የነዚህ አባቶች ሁኔታ ያስደምማል! || ሞሐመድ አሊ ሞሐመድ

የነዚህ አባቶች ሁኔታ ያስደምማል! || ሞሐመድ አሊ ሞሐመድ

ስለክርስትናም ሆነ ስለእስልምና እምነቶች; ከነዚህ አባቶች የተሻለ ዕውቀት; ቅርበት; ተቆርቋሪነትና የኃላፊነት ስሜት ሊኖረው የሚችለው ማነው? እነዚህ በዕድሜም አንጋፋና ቀደምትነት ያላቸው የእምነት አባቶች; በውስጣቸው ብዙ ሀገራዊ እውነት መኖሩን መገመት አይከብድም፡፡ ከነዚህ አባቶች ሁኔታ መረዳት የሚቻለው በኢትዮጵያ በእስልምና እና በክርስትና እምነቶች ተከታዮች መካከል ያን ያህል ሥር የሰደደ ጥላቻ; የጠላትነትና የበቀል ስሜት አለመኖሩን ነው፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ እነዚህ አባቶች እንዲህ ተቀራርበው መንሾካሾክ ባልቻሉና አንዳቸው ለሌላቸው ጆሯቸውን ባልሰጡ ነበር፡፡

በሀገራችን ችግር ነበር ከተባለ የፖለቲካ ሥርዓት እንጅ በህዝብ መካከል አልነበረም፡፡ የፖለቲካ ሥርዓት ደግሞ ከገዥዎች ጋር መጥቶ የሚሄድ ነው፡፡ ይሁንና በአንድ በኩል ያለፈው ሥርዓት እንዲመለስ የሚመኙ; በሌላ በኩል ያ ሥርዓት እንዳይመለስ ሥጋት ያላቸው ወገኖች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ግን በዚህ ዘመን ያን ሥርዓት ሊያስተናግድ የሚችል አውድ እንደሌለ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

ተጨባጩ እውነታ ይኸው ሆኖ ሳለ; አሁን ሀገራችን ለብልቦ እንዲፈጃት ታስቦ የተለኮሰው እሳት ሰው ሠራሽና የአደገኛ ሴራ ማሳያ ነው፡፡ የክርስትና እምነትን ዒላማ አድርገው የሚንቀሳቀሱ; አብያተ-ክርስቲያናትን የሚያቃጥሉ; የእምነት አባቶችን በአሰቃቂ ሁኔታ በድንጋይ ቀጥቅጠውና በገጀራ ቆራርጠው የሚገድሉ; የሴቶችን ጡትና የወንዶችን ብልት ቆርጠው በአፍ በማጉረስ ለሰብኣዊነት ተቃራኒ የሆነ ዘግናኝ ድርጊት የሚፈፅሙ; የሀገርን ሀብትና ንብረት የሚያወድሙ; ሰላማዊ ዜጎችን የሚያሸብሩና ከመኖሪያ አካባቢያቸው በግፍ የሚያፈናቅሉ አረመኔዎች መላውን ሙስሊም ማህበረሰብ የሚወክሉ አይደሉም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አስነዋሪ ድርጊት የእምነቱ አስተምህሮ የሚፈቅደውና የእስላማዊ ሥነ-ምግባር መገለጫ አይደለም፡፡

በሌላ በኩል ሙስሊሞችን እንደመጤና ለሀገር ደህንነት እንደሆኑ በመቁጠር በተለያዬ ሥልትና መንገድ ለማሸማቀቅ የሚሞክሩ; በማያገባቸው ገብተው የእስልምና አማኞችን ዋህብይ/ሰለፍይ እያሉ የሚከፋፍሉና አንዱን ወገን ነጥለው በጠላትነት የሚፈርጁ; መስጊዶችንና የአላህ ቃል የሆነውን ቁርኣንን የሚያቃጥሉ; ሙስሊሞችን የሚገድሉና የአስፈሪ ጦርነት ነጋሪት የሚጎስሙ ወገኖች መላውን ህዝበ-ክርስቲያን የሚወክሉ አይደሉም፡፡ የሃይማኖቱ መሠረታዊ መርህና ቀኖናም ይህን የሚፈቅድና የሚያበረታታ አይደለም፡፡

ነገሩ ወዲህ ነው ወገኔ!
አጀንዳው ሌላ ነው፡፡ ዓላማው ለዘመናት በአንድነትና በሰላም የኖረውን እርስ በርስ ማባላትና አብሮ መኖር የማይቻልበትን ሁኔታ መፍጠር ነው፡፡ ባለፈው ግማሽ ምዕተ-ዓመት ብሔርተኝነትን በማቀንቀን ብቻ ማሳካት ያልቻሉትን የህዝብን አንድነትና ሀገር የመበተን ተልዕኮ ከዳር ለማድረስ የሃይማኖት ልዩነትን ሁነኛ መሣሪያ የማድረግ ስትራቴጂን ተከትለዋል፡፡ በዚህ እሳቤም እስካሁን በስፋት ሲያርከፈክፉት በቆዩት የብሔርተኝነት ቤንዚን ላይ የሃይማኖት አጀንዳን እንደክብሪት በመጫር ሀገርን ብው አድርገው በማንደድ ዶግ አመድ ለማድረግ ሲሞክሩ የታሪክ እማኝ ለመሆን ተረግመን ሊሆን ይችላል፡፡ ከእርግማኑ ባለፈም ከዚህ ማንም ሊያተርፍ እንደማይችል እየታወቀ “ዐይኔን ግንባር ያድርገው” ብለን ለምን ወደገደሉ እንደምናመራ ግራ አጋቢና; አስፈሪም ነው፡፡

እናስ ምን ተሻለን?
የሚሻለን ፊታችንን ወደየቤተ-እምነቶቻችን ማዞር ነው፡፡ የተሻለው አማራጭ የእምነት አባቶቻችንን ምክርና ተግሳፅ መስማት ነው፡፡ ምናልባትም “ይቅር በለን” ብለን ወደ ፈጣሪ አምላክ ማንጋጠጥና; በየልቦናችን እውነተኛ ፈሪሃ-እግዚአብሔር መኖሩንም ማረጋገጥ ሊኖርብን ይችላል፡፡ የምር ፈሪሃ-እግዚአብሔር/አላህ ካለን; በየትኛውም እምነት ቢሆን ፈጣሪ-አምላክ ከፍጥረታት ሁሉ አልቆ የፈጠረውን የሰው ልጅ በአሰቃቂ ሁኔታ መግደልና ተመሳሳይ ግፎችን መፈፀም ውግዝ መሆኑ የሚያግባባ ሳይሆን አይቀርም፡፡

ልብ እንበል;
ይህች ምድር ለሁላችንም የተፈጠረችና በቂ; ግን ደግሞ እኛ ትተናት የምናልፍና ቀሪ መሆኗን; ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለቀጣዩ ትውልድም በኃላፊነት ስሜት ማሰብ እንዳለብን; ለልጅ-ልጆቻችን ፍቅርን; አብሮነትንና የተሻለ ነገን ማውረስ እንዳለብን ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ከዚህ በተቃራኒው የመሰሪዎች አጀንዳ ሰለባ መሆንና በጥፋት መንገድ መንጎድ ከሰውነት ከፍታ ወደ አውሬነት ተርታ ወርዶ መፈጥፈጥ ነው፡፡

ሰው መሆን ታላቅነት ነው፡፡ ሰውነት መሆን ክቡር ፀጋ ነው፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ማሰብም ሆነ ቁሞ መገኘት ከፈጣሪ ዓላማና ፈቃድ ማፈንገጥና አጉል አመፀኝነት ነው፡፡ ስለሆነም በዚህኛውም ሆነ በወዲያኛው ዓለም ቅጣቱ የከፋ ይሆናል፡፡ ግን ደግሞ “ለሃጢያን የመጣ ለፃድቃን ይተርፋል” እንዲሉ ነውና ፈጣሪ-አምላክ ከቁጣውና ከማኣቱ ይጠብቀን!!!

LEAVE A REPLY