ንቀን ያለፍነው ቃል || በእውቀቱ ስዩም

ንቀን ያለፍነው ቃል || በእውቀቱ ስዩም

 

ከለታት አንድ ቀን፤ ወደ ቤቷ ሄድኩኝ;
ጥቅል ጎመን አርዳ ፤ እንጉዳዩን ጠብሳ
ጋበዘችኝ ምሳ
ሙያዋን አደነቅሁ
ገበታው ሲነሳ
ካያቷ ተዋወቅሁ፤

አረጋዊት ናቸው፤ እድሚያቸው የገፋ
ድሮ ልጅ እያሉ፤ ዐይናቼው የጠፋ
በድሚያቸው በረካ፤ በፅዋቸው ጭላጭ
አምሯቸው ብሩህ፤ ልሳናቸው ምላጭ
ወግ ማውጋት ጀመሩ
ቃል እያለዘቡ
ቃል እየጠረቡ- ቃል እያሳመሩ
ሀረግ አለዝበው፤ ዘይቤ እየነቀሱ
በፀጥታ ሞቶ ፤ያላጀብ ተቅብሮ
የተረሳ ታሪክ እየቀሰቀሱ፤
እንደ መቅረፀ፤ ድምፅ ጆሮየን ጠመድሁት
አጥብቆ ገረመኝ
ያረጋዊቷ ወግ፤ ቅድም ከበላሁት-
ክንጉዳዩ ዝልዝል፤ የበለጠ ጣመኝ፤

ፀሃፌ ትዛዛት ፤ቸል ብለው ያለፉት
ዜና ነጋሪዎች፤ አይተው የገደፉት
ያገሬን ሰው ገድል፤ መከራ ፍስሃ
ሳልታክት ቀዳሁት፤ ልክ እንዳርብ ውሃ

ከጥሞናየ ላይ ላፍታ ተፋትቼ
ጋባዤን ፈለግሗት
ፊትለፊቴ አየሗት
ያቻት ያቻትና
ከሶፋው ላይ ሆና
እግሮቿን ዝርግትግት ሰውነቷን ዘና
እንደፊት መስተዋት
ዘመናይ ሞባይሏን: ፊቷ ስር ደቅና

ከስልኳ ሰሌዳ፤ ፊደል ትነካለች
ፎቶ ታምሳለች ፤ኢሜል ትልካለች
ያያቷ ጣፋጭ ወግ ፤ላፍታ እንኳ መች ደንቋት
ሜሴንጀር -ዋትሰፕ -ኢሞ -ቴሌግራም
ሁሉን የወሬ ቋት
ትበረብራለች፤
……..

ካስር አመት በፊት
ለረፍት ከከተማ ፤ወደ ገጠር ሄጄ
ደጅ ላይ ማለዳ ፤ ፀሀይ ስር ተጥጄ
አያቴ ብቅ ብሎ
ከተቀመጥሁበት ፤የወይራ ግንድ ላይ ፤ራሱን አዳብሎ
“ያኔ ጎበዝ ሳለሁ” ብሎ ወግ ሲወጥን
አልባሌ ወሬ፤ እኔን የማይመጥን
የሰማሁ ይመስል ፤በሃይል አዛግቼ
ከካፖርቴ ኪስ ውስጥ ፤መፅሀፍ አውጥቼ
(የማርክስ ፤ የፍሮይድ ምናልባት የኒቼ?)
ገለብ ገለጥ ሳደርግ፤ እሱ ይህን አይቶ
የጀመረውን ቃል፤ አንጠልጥሎ ትቶ
“ ለጥናት ነው መሰል፤ እዚህ መቀመጥህ፤
ወግድልኝ በለኝ፤ እንዳልበጠብጥህ
ብሎ ይወገዳል
አድማጭ ካጣጭ ጋራ ወደሚገኝበት- ጠላ ቤት ይሄዳል፤

አያቴ ከሞተ አመታት አለፉ
ፀፀት ጭንቅላቴን በብረት መዳፉ
እየኮረኮመኝ
ሀፍረት በሸኮናው እየረመረመኝ
በራሴ ስበግን
ምን ሆኘ ነበር ግን
ምን ነክቶኝ ነበር ግን
በማለት አጥብቄ ራሴን ስረግም
ይሄውና ዛሬ
ጋባዤን አየሁዋት፤ ታሪኬን ስትደግም፤
አንድም በመሰልቸት፤ አንድም በቸልታ
ወይ ባወቅሁሽ ናቅሁሽ፤አለያም በወረት
የያዝነውን ዳቦ ፤ቆጥረነው ከኮረት
ጠላ ከሚጠጣ ፤ቆሎ ከሚበላ
እድፍ ከሚለብሰው
ለአይን ከማይሞላ
ካንድ ስም አልባ ሰው
ምን ጥበብ ይገኛል፤ በሚል ተዘናግተን
በቻይና ቅፅር ጡብ፤ ጆሮአችን ዘግተን
ልቦና ቆልፈን
ንቀን ያለፍነው ቃል፤ ንቆ ነው ያለፈን ፤

LEAVE A REPLY