የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ጥቅምት 18 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ጥቅምት 18 ቀን 2011 ዓ.ም

የአብን እና የባለአደራው አመራሮችን ጨምሮ 22 ሰዎች ከወራት በኋላ ከዕስር ተፈቱ

ከሰኔ አስራ አምስቱ የአማራ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናት ግድያ እና የባህርዳሩ ውዝግብ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለው የቆዮት የአብን አመራር እና አባላት የባላደራው ም/ቤት አመራርና አባላት እንዲሁም ጋዜጠኞች እና የአማራ ክልል ተወላጅ የሆኑ ዕስረኞች ዛሬ መፈታታቸው ታውቋል::

አስቀድሞም ቢሆን አያያዛቸው አሳማኝ እንዳልነበረ እና ብዙዎቹ ከስርዓቱ ላይ በፖለቲካና በአዲስ አበባ ጉዳይ ባላቸው ልዮነት ብቻ ለዕስር እንደተዳረጉ የጠቆመው የኢትዮጵያ ነገ ሪፖርተር ታሳሪዎቹ ከሁለት እስከ አራት ወር ድረስ በተለያየ መንገድ በዕስር ላይ እንዲቆዮ ከተደረገ በኋላ በዛሬው ዕለት በመታወቂያ ዋስ ብቻ እንዲወጡ መደረጉ ብዙ ግርምትና ትዝብት ማጫሩን ገልጿል::

በባህርዳሩ ጥቃት ሰሞን አዲስ አበባ ውስጥ ከመንገድ ላይ ተይዞ የታሰረው የባላደራው ም/ቤት የሕዝብ ግንኙነት ስንታየሁ ቸኮል በታሰሩበት ወቅት ከተጠረጠሩበት ወንጀል ጋር የተያያዘ ምርመራ ፈጽሞ እንዳልተደረገባቸው ጠቁሞ በአንጻሩ ለምንድን ነው የባላደራው ም/ቤት አባል የሆናችሁት? ኦዴፓን የምትጠሉት ለምንድን ነው? በሚሉ መሰል ጥያቄዎች በተደጋጋሚ መርማሪዎች ያሰለቿቸው እንደነበር ለሪፖርተራችን ገልጿል:::

የአማራ ብሔረዊ ንቅናቄ (አብን) የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ ክርስቲያን ታደለ እና ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩን ጨምሮ የአብን እና የባላደራው አባላት የሆኑ 22 ሰዎች በመታወቂያ ዋስ ከዕስር ተፈትተዋል::

ከ20 ዓመት በላይ በፕሬስ ውስጥ የቆየው  ፍቃዱ ማ/ወርቅ 7 ዓመት ተፈረደበት

በኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ውስጥ የበርካታ ዓመታት ልምድና ሰፊ ተሳትፎ ካላቸው ጋዜጠኞች መሀል አንዱ የሆነው ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማህተም ወርቅ ከስድስት ዓመት በፊት በአምባገነኑ ስርዓት አማካይነት በተመሰረተበት የፈጠራ ክስ ጥፋተኛ ተብሎ የሰባት ዓመት ዕስር ተላልፎበታል::

ጋዜጠኛ ፍቃዱ በወያኔው መንግሥት ነጻውን ፕሬስ የማዳከሚያ ወንጀል ተከሶ በለውጡ ቡድን መንግሥት ከባድ ቅጣት የተወሰነበት የመጀመሪያውና ብቸኛው ጋዜጠኛ ሆኖ ተመዝግቧል::

በአሁኑ ወቅት በየሳምንቱ ቅዳሜ ለኅትመት ስትበቃ የቆየችው የግዮን መጽሔት አሳታሚ የሆነው ጋዘዜጠኛ ፍቃዱ ማህተመ ወርቅ በተለይ ለውጡን በማበረታታት እና በመደገፍ ረገድ ላለፉት 18 ወራት ከፍተኛ ሥራ መሥራቱን የሚያውቁ ወገኖች ሥልጣን ላይ ያለው አካል ጉዞውን ያቀኑለትና በሙያው ሥነ ምግባር ታንጸው የሠሩ ወገኖችን አለማበረታታቱ ትዝብት ላይ እየጣለው ይገኛል::

ባለፈው ሳምንት ከአምስት ዓመት በላይ ሲንከባለል በቆየው እና በ2006 ዓ.ም መጨረሻ በጉምቱው ወያኔ ባለስልጣን አቶ በረከት ስምዖን አቀናባሪነት ሕገ መንግሥቱን በኃይል ለመናድ  እና የታክስ ማጭበርበር  በሚሉ ክሶች ጥፋተኛ ተብሎ አንድ ሳምንት በዕስር ላይ ከቆየ በኋላ ዛሬ የሰባት ዓመት ዕስርና የሰባት ሺኅ ብር ቅጣት ተላልፎበታል::

በወቅቱ ስልጣን ላይ የነበሩት የወያኔ ሹማምንት በተቀነባበረ የፈጠራ ክስ አምስት መጽሔቶችና አንድ ጋዜጣን ከሕትመትመት ውጪ ማድረጋቸውን ተከትሎ በወቅቱ አርባ ሁለት ጋዜጠኞች ከሃገር ሲወጡ ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማህተመ ወርቅ ግን ከሀገር የሚያስወጣ ወንጀል አልሠራሁም በሚል የፈጠራውን ክስ ለመጋፈጥ ወስኖ በሀገር ቤት መቅረቱ ይታወሳል::

ዛሬ የተሰየመው የልደታ የመጀመሪያ አንደኛ ደረጃ ፍ/ቤት ስምንተኛ ወንጀል ችሎት ከአምስት ዓመት በላይ የቆየውን የጋዜጠኛ ፍቃዱ ማህተም ወርቅ ክስን አስመልክቶ በሰጠው የቅጣት ውሳኔ ፍቃዱ ማ/ወርቅ የተከሰሰበት እና በማኔጂንግ ዳይሬክተርነት በሚመራው ዕንቁ መጽሔት አማካይነት የሰባት ዓመት ቅጣት ተወስኖበታል:: የዕንቁ መጽሔት አሳታሚ የነበረውና በአሁኑ ወቅት በስደት ላይ የሚገኘው ( ወንድሙ) አለማየሁ ማህተም ወርቅ በሌለበት የ25 ዓመት ዕስር ተላልፎበታል::

በሀገሪቱ ውስጥ ለውጥ መጥቷል እየተባለ በሚነገርበት በዚህ ወቅት፤ በርካታ በፖለቲካና በመቶ ሚሊዮን ብር የሚቆጠር ገንዘብ በተናጠል በሙስናና በታክስ ማጭበርበር መንግሥትን አሳጥተዋል የሚባሉ በርካታ ሰዎች ክሳቸው ተሰርዞ በይቅርታና በምህረት ሲለቀቁ ጋዜጠኛ ፍቃዱ ፕሬሱን ጠልፎ ለመጣል በተዘጋጀው ወጥመድ ጥፋተኛ ተብሎ በሕግ ፊት የዚህን ዓመት ያህል ዕስር መወሰኑ ፕሬሱ አሁንም በመንግሥት በኩል በቀና መልኩ እየታየ እንዳልሆነ የሚናገሩ በርካታ ጋዜጠኞች ናቸው::

ዛሬ በችሎት የታደመው የኢትዮጵያ ነገ የአዲስ አበባ ሪፖርተር በፍቃዱ ማ/ወርቅ የፍርድ ውሳኔ ብዛት ያላቸው የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች ሥልጣን ላይ ባለው የለውጥ ቡድን አባላት የጋዜጠኞች አያያዝ ላይ ቅሬታቸውን እየገለጹ ሲሆን በቀጣይም መንግሥት ከጅምሩ መቋረጥ የነበረበትን ክስ እንዲያቋርጥ የተለያዮ ግፊቶችን ለማድረግ እየተዘጋጁ መሆናቸውን ዘግቧል::

በኦሮሚያ ከተምች ከነበረው ግጭት ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ 359 ሰዎች ተያዙ

ሰሞኑን  በኦሮሚያ ክልል ከነበረው ግጭትና ጥቃት ጋር በተያያዘ 359 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።

አሁን ላይ በኦሮሚያ ያለው ሁኔታ እየተረጋጋ መምጣቱን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ከፍያለው ተፈራ ጠቁመው እሁድ ዕለት የሟቾች ቁጥር 67 እንደሆነ መገለጹንና ከዚያ በግጭት ሳቢያ የሞቱ ሰዎች አለመኖራቸውን አስረግጠው ተናግረዋል::

በአብያተ ክርስቲያኖቿና በምዕመኖቿ ላይ ጥቃት እንደተፈጸመ የገለጸችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሕዝብ ግነኙት ኃላፊ የሆኑት መልዓከህይወት አባ ወልደየሱስ ሰይፉ በበኩላቸው፤ 60 የሚደርሱ የእምነቱ ተከታዮች ባለፈው ሳምንት ባጋጠመው ሁከት መገደላቸውን ይፋ አድርገዋል::

“ከእሁድ ወዲህ በሞጆ ከተማ 1 ሰው በባሌ ሮቤ ደግሞ 2 ሰዎች ተገድለው ተገኝተዋል። የሰዎቹ ግድያ ከግጭቱ ጋር የተያያዘ ይሁን በሌላ ምክንያት ይሁን አስካሁን አልታወቀም። የማጣራት ሥራዎች እየተሰሩ ነው” ሲሉም የኮሚሽነሩን ከላይ የሰፈረውን መግለጫ አጣጥለዋል።

ኮሚሽነር ጀነራል ከፍያለው ህይወታቸውን ካጡ ሰዎች 80 በመቶ (54 ሰዎች) የሞቱት በእርስ በእርስ ግጭት እንደሆነ እና የተቀሩት ደግሞ ከጸጥታ አስከባሪ ጋር በነበረው ግጭት ህይወታቸውን ያጡ መሆናቸውን ገልጸው ፤ ከተቃውሞ ሰልፍ ወደ ሃይማኖታዊ ግጭት በተቀየረው ኹከት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ‘ይሄኛው አካል ነው ወይም ያኛው ነው’ ማለት አይቻልም የሚል በገሀድ የታየውን ዕውነታ የሚሸፋፍን መግለጫ ሰጥተዋል።

“ሁከቱ ወደ ሃይማኖታዊ ግጭት ከተቀየረ በኋላ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት የዚኛው ሃይማኖት ተከታይ ነው ማለት አይቻልም። የተቃውሞ ሰልፉ ወደ ግጭት ከተቀየረ በኋላ በሁለቱም ጎራ ባሉት ሃይማኖት ተከታዮች በኩል ህይወት ጠፍቷል” ሲሉም በቤተክርስቲያን ላይ የደረሰውን ጥቃትና ዕልቂት ከግምት ያልከተተ አስተያየት ሲሰነዝሩ ተስተውለዋል ።

የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሞቱብኝ ምዕመኖች ቁጥር 60 ነው ማለቷን ተከትሎ ኮሚሽነር ጀነራል ከፍያለው በሰጡት ምላሽ “እኛ እንዲህ አይነት መረጃ የለንም። በክልሉ ውስጥ የሚፈጠረውን የምንቆጣጠረው እኛ ነን። እነሱ ይህን መሰል መረጃ ከየት እንዳመጡ አናውቅም” ከማለታቸው ባሻገር ፤ ሰሞኑነ በነበረው ግጭት ጉዳት የደረሰባቸው ሦስት የዕምነት ቤቶች ብቻ ናቸው ሲሉም ተደምጠዋል።

“በአዳማ ከተማ አንድ መስጅድ እንዲቃጠል ተደርጓል። ከአዳማ ወጣ ብለው በሚገኙ ገጠራማ ስፍራዎች ደግሞ አንድ የፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያን እና ሌላ አንድ ግንባታው ገና እየተጀመረ ያለ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ተቃጥሏል” ያሉት የኦሮሚያው አመራር ፤ ከሰሞኑ የተከሰተውን ግጭት ኦሮሚያ ፖሊስ ፈጥኖ መቆጣጠር ላይ ድክመት አሳይቷል በሚባለው ትችት ላይ ምላሻቸውን ሲሰጡም “የኦሮሚያ ፖሊስ ግጭቱን ለመቆጣጠር ህይወት እስከመክፈል ድረስ መስዋትነት እየከፈለ ነው” ነው በማለት የክልሉ ፖሊስን በስፋት የተቹትን የነዋሪዎችን ጠንካራና ተደጋጋሚ ምስክርነት ውድቅ አድርገዋል::

በሁሉም ስፍራዎች የወጡት የተቃውሞ ሰልፎች ከአቅም በላይ የሆኑ ነበሩ ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ከሌሎች የመንግሥት የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን ግጭቱ አሁን ወደ ደረሰበት ደረጃ እንዲወርድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተው የኦሮሚያ ፖሊስ መሆኑን ጠቁመው በኦሮሚያ ፖሊስ አባላት በተተኮሰ ጥይት ሰዎች መገደላቸውንም አምነዋል።

“በአምቦ ከተማ ይህን መሰል ክስተት አጋጥሟል። ድርጊቱንየፈጸሙትም በአስቸኳይ በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተከናወነባቸው ነው። የወሰዱት እርምጃ ተመጣጣኝ ነው ወይ? ይህን እርምጃ እንዲወስዱ ያስገደዳቸው ሁኔታ ምን ነበር? የሚሉት ጉዳዮች ከተመረመሩ በኋላ መጠየቅ ያለበት ሰው ተጠያቂ ይደረጋሉ” ሲሉ ተናግረዋል::

ኦሮሚያ ፖሊስ ለአንድ አካል ወግኗል የሚለውን ክስ ኮሚሽነር ጀነራሉ አጣጥለውታል:: “ይህ አይነት ባህሪም በአባላቶቻችን ዘንድ አልተስተዋለም” ይላሉ። “ፖሊሶቻችን ሁሉንም ህዝብ ይታደጋሉ። በኹከቱ ወቅት በሁለቱም ጎራ የነበረውን ከግንዛቤ በማስገባት የሕግ ማስከበር ሥራውን ሲያከናውን ነበር። ለአንድ ወገን አድልቶ ሌላውን ሲጎዳ ነበር የሚለው ፍጹም ውሸት ነው” በማለትም ተከራክረዋል።

ባለፈው ሳምንት ካጋጠመው አለመረጋጋት ጋር ግነኙነት አላቸው ተብለው በመጠርጠር በቁጥጥር ስር ከዋሉት 359 ሰዎች በተጨማሪ ሌሎች ሰዎችንም በቁጥጥር ሥር ለማዋል እየተሠራ እንደሆነ የጠቆሙት ኮሚሽንር ከፍያለው፤ አሁን በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ችግሩ ተፈጥሮባቸው የነበሩት ከተሞች ወደ ቀደመ ሰላማቸው ተመልሰዋል በማለት ክልሉ በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ማረጋገጫ ሰጥተዋል::

ሓላፊው በይፋ ይህን ይበሉ እንጂ ዛሬ ወደ ምዕራብ አሩሲ እና የባሌ ከተሞች ስልክ ደውሎ ነዋሪዎችን ደውሎ ያነጋገረው የኢትዮጵያ ነገ ሪፖርተር ነዋሪዎች አሁንም በጸጥታ ስጋት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙና የተጀመረው ሃይማኖታዊ ጥቃት ፈጽሞ እንዳልረገበ መረጃዎችን በመሰብሰብ ለማወቅ እንደቻለ ዘግቧል:: ክርስቲያኖች አሁንም በር ዘግተው መቀመጣቸውን እና በከተማዋ የሚገኘው ቁጥሩ 20 የማይሞላ የመከላከያ ሠራዊት ጥበቃ እያደረገ የሚገኘው በቤተ ክርስቲያናት ደጃፍ እና በውስጡ የተጠለሉትን ዜጎች ብቻ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል::

በነቀምቴ ከተማ የኢትዮ ቴሌኮም ሓላፊ በጥይትና በስለት ተደብድበው ተገደሉ

በኢትዮ ቴሌኮም የምዕራብ ዞን ሓላፊ የነበሩት አቶ ገመቺስ ታደሰ ከትናንት በስቲያ ዕሁድ አመሻሽ 1 ሰዓት ገደማ ማንነታቸው ባልታወቁ ግለሰቦች መገደላቸው ተሰማ።

የነቀምቴ ከተማ ፖሊስ አዛዥ የሆኑት ኮማንደር ግርማ አብዲሳ እስካሁን በግድያው ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር የዋለ ሰው የለም  ብለዋል:: በከተማዋ የደህንነት ስጋት የለም ያሉት ኮማንደር ግርማ የአቶ ገመቺስ ገዳዮችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የምርመራ ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል ብለዋል።

ግለሰቡ ህይወታቸው ሳያልፍ ወደ ሆስፒታል ቢወሰዱምብዙም ሳይቆዩ ህይታቸው ማለፉን የነቀምቴ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ዳምጠው ጋረደው ለቢቢሲ አስታውቀዋል። አቶ ገመቺስ ቢያንስ አራት ጊዜ በጥይት መመታታቸውን እና አንድ ጊዜ ደግሞ በስለት መወጋታቸውን ሜዲካል ዳይሬክተሩ አረጋግጠዋል።

“ግራ እጁ ላይ ሁለት ጊዜ በጥይት ተመቷል። ትከሻው ላይም በጥይት ተመቶ በብብቱ በስተግራ በኩል ጥይቱ ወጥቷል፤ እግሩ ታፋው አካባቢ ሁለት ቦታ መመታቱን እና ጥይቶቹ የገቡበት እና የወጡበት ቦታ ይታያል” ያሉት ዶ/ር ዳምጠው፤የአቶ ገመቺስ ህይወት በፍጥነት እንዲያልፍ ያደረገው ደረታቸው ላይ በስለት መወጋታቸው እንደሆነ ጠቁመዋል።

“ደረቱ ላይ በስለት ተወግቷል። በስለት የተወጋበት ቦታ በጣም ሰፊ ነው ፣ ህይወቱ እንዲያልፍ ያደረገውም እሱነው። እኔ ሆስፒታል ነበርኩ። ሲመጣ በህይወት ነበር ግን ብዙ ደም ፈሶት ስለፈሰሰው ህይወቱን ማትረፍ አልተቻለም” በማለት የነበረውን ሁኔታ በግልጽ አስቀምጠዋል።

አቶ ገመቺስ በወለጋ ዩኒቨርሲቲ በማናጅመንት የዶክትሬት ድግሪያቸውን እየተማሩ ነበር። ይህን አደጋ ተከትሎም የወለጋ ዩኒቨርሲቲ በአቶ ገመቺስ ሞት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ገልጿል።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ ለዓመታት አንድ ዶርም መጋራታቸውን እና ከወራት በፊት ስለተሞከረበት ግድያም አነጋግሮት እንደነበር ሄኖክ የተባለ የአቶ ገመቺስ ጓደኛ በትዊተር ገፁ ላይ ያስነበበ ሲሆን፤ ሄኖክ እንዳለው ገመቺስ ጥሩ ውጤት ከነበራቸው ተማሪዎች መካከል አንዱ ነበር። በጅማ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ የገመቺስ ፍላጎት እንደ ብዙዎቻቸው ወደ ውጭ ሃገር መሄድን ወይም አዲስ አበባ ላይ ስመ ጥር ኩባንያዎችን መቀላቀል ፣ ይልቁንም ወደ ነቀምት መመለስ ነበር ሲል ግለሰቡ የወጡበትን ማኅበረሰብ ለማገልገል የነበራቸውን ጥልቅ ፍላጎት አሳይቷል::

ከወራት በፊት የግድያ ሙከራ ተደረገበት የሚል መረጃ በመስማቱ ገመቺስን ጠይቆት እንደነበር እና ለዚህም ገመቺስ የሰጠውን ምላሽ ጭምር ሄኖክ ፎቶ አንስቶ በትዊተር ገፁ ላይ ለሕዝብ ይፋ ማድረጉን ቢቢሲ ዘግቧል።

ህዝብ ለቀረበለት አገርን የማዳን ጥሪ በሕብረት መልስ መስጠት የሚገባው ዛሬ መሆኑን ኢዜማ ገለጸ

በፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በአንዷለም አራጌና የሺዋስ አሰፋን በመሰሉ በሳል ፖለቲከኞች የሚመራው ኢዜማ በወቅታዊው የኦሮሚያ ግጭትና ዕልቂት ዙሪያ ጠንከር ያለ መግለጫ ሰጥቷል::

በሀገሪቱ ውስጥ የታየውን የለውጥ ብልጭታ ላለማደብዘዝ ለበርካታ ወራት ነገርችን በሰከነ መንገድ ሲከታተል የኖረውና ለሁሉም ነገር መግለጫ በማውጣት የማይጣደፈው ኢዜማ በቅርብ ጊዜያት ሁለት ከበድ ያሉ ማስጠንቀቂያዎችን በማውጣት ከለውጡ ቡድን ላይ ያለው ተስፋ እየደበዘዘ መሄዱን አመላክቷል::

በተለይም በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ ሠሞኑን በተለያዮ የኦሮሚያ ከተሞች ለታየው ግጭትና ለደረሰው ዕልቂት መንስዔ የሆኑና በጥፋት ተግባሩ ላይ የተሠማሩ ሰዎች በሙሉ በሕግ እንዲጠየቁ ጥሪ አቅርቧል::

LEAVE A REPLY