የዛሬዋ ኢትዮጵያ ለኤሊያስ እና ለጃዋር || ያሬድ ኃይለማርያም

የዛሬዋ ኢትዮጵያ ለኤሊያስ እና ለጃዋር || ያሬድ ኃይለማርያም

የሞተለሽ ቀርቶ የገደለሽ… የፖለቲካ አዙሪት የተጠናወታት አገራችን፤

በቅርብ ጊዜ የእስክንድር ነጋ እና የጃዋር ኢትዮጵያ በሚል አገራችን ሁለቱን ዜጎች በምን ሁኔታ እንደያዘቻቸው ጽፌ ነበር። አዎ ያ አይነቱ ስሜት ዛሬም የኤሊያስ ገብሩን የፍርድ ቤት ውሎ ስሰማ እና ጃዋር በኦሮሚያ ክልል ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶችን አፈራራሚና አስታራቂ ሆኖ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ፊት ቆሞ ሳይ “አገሬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ፤ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ” የሚለውን ግጥም የተገጠመላቸውን እና አገር የከዳቻቸውን፣ አብዮት የበላቸውን፣ ሕዝብ ባላየ ፊቱን አዙሮ ድምጹን የነፈጋቸውን፣ ሹማምንት የፈረጠሙ ክርኖቻቸውን የፈተኑባቸውን እነዛን ለአገር እና ለሕዝብ የታገሉ ምርጥ የኢትዮጵያ ጀግኖች ሰማዕታት አስታወሰኝ።

ኤሊያስ ገብሩ ደፋር እና ለእውነት የቆመ ጎበዝ ጋዜጠኛ ነው። አንደበቱ የተቆጠበ፣ አገር ወዳድ እና ሰው አክባሪ ነው። ለሰላም እና ለፍትህ ካለው ቀናዒነት ውጭ አንድም ቀን ጸብ ጫሪ፣ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጭ ወይም አመጽ ቀስቃሽ የሆነ ነገር ሲጽፍም ሆነ ሲናገር ሰምቼው አላውቅም። በተቃራኒው ግን በድፍረት መንግስት ላይ የሚያየውን ህጸጽ ከዘመነ መለስ እስከ ዘመነ አይብ ሲተች እና ሲነቅፍ አውቀዋለሁ። ዛሬ ፖሊስ በፍርድ ቤት በኤሊያስ ገብሩ ላይ ያቀረበውም ማስረጃ ይህንኑ ጥሩ አድርጎ ያሳያል። ኤሊያስ አብይንም ሆነ ማንንም ከመተቸት የሚሰንፍ ጋዜጠኛ አይደለም። ሙግቱ ልክ ነው ወይም አይደለም የሚለው ሌላ ጉዳይ ሆኖ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩን መወረፍ በምንም ተአምር በሽብርተኝነት ሊያስጠይቀው አይችልም። ኤሊያስ ትግልን አንባገነኖች አፍንጫ ስር ሆኖ ነው ሲታገል የኖረው እንጂ እንደ ጃዋር በብዙ ሺህ ማይልስ እርቀት ላይ ሆኖ በስማ በለው አልነበረም። ለዚህም የከፈለው ዋጋ ጥሩ ማሳያ ነው።

በተቃራኒው ትግልን በኢንተርኔት ሲያጧጡፍ የነበረው ልጅ ጃዋር ወደ አገር ቤት ሳይገባም ሆነ ከገባ ወዲህ ከሚናገራቸው እና ከሚሰራቸው ነገሮች ውስጥ ከሦስቱ ሁለቱ ጸብ አጫሪ፣ ሕዝብን ሰዳቢ፣ አንድን ማህበረሰብ አጠልሺ፣ ዜጎችን ለወንጀል አድራጎት የሚያነሳሳ፣ አመጽን የሚቀሰቅስ፣ ሁከትን የሚያስፋፋ፣ የመንግስት ፖሊሲዎችን የሚያደናቅፍ፣ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን የሚጣጥላላ እኩይ እና በሕግ የሚያስጠይቁ ተግባሮች ናቸው። በጅዋር አድራጎት እና ቅስቀሳ የዜጎች ህይወት ጠፍቷል፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ንብረት ወድሟል፣ ሌሎች በርካታ የወንጀል አድራጎቶችም ተፈጽመዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩንም መስደብ የሚያሳስር እና የሚያስከስስ ከሆነ እንደ ጃዋር ግጥም አድርጎ፤ ልባሽ ጨርቃቸው እንኳ እንዳይሸጥ አድርጎ የሰደባቸው ሰው ያለ አይመስለኝም። ስልጣን እንዲለቁም ጠይቋል፤ ከመንግስቱ ኃይለማርያም ጎንም አስቀምጧቸዋል።

ዛሬ ለሕዝብ መብት የታገለው እና ለሰብአዊ መብቶች የተሟገተው ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በሃሰት ስማቸውን አጥፍተሃል በሚል በሽብር ወንጀል ተጠርጥሮ በእስር እየማቀቀ ነው። የንጹሃን ዜጎች ደም በእጁ ያለው ጃዋር ደግሞ ሲሰድባቸው በቆየው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፊት ቆሞ አፈራራሚና ሸምጋይ ሆኗል።

ይሄ ነገር ወዴት ይወስደናል?

ፍትህ ለኤሊያስ ገብሩ እና ለሌሎች በተመሳሳይ መልኩ ታስረው ለሚማቅቁ ዜጎች!
ፍርድ ጀዋር መሃመድ ለፈጸማቸው የወንጀል አድራጎቶች!

ፍትህ ዛሬም በብልሹ አሰራር ለሚማቅቁት የፖሊስ፣ አቃቤ ሕግ እና የፍርድ ተቋማት!

LEAVE A REPLY