሁኑ ወቅት ሰንጓት በሚገኘው ቁርቋሶ እና በቀጣዩ አመት ታካሄደዋለች ተብሎ በሚጠበቀው አገር አቀፍ ምርጫ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊያመጣ ይችላል ሲል ስጋቱን ከወዲሁ ገልጿል።

ዘንድሮ የሚከበረው የመስቀል ክብረ በዓል ከቀደሙት ለየት የሚያደርገው በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች የሚገኙ የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች እና ምእመናኖች ባለፉት ሁለት ሳምንታት “ፍትህ ለኢ/ኦ/ተ/ቤ/ን” በማለት እጅግ ታላቅ እና ሰላማዊ የሆነ የተቃውሞ ሰልፍ ባደረጉበት ማግስት ሲሆን የመስቀል ክብረ በአልን በተመለከተ የፌደራል ፖሊስ ሐሙስ እለት ባወጣው መግለጫው “የተለያዩ ጽሑፎችን፣ ምስሎችን እና ህጋዊ ያልሆኑ ሰንደቃላማዎችን ይዞ መገኘት ክልክል ነው” ሲል አስጠንቅቋል።

እንደ አቶ አክሊል እምነት ቤተክርስቲያኒቱ ባለፉት ሁለት አመታት ውስጥ በትንሹ ከሀያ አምሰት የሚበልጡ ህንጻ ቤተክርስቲያናት ተቃጥለውባታል ብለዋል። ብዛት ያላቸው ካህናት እና ምእመናኖቿም መገደላቸው፣ ለአካለስንኩልነት መዳረጋቸው፣ በእምነታቸው ብቻ ከገዛ አገራቸው መፈናቀላቸው።

የተለያዩ የመገናኛ ብዙሀናት በስፋት ዘግበውታል። እርምጃውን የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች በበኩላቸው ይዘቱ ፣ቦታው እና ጊዜው ይለያይ እንጂ የጸረ ኦርቶዶክስ እምነት ነጸብራቅ ነው ይሉታል።

በአሜሪካ፣ የፍሎሪዳ ዩንቨርስቲ መምህር እና በኢትዮጵያ በሀይማኖት ጉዳዮች ዙሪያ አጥኚ የሆኑት ቴሪጂ ኦስቲቦ ለዜና አገልግሎቱ በሰጡት አስተያየት” ብዙውን ጊዜ በተፈጥሮ ሀብት ይገባኛል፣ በጎሳ እና በተመሳሳይ ሁኔታዎች የሚፈጠሩ አለመግባባቶች እና ግጭቶች ሀይማኖታዊ ተቋማትንም ኢላማ ያደርጋሉ ነገሮችም ይወሳሰባሉ”ብለዋል።

ቤተክርስቲያኒቱ የሚደርሱባት በርካታ የውጫዊ አካላት ጥቃቶችን የመጋፈጧ ያህል ከቤተክርስቲያኒቱ ጉያ የወጡ እና እራሳቸውን የኦሮሚያ ኦርቶዶክስ ቤ/ን አስተባባሪዎች ብለው የሰየሙ ወገኖች በቅርቡ ያቀረቧቸው ጥያቄዎች እና ለጥያቄያቸው ምላሽ ያስቀመጡት የጊዜ ገደብ የሀይማኖት አባቶችን በእጅጉ ያሳዘነ ሲሆን ሁኔታውን ቅድስት ቤተክርስቲያኒቱ በየትኛውም ዘመን በመከራ ላይ መሆኗን ያመላክታል የሚሉ ወገኖች ብዙ ናቸው።

ጠ/ሚ/ር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን በመጡ ማግስት ለሁለት አስርት አመታት በላይ ተራርቀው የነበሩት ሁለቱ ሲኖዶሶችን ወደ አንድነት እንዲመጡ ላበረከቱት ጥረት ከሀይማኖት አባቶች እና ከምእመናኖች ዘንድ ከፍተኛ ውዳሴ የተቸራቸው መሆኑ ባይዘነጋም በአሁኑ ወቅት በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ያነጣጠረው ዘርፈ ብዙ ችግሮች ግን ብዙዎችን ከስጋት ውስጥ እንደከተታቸው ዘገባዎች ይገልጻሉ።

LEAVE A REPLY