ነጻነትም፣ ስርዓትም ማጣት! || በፍቃዱ ዘ. ኃይሉ

ነጻነትም፣ ስርዓትም ማጣት! || በፍቃዱ ዘ. ኃይሉ

ሁሉም ሰው የራሱን ጥቅም ለማስከበር በሚያደርገው እንቅስቃሴ ግጭት እንዳይፈጥር በነጻነትና በስርዓት መካከል እርቅና ሚዛን ያስፈልጋል የሚሉት በፍቃዱ ኃይሉ፣ በአብዛኛው ዴሞክራሲያዊ ስርዓቶችም ሰብኣዊ ነጻነትን ከተገቢው ስርዓት ጋር ሚዛን አስጠብቀው መዝለቅ የቻሉት ናቸው ይላሉ። ይሁንና ይህንን የነጻነት እና ስርዓትን ሚዛን ጠብቆ የሚጓዝ ስርዓት መመሥረት ብዙ ጊዜና ጥረት ከመጠየቁ በላይ የዜጎችንም ቁርጠኝነት ይፈልጋል ሲሉ ጉዳዩን ከኢትዮጵያ ነባራዊ ኹኔታ ጋር አዛምደው ሐሳባቸውን አካፍለዋል።

“ሰዎች መልዓክ ቢሆኑ ኖሮ፥ መንግሥታት አያስፈልጉም ነበር። ሰዎችን የሚገዟቸው መላዕክት ቢሆኑም ኖሮ፥ መንግሥታት ላይ ቁጥጥር መጣል አያስፈልግም ነበር። ሰዎችን ሰዎች በሚያስተዳድሩበት ሁኔታ መንግሥትን መቅረፅ፥ ከባድ ፈተና አለበት። መጀመሪያ ገዢው ተገዢዎቹን መቆጣጠር መቻል አለበት፤ ከዚያ ገዢው ራሱን እንዲገዛ ማስገደድ ያስፈልጋል” – ጀምስ ማዲሰን (‘ፌዴራሊስት ፔፕርስ’ 51)

ጀምስ ማዲሰን ‘ከአሜሪካ መሥራች አባቶች’ አንዱ ናቸው። ‘ፌዴራሊስት ፔፐርስ’ የሚባሉት አሌክሳንደር ሐሚልተን፣ ጀምስ ማዲሰን እና ጆን ጄይ የጻፏቸው 85 መጣጥፎች መድብል ነው። አሌክሳንደር ሐሚልተን በነዚህ መጣጥፋቸው ጠንካራ ማዕከላዊ ወይም ፌዴራላዊ መንግሥት እንዲኖር ሲከራከሩ፣ ጀምስ ማዲሰን ደግሞ መንግሥት ከቁጥጥር ውጭ እንዳይወጣ ሥልጣኑ ገደብ ይኑረው በሚል ሲከራከሩ ከርመዋል። 51ኛው መጣጥፋቸውም “የማዲሲያን ሞዴል” እየተባለ የሚታወሰው ቁጥጥር እና ሚዛን (‘ቼክ ኤንድ ባላንስ’) የሚሰኘው አንዱ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ዋልታ ነው።

ሁሉም ሰዎች ነጻነታቸውን ይወዳሉ። ነገር ግን ነጻነታቸው በጉልበተኞች መነጠቁ አይቀርም። ሁሉም ሰዎች የየራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር ወዲያ ወዲህ ሊሉ መጋጨታቸው እና ትርምስ መፈጠሩም አይቀሬ ነው። ለዚህ ነው ስርዓት (‘ኦርደር’) የሚያስፈልገው። በነጻነት እና ስርዓት መካከል እርቅ እና ሚዛን የሚያስፈልገውም ለዚሁ ነው። መንግሥታዊ ስርዓቶች ከሽፍትነት ተነስተው አሁን የደረሱበት ደረጃ የዘለቁት መብቶች ቆርሰው በመውሰድ በምላሹ መጠነኛ ስርዓት መስጠት በመቻላቸው ነው። ይህንን በማገናዘብ ነው ዢን-ዛክ ሩሶ የማኅበራዊ ውል (‘ሶሻል ኮንትራክት’) ኅልዮቱን የፈጠረው።

በየትኛውም ዓለም እንደሚሆነው ሁሉ በኢትዮጵያ ስርዓቶች የሚቀያየሩት በየጊዜው በነጻነት እና ስርዓት መካከል የተሻለ ሚዛን የሚያስጠብቅ አገዛዝ ፍለጋ ነው። በዘመናት ውስጥ ገዢዎች ፍፁማዊ ሥልጣናቸውን እያጡ ቀስ በቀስ በተገዢዎቻቸው ፍላጎት እየተመሩ መጥተዋል። ይኸውም ግፊት የተለያዩ የፖለቲካ ርዕዮቶችን ለመወለድ አስገደድዷል። ብዙዎቹ አገዛዞች በነጻነት ርዕዮተ ዓለማቸውን የሚመርጡት፣ እንዲሁም የተለያየ ዓይነት ሚዛን ለነጻነት እና ርዕዮት የሚሰጡት ሰዎችን ከሚመለከቱበት መነፅር በመነሳት ነው።

‘ሆሞ ኢኮኖሚከስ’
ሰው ‘ሆሞ ኢኮኖሚከስ’ ነው የሚለውን አረዳድ የሚያራምዱት “ሰው የማመዛዘን ችሎታውን ተጠቅሞ ትርፉን ለማካበት የሚኖር ፍጡር ነው” ብለው ያስባሉ። ስለሆነም፣ ሰውየው ወይም ሴትየዋ ጥቅም የምትለው ላይ እና ዋጋ የምትሰጠው ነገር ላይ ይለያዩ ይሆናል እንጂ ውሳኔያቸው ግን ሁሌም ጥቅምና ጉዳትን በማመዛዘን ስለሆነ ራሳቸውን የሚጎዳ ነገር አያደርጉም ብለው ነው የሚያስቡት።

ማኅበራዊ እንስሳ
ከ’ሆሞ ኢኮኖሚከስ’ በተቃራኒ ሰው ማኅበራዊ እንስሳ ነው ብለው የሚያምኑት ሰዎች ደግሞ ሰዎች ሌሎች ሰዎች ከሌሉ መኖር የማይችሉ፣ ወይም በመኖራቸው ውስጥ ትርጉም የማያገኙ እንስሳ አድርገው ይመለከቷቸዋል። ስለሆነም ማኅበራዊ ግንኙነታቸውን ከሁሉ በላይ እንደሚያስበልጡ ያምናሉ። ሰዎች በሰዎች ጎደሎ እየተሞላሉ በጋራ የሚኖሩ ፍጡራን ናቸው ብለው ያምናሉ።
ሌሎች ደግሞ ሰዎች ‘ሆሞ ኢኮኖሚከስም’፣ ማኅበራዊ እንስሳም ናቸው ብለው ያምናሉ።

“መልካሞች” ወይስ “ክፉዎች”?
በሌላ በኩል ደግሞ ሰዎች መልካሞች ናቸው ወይስ ክፉዎች የሚለው ጥያቄ ላይ የሚኖራቸው ምላሽ የሰዎችን ርዕዮተ ዓለም ለመቅረፅ የሚወስን መሥፈርት ነው። “ሰዎች በተፈጥሯቸው ጥሩ ናቸው” ብለው የሚያስቡ ሰዎች በብዛት ነጻነት ይሰጡና ለስርዓት ሲባል ሕግጋትን ያረቅቃሉ። የሕግ ዋነኛ መርሑም ይህ መሆን አለበት ብለው ይከራከራሉ። ሕግ ለመከልከል ሳይሆን ስርዓት ለማስያዝ ብቻ መውጣት አለበት ብለው ነው እነዚህኞቹ የሚያምኑት፤ ዓላማውም መቅጣት ሳይሆን ተጠያቂነት ማኖር ነው።

ከነዚህኞቹ በተቃራኒ “ሰዎች ክፉዎች ናቸው” ብለው የሚያስቡት ሰዎች ለስርዓት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው አነስተኛ ነጻነት ያጎናፅፋሉ። በነዚህ አመለካከት ሕግ የሚያስፈልገው ሰዎችን ለመከልከል ነው። ሰዎች አጥፊ ስለሆኑ በሕግ ማስፈራራት እና መቅጣት ያስፈልጋል የሚል አመለካከት አላቸው። ሰዎች በነጻ ፈቃዳቸው ስርዓት ይይዛሉ የሚል እምነት እነዚህኞቹ የላቸውም።

በነዚህ እና ሌሎችም አመለካከቶች የተቀረፁ ግለሰቦች ስብስቦች የሚመሠርቱት ስርዓት አሁን በሰፊው ተመራጭ በሆነው ስርዓት ዴሞክራሲያዊ ወይም አምባገነናዊ ይሆናሉ። ዴሞክራሲያዊ ስርዓቶች በአብዛኛው ሰብኣዊ ነጻነትን ከተገቢው ስርዓት ጋር ሚዛን አስጠብቀው መዝለቅ የቻሉት ናቸው።

ኢትዮጵያ፤ ከኹለቱም ያጣች
ኢትዮጵያ እስካሁን የይስሙላ ካልሆነ በስተቀር ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ማምጣት ካልቻሉ አገራት አንዷ ናት። በተለያዩ ጊዜያት ትግሎች ቢደረጉም የተሻለ ነገር ተፈጥሮ እንደሆን እንጂ ነጻነት እና ስርዓት ሕዝቡ በሚፈልገው ደረጃ ያላገኘባት አገር ናት። በጥቅሉ ከኹለት ያጣች አገር የሚለው ይገልጻታል።

የቅርብ ጊዜ ክስተቶችን ስንመለክት በከፍተኛ የሕዝቦች ተጋድሎ የተገኘው የፖለቲካዊ ለውጥ ዕድል የሚፈለገውን ነጻነትም ይሁን ስርዓት – በተናጠልም፣ በጋራም – ዜጎችን ማጎናፀፍ አልቻለም። ከ2010 ወዲህ መንግሥት አንፃራዊ ነጻነት እሰጣለሁ ሲል፥ የተለያዩ የፖለቲካ ልኂቃን የሚቀሰቅሷቸው ቡድኖች ሚሊዮኖችን አፈናቅለዋል፣ ብዙዎችን በደቦ ፍርድ ገድለዋል፣ ሌሎችን በፍርሐት አሸማቀዋል። ወጥቶ መግባትና ሠርቶ መብላት ዋስትና አጥቷል። እነዚህን ክስተቶች ከወዲያኛው ጊዜ ጋር እያነፃፀሩ ይሄ ይበልጣል ወይም ያንኛው ይብሳል መባባል ይቻላል፣ ነገር ግን ለችግሩ መፍትሔ አይሰጥም። ይልቁንም የችግሩን መንስዔ ጠቅሶ መወያየት ይበጃል።

አንፃራዊ ነጻነት በተገኘ ጊዜ ብዙ ኢትዮጵያውያን ከመንግሥት ጋር የነበራቸውን ግብ ግብ ትተው አግድም ከሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ያደረጉት ነጻነት በዝቶባቸው ወይም ስለማይገባቸው አይደለም። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ አለ ከምንለው የነጻነት ዐውድ የሰፋ ነጻነት ያላቸው አገራት በርካቶች ናቸው ነገር ግን እርስ በርስ አልተጠቃቁም፤ የመጠቃቃት ፍላጎትም የላቸውም። በሌላ በኩል ኢትዮጵያውያን ከሌሎች የሰው ዘሮች ተለይተው ነጻነት የማይገባቸው ሆነውም አይደለም። ይህንን ለማስረዳት አንድ ምሳሌ መጠቀም እፈልጋለሁ።

በኢትዮጵያ የተበራከቱትን እርስ በርስ ግጭቶች አስመልክታ አንዲት ሴት “የኢትዮጵያ ሕዝብ ነጻነት አይወድለትም፤ መረገጥ ነው የሚፈልገው” አለችኝ። “አንቺ መረገጥ ይወድልሻል?” አልኳት፣ “ኧረ እኔ!” አለችኝ፤ “ቤተሰቦችሽ መረገጥ ይፈልጋሉ?” አልኳት፤ “በፍፁም” አለች። “ጎረቤቶችሽ?” አሁንም መልሷ “የለም!” የሚል ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ ግጭት ውስጥ የሚገቡት ሰዎች ቁጥር ግጭቱን ከሚፀየፉት አንፃር ስንመለከተው እጅግ በጣም ትንሽ ነው። ነገር ግን በዜና የምንሰማው፣ ትኩረት የምንሰጠው ተገቢ ያልሆነውን ድርጊት ነው እና ገዢው ድርጊት ያኛው የሆነ ይመስለናል።

በኢትዮጵያ የሚቀሰቀሱት ግጭቶች እና ጉዳቶች በሙሉ በጥቂት ክፉ አመል በተጠናወታቸው ጠንሳሾች አነሳሽነት፣ “መጡብህ፣ ሊያጠቁሽ ነው፣ ሳትቀደም ቅደም፣ ወሰዱብሽ” በሚሉ የአሉባልታ ወሬዎች እና የሴራ ትንተና አቅላቸውን ያጡ ሰዎች ናቸው፤ የሰውን ‘ሆኖ ኢኮኖሚከስ’ እንዲሁም ማኅበራዊ እንስሳነት የሚፈነቅሉ ማነሳሻዎች ለግጭት መቀስቀሻነት ውለዋል። እነዚህ ግጭት ውስጥ የሚገቡ ሰዎች ለፖለቲካ ግባቸው ሌሎችን ዓላማ ያደረጉ ሰዎች የቀሰቀሷቸው ናቸው። ነገር ግን መንግሥታት እነዚህ እኩይ ዓላማ ያነገቡ ሰዎች መነሻ በማድረግ ሰዎችን ሁሉ እንደ እኩይ፣ ሕግንም እንደመቅጫ መሣሪያ አድርገው ይጠቀሙበታል።

አሁንም ፍራቻዬ፣ ካለፉት መንግሥታት ስህተት ተምሬያለሁ የሚለው አዲሱ የኢትዮጵያ መንግሥት በእነዚህ ሰበብ አስባቦች ወደ ለየለት አምባገነንነት እንዳይለወጥ ነው። ከላይ እንደጠቀስኳት ሴት ያሉትም በየዋሕነት ለዚህ ዓይነቱ የመንግሥት ውሳኔ ግብዓት የሚሆን ግፊት ያደርጋሉ። ለዚህም ነው በርካቶች በማኅበራዊ ሚዲያ ሳይቀር መንግሥት አምባገነናዊ እርምጃ እንዲወስድ እስከመምከር የሚቃጣቸው።

ምን ይበጃል?
የነጻነት እና ስርዓትን ሚዛን ጠብቆ የሚጓዝ ስርዓት ለመመሥረት ቀላል ጊዜ እና ጥረት አይጠይቅም። በመንግሥት ኀይሎች ብቻ የሚሳካ ነገርም አይደለም። የዜጎችንም ቁርጠኝነት ይጠይቃል። የፖለቲካ ቡድኖችንም ሰናይ ትብብር ይጠይቃል። ብዙ ጊዜ ገዢ የፖለቲካ ድርጅቶች እንጂ ተቃዋሚዎች ለሰዎች ነጻነት እና ስርዓት ታማኝ ይመስላሉ። አሁን ግን በኢትዮጵያ የኀይል ሚዛኑ ስለተዛባ ተቃዋሚ የሚባሉት ድርጅቶችም የኀይል አቅማቸውን እያሳዩ እና የሌሎችን ነጻነት ከመግፈፍም አልፈው ስርዓት አልበኝነትን እያሰፈኑ ነው። ይህ ሊቀረፍ የሚችለው በመጀመሪያ የሕግ የበላይነትን በማስከበር ነው። ይህ ብዙ ተብሏል፤ ሆኖም ቅድመ ሁኔታው እምብዛም አልተነገረለትም።

የሕግ የበላይነት “ቅቡልነት ያለው የኀይል የበላይነት” ይጠይቃል። አዲሱ የኢትዮጵያ ገዢ ቡድን ከሞላ ጎደል ቅቡልነትም ይሁን የኀይል የበላይነት አለው። ነገር ግን ኹለቱንም በአግባቡ መጠቀም ባለመቻሉ ምክንያት እያጣቸው ይገኛል። ቅቡልነቱን በሐቀኝነት እና በግልጽነት ሥራውን በመሥራት ማስጠበቅ ሲኖርበት የገዢ ፓርቲነቱን ሚና ተጠቅሞ ተቀናቃኞቹን ለማዳከሚያነት በማዋሉ እየተሸረሸረበት ነው። የኀይል የበላይነቱን ደግሞ እውነተኛ አጥፊዎችን ለሕግ ለማቅረብ ዳተኛ በመሆን እና አጥፊዎቹ ቀስ በቀስ ትይዩ ኀይል ሲገነቡ በዝምታ በማለፍ እያፈረሰው ነው። እነዚህ አካሔዶች በአስቸኳይ ካልታረሙ በስተቀር ሕዝብ የሚናፍቃቸው ነጻነት እና ስርዓት እንደተናፈቁ መቅረታቸው ነው። የለውጥ ሒደቱም ወደ ኋላ ብዙ ርቀት ሊመለስ ይችላል።

በፍቃዱ ኃይሉ የሰብኣዊ መብቶች ተሟጋች እና ጸሐፊ ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው befeqe@yahoo.com ሊገኙ ይችላሉ።

LEAVE A REPLY