ዝቅ ብሎ ሊያስታርቅ ለሚችል አባት ቦታ ሊሰጥ ይገባል || ታምሩ ገዳ

ዝቅ ብሎ ሊያስታርቅ ለሚችል አባት ቦታ ሊሰጥ ይገባል || ታምሩ ገዳ

ዛሬ አለማችንን እያወደመ እና እያባላን የሚገኘው የእኔ ልብለጥ ፣የእኔ ልብለጥ ፣ ሁሉን አዋቂነት ፣ልበ ደንዳናነት እና በንጹሃኖች ደም እና ህይወት የመንገድ ልክፍት ናቸው።

አንድ ታላቅ አባት(መሪ) እርቀ ሰላም አውርዱ ብሎ ሲማጸን የተናጋሪውን ያህል ለሰላም ከመ ቅርብ ይልቅ ፣የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር በሂዱበት መንገድ ዝንተ አለም መጓዝ በህዝብ ዘንድ ወንጀል ሲሆን በፈጣሪም ዘንድ ትልቅ ሐጢያት ነው።የብዙዎቻችን ትልቁ ችግርም እዚህ ላይ ነው።ሰለ ሰላም ይሰበካል፣ይጸለያል፣ይዘመራል፣ግጥሙ ይደረደራል፣ማስታወቂያው ይለፈፋል ፣ፖስተሩ ይለጠፋል፣ ስብሰባው ይንጋጋል…አረ ስንቱ ያልተደረገ እና የማይደረግ ነገር የለም።

ሰላም ምንም የሂሳብ ቀመር ፣የምሁራን ተብዮዎች ፍልስፍና እና ቀይ መስመር የሚያልፉ አክቲቪስት ተብዬዎች የቃላት ሽወዳ አያስፈልገውም። ሰላም እንደ ስያሚው ሁሌም ሰላም ነው። ታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ “ስለ እርቀ ሰላም ከልባቸው የሚያለቅሱ፣የሚማጸኑ ብጹአን ናቸው…እነርሱም ይማራሉና” እንደሚለው ሳይሆን ብዙዎቻችን እርቀ ሰላም እና ትሩፋቱን በብሔር፣በሀይማኖት፣በፖለቲካ አሰላለፋችን ጎራ በመክፈል “ወትሮስ ከእገሊት/ከእገሌ ምን ይጠበቃል ?” የሚለውን የጸረ ሰላም ግንብ በልባችን እና በአይምሯችን ውስጥ ቀድመን ለመገንባት ስንጣጣር እንስተዋላለን። በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ የጎረቤት አገራት ስደተኞች (ሶሪያዊያኖችን እና የመኖችን ጨምሮ) መጠጊያ የሆነችው ኢትዮጵያ የራሷን ልጆች ከሰው ተኩላዎች መታደግ ተሳናት። እንሆ አንጻራዊ ሰላሙም እንደ መብራት እና እንደ ውሀ በፈረቃ መታደል ከተጀመረ ተስነበተ።

በዘመኑ የስልጣን ጥመኞች እና ጉልቤዎች ሳቢይ ሰሞኑን ከሰማኒያ በላይ ምስኪን ዜጎች ህይወታቸው እንደቀልድ ይተቀጠፋባት ፣ለስደት የተዳረጉባት ኢትዮጵያን እና ልጆቿን በጸሎት ያሰቡት፣ከአንድ ቢሊዮን በላይ ተከታይ(ይቅርታ የፌስ ቡክ ተከታይ ማለት እንዳልሆነ ይሰመርበት ) ያላቸው የሮማ ካቶሊክ ቤ/ን አባት የሆኑት አቡነ ፍራንሲስ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ በርካታ ምሁራኖች እና አወቅን ባይ ልጆች እያልት፣ ነገር ግን በጎሳ ፖለቲካ እና በስልጣን ጥማት ሳቢይ ዜጎችን ለሞት እና ለስደት እየዳረገች የምትገኘው የጎረቤት ደ/ሱዳን መሪዎችን ባለፈው እኤአ የካቲት 2019 ለእርቀ ሰላም ጣሊያን ቫቲካን በመጋበዝ ፣እግራቸው ላይ በመውደቅ “ስለህዝባችሁ መከራ እና ሰቆቃ ስትሉ ታረቁ….ወዘተ” በማለት ሀይማኖታዊ ቆባቸውን ሳይቀር መሬት ላይ ጣል አድርገው ተማጽነዋቸው ነበር።

ሁኔታውን የታዘበ እና ከደ/ሱዳን ተቃዋሚዎች ዋንኛ የሆኑትን ዶክተር ሬክ መቻርን በቅርበት የሚያውቃቸው አንድ የምእራባዊያን ጋዜጠኛ”ሬክ ማቻር ምንም እንኳን በፍልስፍና እና በእቅድ ጥናት(Philosophy and Strategic planning) የዶክትሬት ማእረግ ቢኖራቸውም እስከ ማውቃቸው ድረስ ልባቸው ከብረት የጠነከረ በመሆኑ እኔ በበኩሌ የእርሳቸውን እግር ለመሳም ትዕግስቱ የለኝም ።አቡኑ ግን መንፈሳዊ ሃላፊነታቸው በመሆኑ ብዙ ሀጢያተኞችን ወደ ጽድቀት ለማምጣት ብዙ ስራ ስለሚጠይቃቸው ወድቀው ለመማጸን ተገደዱ ።” ሲል አንዳንድ ጦርነት ናፋቂ መሪዎች እንዴት አስቸጋሪዎች እንደሆኑ ትዝብቱን አስፍሯል።

በኢትዮጵያ የሰላም እና የእርቅ ኮሚሽን ዋና ስብሳቢ የሆኑት ካርዲናል ብርሀን እየሱስ ሱራፌል ሰሞኑን ከተለያዩ የከካቶሊክ ቤ/ን ነክ ከሆኑ ድህረ ገጾች ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ” እኔ ይብጹነታቸው ትንሽ ስሆን ለእርቀ ሰላም ሲባል ዝቅ ብዬ እግር ለመሳም እሞክራለሁ። ከተደፋሁበት መነሳቴን ግን ፈጣሪ ይወቀው ። “በማለት ለእርቀ ሰላም ሲባል ማጎንበስ ለሰማኒያ ሁለት አመቱ ፖፕ ፍራንሲስ አይደለም ለሰባ አንድ አመቱ ብርሀን እየሱስ ከባድ እንደሆነ በቀልድ መልክ ተናግረዋል።

በመቀጠልም ካርዲናል ብርሃነ እየሱስ አቡነ ፍራንሲስ የደ/ ሱዳን ፖለቲከኞች እግሮችን ለመሳም ከመሬት የመውደቃቸው ምስጢርን ሲዘረዝሩ ” በእናንተ የስልጣን እና የሀብት ጥማተኝነት ሳቢያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህጻናት፣እናቶች፣አዛውንቶች ሞተዋል፣ተሰደዋል።ለዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ ዋንኛ ተጠያቂዎቹ እናንተ ብቻ ስለ ሆናችሁ ወደ ልቦናችሁ እና ወደ ህሊናችሁ ተመለሱ ለማለት የተጠቀሙበት ብልሃት ነው።”ብለውታል።

በኢትዮጵያ ውስጥም ቢሆን በስልጣን ፣በጊዜያዊ ዝና እና በጎሰኝነት ስሜት በታወሩ የፖለቲካ መሪዎች እና አክቲቪስት ነን ባዮች የተነሳ ብዛት ያላቸው ወገኖች ህይወታቸውን ገብረዋል፣ በሚሊዮኖች የተቆጠሩ ህጻናት ሴቶች እና አዛውንቶች የአገር ውስጥ ስደተኛ ለመሆን ተገደዋል።

እነዚህ ከቀይ ምንጣፍ፣ከተሽከርካሪ ወንበር፣ከልዪ ጥበቃ ፣ከዘመናዊ ቤት እና መኪናዎች ውጪ በአይናቸው እና በአይምሯቸው ውስጥ የዜጎች መሞት፣መሰደድ እና የሰላም ዋጋ ዝር የማይልባቸው የዘመናችን ቁጭበሉዎችን ገመናቸውን በጉልበት እና ብግጭት ሳይሆን በሰለጠነ መንገድ ሊያጋልጡ፣እርቃናቸውን ሊያስቀሩ እና ደጋፊዎቻቸውንም ከጭልምት አለም ነጻ ሊያወጡ የሚችሉ ብልሀተኛ እና ቆራጥ የሆኑ ነገር አዋቂ ዎች መድረኩ ሊሰጣቸው፣ ሰላም ወዳድ ህዝቡም ውጥናቸውን ሊደግፍላቸው ይገባል።

LEAVE A REPLY