የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || መስከረም 19ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || መስከረም 19ቀን 2011 ዓ.ም

የአማራ ክልል ልዮ ኃይል በሽፍታ ፍለጋ ስም የቅማንት ሕዝብን እየገደለ ነው ተባለ

በቅማንት አካባቢ ዳግም ግጭት ሊቀሳቀስ የቻለው ጳጉሜ 3 2011 ዓ.ም የአማራ ልዮ ኃይል የማህበረሰቡን የአስተዳደር ይከበርልኝ ኮሚቴ አባላትን ለመውሰድ በመሞከሩ እንደሆነ የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ:: የአማራ ክልል የሰላምና ሕዝብ ደህንነት ቢሮ ሓላፊ አቶ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው የክልሉ ልዩ ኃይል ወደ ስፍራው የተጓዘው ሕግ ለማስከበር እንደሆነ ይናገራሉ::

ከጳጉሜ 3 ጀምሮ የክልሉ የፀጥታ ኃይል ቅማንት ወደሚኖርበት በማንቀሳቀስና ወደ ቀበሌዎች ውስጥ በመግባት፣ ሰላማዊ መንደርን ከብቦ ጥቃት  እንዳደረሰናየፀጥታ ኃይሉ ለተኩሱ ምክንያት የሰጠው “በአካባቢው ሽፍታ አለ” የሚል   ሰበብ መሆኑን ነዋሪዎች አስረድተዋል::

መምህር መካሻው በስፍራው ሽፍታ እንደሌለና፣ ሰላማዊ ሰዎች የሚኖሩበት አካባቢ በልዩ ኃይሉ በጥይት መደብደቡን ይናገራሉ። “በሕዝብ ይሁንታ የቅማንት የማንነትና የአስተዳደር ጥያቄን ለማስተባበር የተቋቋመው ኮሚቴ አባላትን ለመያዝ ሆን ብሎ የተደረገ ነው” የሚሉት መምህር መካሻው ሕዝቡ ኮሚቴዎቻችንን አትንኩ እያለ ስለሆነ “ሽፍታ ልንይዝ ነው” በሚል ሰበብ መጥተዋል ሲሉ ያስረዳሉ።

አቶ ከፍአለ ማሞ በበኩላቸው በ2012 ዓ.ም ከመስከረም 10 ጀምሮ በአካባቢው የልዩ ኃይል ጥቃት እያደረሰ ነው ሲሉ ይከስሳሉ። መስከረም 11 ወደ መንደር ገብተው ወጣቶች ላይ ተኩስ መክፈታቸውን ከዚያም ገበሬውም ላይ መተኮስ መጀመሩን ያስረዳሉ።

በአሁኑ ሰዓት ወደ ስፍራው ከፍተኛ ጦር እየተንቀሳቀሰ ነው ያሉት የአካባቢው ነዋሪ ፤ መምህር መካሻው መስከረም 11 የልዩ ኃይል አባላት በድጋሚ መጥተው መንደሩን ማሰሳቸውን፣ የደረሰውን ሰብልም ሲያጠፉ ውለዋል በማለት ምሬታቸውን ለቢቢሲ አሰምተዋል:: የፀጥታ ኃይሉ በእግሩ የደረሰውን ሰብል ሲረመርም፣ ገበሬዎች ተኩስ ጀመሩ ያሉት መምህር “በጥቃቱ ምክንያት ንብረት ወድሟል፣ ሰዎች ከቀያቸው ከአካባቢያቸው ተፈናቅለዋል” ሲሉም ዕውነታውን በግልፅ አስቀምጧል::

ከመስከረም 16 ጀምሮ ባሉ ተከታታይ ቀናት ጥቃት እየደረሰባቸው እንዳለ የተናገሩት ግለሰቡ በዚህም የተነሳ አንድ ሰው ጨንቾ አካባቢ ሕይወቱን አጥቷል:: በተመሳሳይ ሁኔታ አይከል ከተማ አካባቢ የሞቱ ሰዎች መኖራቸውን የተናገሩት ግለሰብ በዋና ከተማው ሰው መገደሉን በመግለፅ በቁጥር በርከት ያሉ ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸውንና መቁሰላቸውን ይፋ አድርገዋል::

አቶ አገኘሁ ተሻገር የአማራ ክልል የሰላምና ሕዝብ ደህንነት ቢሮ ኃላፊ፣ የቅማንት የማንነትና የአስተዳደር ጥያቄ በአግባቡ እንዲፈታ ክልሉ ውሳኔዎችን መወሰኑን በማስታወስ “የአማራ ክልል ውስጥ የተረጋጋ ሁኔታ እንዳይፈጠር የሚፈልጉ ኃይሎች” ግን እንዲህ ዓይነት ያለመረጋጋት ግጭቶችን እየቀሰቀሱ ነው ብለዋል::

ሁከት ፈጣሪ ናቸው ያሏቸውን ኃይሎች ማንነት በስም ባይጠቅሱም ፤ የግጭቱ ዓላማ ነው ያሉትን ሲያስረዱም”በአካባቢው አለመረጋጋት እንዲኖር፣ ወደ መተማ የሚሄደውን መንገድ መዝጋት፣ በዚህም የተነሳ የአማራ አርሶ አደርና ባለ ሀብት ምርቱን እንዳይሰበስብ ሆን ተብሎ፣ ታቅዶ እየተሰራ ያለ ሥራ ነው” በማለት ያብራራሉ::

በስፍራው በታጣቂዎች በደረሰ ጥቃት “ሰላማዊ ዜጎች በመኪና ሲንቀሳቀሱ መኪናውን አስቁመው በማንነታቸው ብቻ ተገድለዋል፤ ከዚህ በተጨማሪም የሚኒባስ ሾፌር ተገድሏል፣”  ያሉት ሓላፊ የነዳጅ ቦቴ ሾፌሮች መታገታቸውንና ቦቴውም ተቃጥሏል ብለዋል::?

ሰሞኑን የተቀሰቀሰው የቅማንት ችግር የፀጥታ አካላት አንድ በወንጀል የሚጠረጠር ግለሰብ ይዘው፣ ከአንድ ቀበሌ ወደ ሌላቀበሌ ሲንቀሳቀሱ ተኩስ በመከፈቱ መሆኑን የሚያስረዱት የክልሉ የሰላምና ሕዝብ ደህንነት ቢሮ ሓላፊ በዚህም የተነሳ አንድ የፖሊስ አባል ሕይወቱን ማጣቱን ገልጸዋል::

በቀጣይ የመከላከያና የልዩ ኃይል አባላት በጭልጋ ወረዳ ጮንጮቅ ቀበሌ ለሚገኝ የልዩ ኃይል አባላት ቀለብ አድርሰው ሲመጡ ተኩስ ተከፍቶባቸዋል ያሉት እኚህ አመራር ፤ የፀጥታ አካላት ወደ ማደሪያ ካምፓቸው ሲገቡ ከበባ ስለተፈጸመባቸው በወቅቱ “ከደረሰባቸው ውርጅብኝ” ራሳቸውን መከላከላቸውን ይናገራሉ። ግጭት ውስጥ ተኩስ ሲከፈት ሰው መሞቱ አይቀርምና ይህንን ይዞ “ጭፍጨፋ እየተፈፀመብን ነው ማለት ሐሰት ነው” በማለት በአማራ ክልል ልዮ ኃይል ላይ የቀረበውን ክስ ያጣጥላሉ::

ከታጣቂ ኃይሎች፣ ከፀጥታ አካላት የሞቱና የቆሰሉ  መኖራቸውን ያልደበቁት ኃላፊ ሕግ ለማስከበር ተንቀሳቅሰናል፤ ሕግ ማስከበርም ግዴታችን ነው ሲሉ እየወሰዱት ያለውን እርምጃ ሕጋዊነት ገልጸዋል::

ልዩ ኃይልና መከላከያ አይከል ከተማ ውስጥ በአሁን ሰዓትመኖሩን በመጥቀስ “አንደኛው ጥያቄ ልዩ ኃይል ከአካባቢው ይውጣ የሚል ነው፤ ደግሜ እናገረዋለሁ ልዩ ኃይል ከአካባቢው አይወጣም። ሕግ ለማስከበር እንቀሳቀሳል” በማለት ለቢቢሲ የተናገሩት የክልሉ ፀጥታ ኃላፊ በአጭር ጊዜ ውስጥ መንገዱን ለማስከፈት እየሰራን ነው ብለዋል::

የኦነግ አቀባበል ላይ ችግር ፈጥራችኋል የተባሉ የአ/አ ወጣቶች ከ1 ዓመት በኋላ ከስ ተመሰረተባቸው

ኦነግ (የኦሮሞ ነፃነት ግንባር) መስከረም 4 2011 ዓ.ም አዲስ አበባ ሲገባ ግርግር አስነስታችኋል በሚል የታሰሩ የአዲስ አበባ ወጣቶች ከአንድ ዓመት ዕስር በኋላ መደበኛ ክስ ተመሰረተባቸው::

ዐቃቤ ሕግ በመሠረተው ክስ “የጦር መሣሪያ ይዞ በማመፅ ወይም የእርስ በርስ ጦርነት በማስነሳት በመንግሥት ላይ የሚደረግ ወንጀል” የሚል ሲሆን ክስ ከተመሰረተባቸው ስምንት ተጠርጣሪዎች መካከል ሁለቱ በአንድ ሰው ነፍስ ማጥፋት ሲጠየቁ ሌሎቹ ከዚያ በቀለሉ ወንጀሎች ተጠያቂ ሆነዋል::

ተከሳሾቹ ከውጭ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ ለሚገቡ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አመራርና አባላት አቀባበል ለማድረግ ከኦሮሚያ ክልል የተለያዮ አካባቢዎች መስከረም 4 ቀን 2011 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ አናስገባም ፣ የኦነግንም አርማ አዲስ አበባ ውስጥ አናሰቅልም ፣ የአርማውንም ቀለም ምልክት አናስቀባም” ብለዋል የሚል ክስ ነው አንድ ዓመት በዕስር የቆዩት የአዲስ አበባ ልጆች ላይ የተመሰረተው::

ፍፁም አስቂኝ የሆነው የፖሊስ እና የዐቃቤ ሕግ የኦነግ ተቆርቋሪነት የታየበት ይህ ክስ በርካታ ኢትዮጵያውያንን እያነጋገረ ከመሆኑ ባሻገር፣ በሠላም ዕጦት እና በኹከት ሀገሪቱን እየናጣት ላለው ጽንፈኛ ድርጅት መንግሥት ተከራካሪ መሆኑ ሥርዓቱን ጥርጣሬ ላይ ጥሎታል::

በኦነግ የአቀባበል ዝግጅት ላይ በግልጽ እንደታየው ከተማዋን አስፋልትና ግድግዳውን ጭምር ቀለም ከመለቅለቅ ባሻገር መኪኖችና ንብረቶችን ሲያወድሙ የታዮት የኦነግ ደጋፊዎችና ቄሮ እንጂ የአዲስ አበባ ወጣት አልነበረም:: ይህንን የጋጥ ወጥነት ተግባር በሰላማዊ መንገድ ለማስቆም የሞከሩ የመዲናዋን ነዋሪዎች ማገዝ የነበረባቸው የአዲስ አበባ ፖሊስና የፌደራል ፖሊስ አባላት ድጋፋቸውን ለኹከተኞቹ በማድረግ ወጣቱን ሲደበድቡና ሲያስሩ መክረማቸው አይዘነጋም::

በዚያኑ ዕለት ምሽት በአሸዋ ሜዳ አካባቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን የኦነግ ደጋፊዎች ዘግናኝ ጥቃት ሲያደርሱባቸው፣ ሚስት በባሏ ፊት በጎረምሶች ስትደፈር ፣አባት በልጆቹ ፊት ሲታረድ  መንግሥት በዘመቻ ጠራርጎ ለዕስር የዳረገው የአዲስ አበባን ወጣት ነበር:: በኦነግ አቀባበል ግፍ የፈጸመው ቄሮ ሳይወቀስና ሳይከሰስ ያለማስረጃ ለአንድ ዓመት በዕስር እንዲቆዮ የተደረጉት የአዲስ አበባ ልጆች አሁን ላይ ለሁከቱ መነሻ ናቸው በሚል መከሰሳቸው ስርዓቱ አምባገነናዊ መሆኑን ያሳያል የሚሉ አስተያየቶች ከተለያየ አቅጣጫ እየተሰሙ ነው::

በአሜሪካ የአየር ጥቃት ሶማሊያን ገበሬዎች በስህተት መገደላቸውን አምንስቲ ኢንተርናሽናል ገለጸ

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አምንስቲ ኢንተርናሽናል መጋቢት ወር ላይ አሜሪካ ባደረገችው የአየር ጥቃት የተገደሉት የአልሻባብ ታጣቂዎች ሳይሆኑ አርሶ አደሮች መሆናቸውን አስታወቀ::

የአሜሪካ ጦር አፍሪካ እዝ (አፍሪኮም) በጊዜውታጣቂዎችን መግደሉን ቢገልፅም በተደረገው ማጣራት በወቅቱ መኪናው ውስጥ ሲጓዙ የነበሩት ንፁኃን ዜጎች መሆናቸው ተረጋግጧል::

በአየር ጥቃቱ የተገደሉት ሦስቱ ግለሰቦች አርሶ አደሮችና ከአልሻባብም ጋር ይሁን ከየትኛውም ታጣቂ ቡድን ጋር ግንኙነት የነበራቸው አለመኖሩን አሜሪካ ለማጣራት ተስኗታል ሲል የተቸው አምንስቲ ኢንተርናሽናል ፤ ሦስቱ አርሶ አደሮች የግብርና ተግባራቸውን አከናነው ወደቤታቸው ሲመለሱ መኪናቸው ላይ ጥቃት እንደደረሰባቸው ይፋ አድርጓል::

የሟቾቹ የሥራ ባልደረቦችና ቤተሰቦችን ጨምሮ አስራ አንድ ሰዎች ቃለ መጠይቅ ተደርጎላቸው ሁሉም ግለሰቦቹ ከአልሻባብ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌላቸው መስክረዋል:: “የአሜሪካ ጦር የአፍሪካ ዕዝ በጥቃቱ ማንን ኢላማ እንደሚያደርግ ሳያውቅ በደመ ነፍስ እየተራመደ ነው፤ ግለሰቦችንም በመግደል እንዲሁም ሚስጥራዊ ጦርነት በሶማሊያ ላይ በማካሄድ ናቸው” በማለት በሶማሊያ የአምነስቲ ተመራማሪ የሆነው አብዱላሂ ሃሰን ይናገራል::

በአየር ጥቃቱ የተገደሉት ሦስት አሸባሪዎች እንደሆኑ፣የንፁኃን ዜጎች ተገድለው ሊሆን ይችላል የሚለው ሪፖርት እንደደረሰው የጠቆመው የአፍሪኮም ቃል አቀባይ ጆን ማንሌይ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ” የአሜሪካ ጦር የአፍሪካ እዝ ተሽከርካሪውም ሆነ በውስጡ የነበሩ ተሳፋሪዎች የአልሻባብ አባላትና እንዲሁም የአልሻባብን እንቅስቃሴ የሚደግፉ መሆናቸውን ምክንያታዊ በሆነ መንገድ እርግጠኞች ነበርን” ሲሉ አብራርተዋል::

አሜሪካ በሶማሊያ የምታደርገው የአየር ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደቡባዊት ሶማሊያ ላይ ያሉ እንቅስቃሴዎችን መቆጣጠር አለብን ማለታቸውን ተከትሎ ነው። በትናንትናው ዕለት የአልሸባብ ታጣቂዎች የአሜሪካን የጦር ሰፈር ያጠቁ መሆናቸውን መዘገባችን ይታወሳል::

ብዙ የተወራለት ቤተ መንግሥት  መስከረም 29 ለጎብኚዎች ክፍት ይሆናል ተባለ

የቤተ መንግስቱ ዕድሳት በቀጣይ ሳምንት ሀሙስ መስከረም 29 ቀን 2012 ዓ.ም ተጠናቆ ለጎብኚዎች ክፍት እንደሚደረግ ዛሬ ይፋ ተደርጓል::

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቻይና መንግስት ድጋፍ ግንባታው የሚካሄደው የሽገር ማስዋብ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ ስነ ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ላይ ነው ይህንን የሰማነው::

የቤተ መንግስት እድሳቱ መስከረም 29 2012 ተጠናቆ ለጎብኚዎች ክፍት ይሆናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፤ በማግስቱ አርብ መስከረም 30 2012 ዓ.ም ደግሞየመከላከያ ሠራዊት እና የፌዴራል ፖሊስ  አባላት ቤተ መንግሥቱን እንደሚጎበኙ ከወዲሁ አረጋግጠዋል::

ቅዳሜ እና እሁድ በዕድሜ ታላላቅ ዜጎች እና የጎዳና ተዳዳሪዎች ቤተ መንግሥቱን እንዲጎበኙ ፕሮግራም የተያዘላቸው መሆኑን ያመላከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ ከስኞ ጥቅምት 3 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ማንኛውም ዜጋ 200 ብር በመክፈል ቤተ መንግስቱን መጎብኘት ይችላል ብለዋል::

አትክልት ተራ የ19 ዓመቱን ወጣት የገደሉት ፖሊሶች ሆን ተብሎ  እንዲሰወሩ ተደርጓል ተባለ

ጳጉሜ 3 ቀን 2011 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ በተለምዶ አትክልት ተራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በፖሊስ ሦስት ጥይቶች በአሰቃቂ ሁኔታ ተደብድቦ የተገደለው የ19 ዓመቱ ወጣት የጅብሪል አሕመድ ገዳዮች እስካሁን ድረስ ይፋ አለመደረጋቸው እያነጋገረ ይገኛል::

ከጅምሩ ወጣቱ በከተማዋ የፖሊስ አካላት ስህተት መገደላቸውን ማመን ያልፈለገው ኮሚሽኑ ገዳዮቹን ፖሊሶች ይህን ያህል ጊዜ ሳያሳውቅና ሕግ ፊት ሳያቀርብ መቆየቱ የፀጥታ አካላቱን ሆን ብሎ  እንዲሰወሩ አድርጓል የሚል ጥርጣሬ ላይ እንደጣላቸው ቤተሰቦቹና የቅርብ ጓደኞቹ ይናገራሉ::

ጅብሪል አህመድ ገና በለጋ ዕድሜው ሁለት እህቶቹን እና 4 የእህቶቹን ልጆች ተሯሩጦ በሚያገኘው ገቢ የሚያስተዳድር ወጣት ነበር:: ቀደም ሲል በሞተር ሥራ እሱንና ቤተሰቦቹን ያንቀሳቅስ የነበረው ወጣት ከሰኔ ወር መጨረሻ ጀምሮ የሞተር አገልግሎት ይቁም በመባሉ ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር አትክልት ተራ ፌስታል የማከፋፈል፣ አንዳንዴም ቃሪያና ሎሚ እያወረደ በችርቻሮ በመሸጥ ሕይወትን ለማሸነፍ ሲታገል ቆይቷል::

ይሁንና ከላይ በተጠቀሰው ቀን ግን  በፖሊሶች በጥይት ተመትቶ ሕይወቱ አልፏል:: በጊዜው በአካባቢው ሎሚና ቃሪያ ከማውረድ ጋር በተያያዘ በአካባቢው በነበሩ ሰዎች መሀል አለመግባባት ተከስቶ የነበረ ቢሆንም የተወሰደው የግድያ ዕርምጃ ግን ፍፁም ተገቢ እንዳልሆነ የሚናገሩ የዓይን እማኞች በርካታ ናቸው:: በተለይ ወጣት ጅብሪል የተገደለበት መንገድ አግባብ ካለመሆኑ ባሻገር ጥፋቱም ግልጽ አይደለም ይላሉ::

ወጣቱ በፖሊሶች በቅድሚያ ከኋላው በጥይት ታፋው ላይ ተመትቶ ከወደቀ በኋላ ፖሊሶቹ በተኛበት በሁለት ጥይት ደጋግመው እንደመቱት የገለጹት ቤተሰቦቹና የቅርብ ጓደኞቹ ጅብሪል አሕመድ በሕይወት የመትረፍ ዕድል የነበረው ቢሆንም ፖሊሶች ሰዎች ወደ ሕክምና እንዳይወስዱት ለ40 ደቂቃ ያህል መከልከላቸውን ተናግረዋል::

ግድያውን በተመለከተ በፍጥነት መረጃ ለመጠየቅ እና ፖሊሶቹም በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ለማድረግ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በሄዱበት ወቅት ስለጉዳዮ ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ፖሊሶች እየገለጹላቸው ቅፅበት ኮሚሽኑ “በአትክልት ተራ አካባቢ ፖሊሶችን በገጀራ ሊያጠቃ የሞከረ ወጣት ተገደለ” የሚል የሀሰት መግለጫ በማኅበራዊ ሚዲያዎች በማየታቸው ቅስማቸው በእጅጉ እንደተሰበረ አስታውቀዋል::

በተደጋጋሚ ምስጉኑን ወጣት በግፍ የገደሉ ፖሊሶች በቁጥጥር ስር እንዲውሉና በሕግ ፊት እንዲዳኙ የሟች ቤተሰቦች ቢጠይቁም ኮሚሽኑ እንኳን ወንጀለኞቹን ለፍርድ ሊያቀርብ ቀርቶ ማንነታቸውን ከመግለፅ ሆን ብሎ እንደሰወራቸው ገልጸዋል::

ኖርዌይ 31 ኢትዮጵያውያንን ከሀገሯ ማስወጣቷን አረጋገጠች

የተለያዮ ሀገራት ስደተኞችን ከሀገሩ በማስወጣት ላይ የሚገኘው የኖርዌይ መንግሥት 31 ኢትዮጵያውያንን እንዳባረረ ተሰማ:: የኖርዌይ ስደኞች ጉዳይ ፖሊስ (The National police Immigration Service) እኤአ በ2019 ብቻ 31 ኢትዮጵያውያን ኖርዌይን ለቅቀው እንዲወጡ አድርጊያለሁ ሲል መግለጫ አውጥቷል::

ከኖርዌይ እንዲወጡ ከተደረጉት ኢትዮጵያውያን መካከል 12ቱ በቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ ሲላኩ ፤ ቀሪዎቹ ሊቀበላቸው ወደሚችል ሦስተኛ ሀገር መላካቸውን መግለጫው ያስረዳል:: ወደ ሌላ ሀገር ተሸኝተዋል የተባሉት ኢትዮጵያውያንየትኞቹ ሀገራት እንደተቀበሏቸው ግን በይፋ አልተገለጸም::

ከኖርዌይ በ2019 ብቻ እንዲወጡ ከተደረጉ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች መካከል 47 ኤርትራውያን እንደሚገኙበት መግለጫው ያስረዳል:: ከእነዚህ ኤርትራውያን መካከል ግን ወደ ሀገራቸው በቀጥታ የተወሰዱት ሁለት ብቻ መሆናቸውም ታውቋል::

በኤርትራ የብሔራዊ አገልግሎት የተጀመረበትን 25ኛ ዓመት ክብረ በዓል በኖርዌይ ኤርትራ ኢምባሲ ሲከበር ተገኝተው ከማስታወቂያ ሚኒስትሩ፣ የማነ ገብረመስቀል፣ ጋር ኬክ የቆረሱ ስደተኛ ኤርትራውያን ላይ የኖርዌይ መንግሥት የጥገኝነት ጥያቄያቸውን በድጋሚ እያጤነው መሆኑ አይዘነጋም::

የኖርዌይ መንግሥት ከሀገሬ ይውጡልኝ ብሎ ካሰናበታቸው የተለያዩ ሀገራት ዜጎች መካከል 23 ታዳጊዎች እንዳሉበትም ሰምተናል:: ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የተደረጉ እና ወደ ሦስተኛ ሀገር የተሸጋገሩ ዜጎች ጥገኝነት ጠይቀው የነበሩ፣ ወደ ኖርዌይ እንዳይገቡ የታገዱ እንዲሁም እንዲወጡ የተደረጉ ናቸው ተብሏል::

LEAVE A REPLY