የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ህዳር 2 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ህዳር 2 ቀን 2011 ዓ.ም

ኒኩሌር (አቶሚክ ጨረር) ለጤፍ ምርት ማሻሻያ ጥቅም ላይ ዋለ

በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዮት የደብረ ዘይት የእርሻ ምርምር ተቋም ውስጥ ሦስት ዓመት ሙሉ ሲደረግ የነበረው አቶሚክ ጨረርን በመጠቀም የጤፍ ምርጥ ዘርን የማሻሻል ምርምር የላቦራቶሪ ሙከራውን በተሳካ መልኩ ተጠናቆ የመስክ ላይ ሙከራ መጀመሩ ታወቀ::

አራት ባለሙያዎችን ያቀፈውና በዶ/ር ሰሎሞን ጫንያለው የሚመራው ቡድን በኢትዮጵያ መንግሥት ሙሉ የፋይናንስ ድጋፍ በሚደረግለት በዚህ ምርምር የኒኩሌር ጨረርን በመጠቀም የጤፉን ዘረመን በማሻሻል የተሻለ ዘርን ለማግኘት ተስፋ ሰጪ ምልክቶች መታየታቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ::

በቁመቱ አጭር የሆነ እንዲሁም በአጭር ጊዜ ውስጥ በመድረስ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ምርጥ ዘር ለማግኘት የተለያየ መጠን ያለው የኒኩሌር ጨረርን በመጠቀም ሙከራ እየተደረገ መሆኑን ተማራማሪዎቹ ይናገራሉ:: “ከተለያዮ ዝርያዎች የተወሰዱ የጤፍ ዝርያዎች ላይ የተለያየ የጨረር መጠንን በመጠቀም የጤፉን ዘረመን በማሻሻል ከፍተኛ የፕሮቲን መጠን ያለው ፣ በጥቂት ውሃ በአጭር ጊዜ የሚደርስ ሰብል ለማምረት የሚያስችሉ ምልክቶችን ተመልክተናል” ብለዋል-ባለሙያዎቹ::

በተያዘው ዓመት ምርቱን ወደ መስክ ወስደነዋል የሚሉት ተመራማሪዎች የጤፍ ተክል ቁመቱ ሲረዝም የመውደቅ አደጋ አዝማሚያ ስለሚኖረው የምርታማነት አቅሙ የሚቀነስ ሲሆን በቁመቱ ያጠረ እና በአጭር ጊዜ የሚደርስ ዝርያን በመፍጠር ድርቅን የሚቋቋም ምርት እናገኛለን ብለን እምናለን ሲሉ ተናግረዋል::

ቀደም ባሉት ጊዜያት የተለያዮ ኬሚካሎችን በመጠቀም ምርጥ ዘሮችን ሲያዘጋጅ የቆየው ተቋሙ የኒኩሌር ቴክኖሎጂን በመጠቀም ተመሳሳይ ጥናት ሲያካሂድ የመጀመሪያው ነው:: በኢትዮጵያ ውስጥ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በጤፍ ምርት የሚለማ ሲሆን በየዓመቱ ስድስት ሚሊዮን አርሶ አደሮች ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሏል::

ተመራማሪዎቹ ከኤክስ ሬይ ጋር ሲነፃፀር ከ10 እስከ 100 ሚሊዮን እጥፍ የሚበልጥ ጨረርን እንደሚጠቀሙ  ታውቋል:: ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ተቋምም ለጥናቱ የቴክኒክና የስልጠና ድጋፎችን ከማድረግ ባሻገር የጥንቃቄ እርምጃ ላይ ድጋፍ እንደሰጠ በይፋ አረጋግጧል::

በአዲስ አበባ 1.7 ቢሊዮን ብር ብድር ያለ ዋስትና መሰጠቱ ታወቀ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2012 በጀት ዓመት ከመደበው የወጣቶች ብድር ፈንድ ውስጥ 1.7 ቢሊዮን ብሩን በስድስት ወር ውስጥ አከፋፍሏል:: ለብድሩ መያዣነትም የተመሰረቱት ኢንተርፕራይዞች ራሳቸው እንጂ የማስተማመኛ ንብረት እንዳልቀረበም ታውቋል::

አዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም ለሰባት ሺኅ ኢንተርፕራይዞች ብድሩን አከፋፍሏል:: በዚህ ብድር ውስጥ 21 ሺኅ ወጣቶች የተደራጁ ሲሆን በግንባታ ዘርፍና በአምራችነት ለተሰማሩ ዘርፎች ቅድሚያ ተሰጥቷል::

ወጣቶቹ የተበደሩትን ገንዘብ እንደተሰማሩበት የሥራ መስክ አዋጭነት ከአንድ ዓመት እስከ አራት ዓመታት በሚደርስ ጊዜ ውስጥ እንዲመልሱ ውል መግባታቸውም ታውቋል:: በአዲስ አበባ በሚገኙ በሁሉም ክፍለ ከተሞች እና ወረዳውች ለሚገኙ ወጣቶች ብድሩን ማቅረቡን አዲስ ብድርና ቁጠባ ገልጿል::

የሥራ እድል ፈጠራ እና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ በበኩሉ ወጣቶችን በማደራጀት ለሚሰማሩበት ሥራ ዘርፍ ሥልጠና በመስጠት እና በማማከር እየተሳተፈ ይገኛል::

አንዳንድ ኢንተርፕራይዞች ብድር ካገኙ በኋላ ወደ ሥራ ሳይገቡ እንደሚጠፉ እና ወደ ሥራ በሚገቡበት ወቅት የቤት ኪራይ አዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም መክፈሉን ተከትሎ ከሦስት እስከ ስድስት ወራት የሚሆን ገንዘብ በመቀበል እንደሚጠፉ በኤጀንሲው የኢንተርፕራይዞች ልማት ድጋፍና ክትትል ሓላፊ የሺጥላ ክፍሌ አስታውቀዋል::

በመጪዎቹ 2 ሳምንታት በኢትዮጵያ ወቅቱን ያልጠበቀ ከባድ ዝናብ ይኖራል ተባለ

በመጪዎቹ ሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ በኦሮሚያ ደቡብ ክልል ድሬደዋ ሶማሌ እና አማራ ክልሎች በአብዛኛው ከመደበኛ ጋር የተቀራረበ በጥቂቶች ደግሞ ከመደበኛው በላይ የሆነ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል የብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ ገለጸ:: ኤጀንሲው በዓለም ዐቀፍ ተቋማት የጎርፍ አደጋ ሊኖር ይችላል በሚል እየወጡ ያሉትን መረጃዎችን አስተባብሏል::

ዓለም ዐቀፉ የስደተኞች ተቆጣጣሪ ተቋም ባወጣው መረጃ በመጪዎቹ  ሳምንታት በኢትዮጵያ ኬንያና ሶማሊያ ከባድ ዝናብ እንደሚዘንብና አምስት መቶ ሺኅ ዜጎችን ካፈናቀለው የጥቅምት ወሩ አደጋ የባሰ ሊሆን ይችላል ሲል ተንብዮዋል:: በታሪክ ከፍተኛ ሆኖ በተመዘገበ ሙቀት ምክንያት በህንድ ውቅያኖስ ላይ ያጋጠሙ ለውጦች ከፍተኛ የዝናም መጠን እና መጥለቅለቅ ለአደጋው መከሰት እንደ ምክንያትነት ቀርቧል::

የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ በበኩሉ የአገሪቱ አብዛኛው ክፍሎች የበጋው ደረቃማ የአየር ሁኔታ ላይ ሆነው ይቆያሉ ብሏል:: ከኦሮሚያ ዞኖች በተለይም ምዕራብና ምሴራቅ ወለጋ ፣ ጅማ፣ ኢሉአባቦራ፣ አርሲ፣ ባሌ፣ ምሥራቅና ምዕራብ ሐረርጌን ጨምሮ የቦረና እና የጉጂ ዞኖች መደበኛ የዝናብ ስርጭት ይኖራቸዋል ያለው የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ ከድሬደዋና ሀረሪ በተጨማሪ የጋምቤላና የቤንሻኔጉል ጉሙዝ አንዳንድ አካባቢዎች የዝናብ ስርጭትያገኛሉ ሲል አረጋግጧል::

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የወላይታ፣ የዳውሮ፣ የጋሞ ጎፋ ፣ የከፋ የቤንች ማጂ፣ የደቡብ ኦሞ ፣ የጌዲኦ እና የሰገን አካባቢዎች የዝናብ ስርጭቱ ያገኛቸዋል የሚለው መረጃ በሶማሌ ክልል ደጋሀቡር ፣ ፊቅ፣ ቀብሪዳሃር፣ አፍዴር ፣ሉበን እና ጎዴም በዚህ ሂደት ውስጥ ተካታች መሆናቸውን አስታውቋል::

ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአነስተኛ ፋይናንስ ዘርፍ ላይ እንዲሠሩ ተፈቀደ

በገጠርም ሆነ በከተማ በሚደራጁ የአነስተኛ የፋይናንስ ሥራዎች ላይ የኢትዮጵያ ተወላጅ የሆኑ የውጭ ዜጎች እንዳይሳተፉ ይከለክል የነበረው አዋጅ ተሻሻለ::

እግዱን በማንሳት በዘርፉ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ በመፍቀድ በአገሪቱ ማኅበራዊና ምጣኔ ሀብት ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ በማሰብ አዋጁ እንደተሻሻለ ለማወቅ ተችሏል:: ትውልደ ኢትዮጵያውያን በባንክ ሥራ በመድኅን እና በአነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ድርሻ እንዳይኖራቸው ተከልክሎ የቆየ ሲሆን እነዚህን ህጎች የማሻሻል ሥራ ባሳለፍነው ሳምንት በፀደቁት ህጎች ተጠናቋል::

አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት በጥቃቅን እና አነስተኛ የሥራ መስኮች ላይ ብቻ ተገድበው እንዲቆዮና የሚሰጡት የብድር አገልግሎት ማደግ እንዳይችል አድርጎ ነበር:: ማሻሻያው በማንኛውም ምርታማ የሥራ መስክ ላይ መሳተፍ እንዲችሉ መብት የሰጠ ሆኗል::

በሥራ ላይ የዋለው አዋጅ የብድርና ቁጠባ ተቋማት በከተማ በግብርና ሥራ እና በሌሎች ሥራዎች ላይ እንዲሁም በጥቃቅን እና አነስተኛ የሥራ መስኮች ለተሰማሩ እንዲያበድሩ እና በተለይም በድህነት ቅነሳና በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ብቻ እንዲሰማሩ የገደበ ነበረ:: በተጨማሪም በዲጂታል ዘዴዎች የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት፣ ወኪል ባንኪንግ አገልግሎትና ከወለድ ነጻ አነስተኛ የፋይናንስ ሥራ አገልግሎት እንዲሰጡ ረቂቁ ፍቃድ ሰጥቷል::

ኮሪያ “ለኮሪያ ዘማች ኢትዮጵያውያን” ያስገነባችውን መኖሪያ ህንጻ ዛሬ አስረከበች

የደቡብ ኮሪያ መንግሥት ለኮሪያ ዘማች ኢትዮጵያውያን ያስገነባውን ባለ ሁለት ወለል መኖሪያ ህንጻ አስረከበ። መኖሪያ ህንጻው በደቡብ ኮሪያው ሎቴ ግሩፕ ድጋፍ አማካኝነት የተገነባ መሆኑን የሃገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር ገልጿል።

ህንጻው በፈረንጆቹ ከ1950 እስከ 53 በተደረገው የኮሪያ ጦርነት ወቅት ለዘመቱ ኢትዮጵያውያን ወታደሮች መኖሪያነት የሚያገለግል እንደሆነ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ተገልጿል። ኢትዮጵያ በኮሪያ ጦርነት ወቅት ከአፍሪካ ሃገራት ወደ ደቡብ ኮሪያ ወታደር ያዘመተች ብቸኛ ሃገር ስትሆን ፣ በጦርነቱም ከ120 በላይ ኢትዮጵያውያን ህይወታቸውን አጥተዋል።

ያኔ ከዘመቱት 3 ሺህ 500 ኢትዮጵያውያን መካከል አሁን ላይ ወደ 150ዎቹ በህይወት ይገኛሉ ያለው የኮርያ ዘማቾች ማኅበር ለባለዉለተኞቹ በደቡብ ኮርያ መንግሥት በኩል የተደረገው የመኖሪያ ህንጻ በእጅጉ እንዳስደሰተው አስታውቋል።

ለአቶ ገመቺስ ሞት የኢትዮ ቴሌኮምና መንግሥት ተጠያቂ መሆናቸውን ባለቤታቸው ገለጹ

የኢትዮ ቴሌኮም የምዕራብ ዞን ሓላፊ የነበሩት አቶ ገመቺስ ታደሰ በተደጋጋሚ ለኢትዮ ቴሌኮም የዝውውር ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ባለቤታቸው ወ/ሮ መሰረት ሁንዴሳ ተናገሩ።

አቶ ገመቺስ ከዓመት በፊት የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸው ነበር፤ ይህን ተከትሎም ለኢትዮ ቴሌኮም የዝውውር ጥያቄ አቅርበው ነበር። ወ/ሮ መሰረት ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ አቶ ገመቺስ የዝውውር ጥያቄያቸውን ለኢትዮ ቴሌኮም አቅርበው ከተቋሙ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋር እየተጻጻፉምነበር። ግለሰቡ ከኢትዮ ቴሌኮም ባገኙት ምላሽ ደስተኛ እንዳልነበሩ እና “የኢትዮ ቴሌኮም ሓላፊዎች ሕይወቱን ማዳን ይችሉ ነበር” ሲሉ ዕምነታቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የአቶ ገመቺስን ግድያ እየመረመረ ያለው ቡድን አንድ ሰው በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የገለጸ ሲሆን አቶ ገመቺስ ጥቅምት 16 ቀን 2012 ዓ. ም. በነቀምቴ ከተማ ውስጥ ጨለለቁ በተባለ አካባቢ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው አቅራቢያ መገደላቸው ይታወሳል።

በእለቱ አቶ ገመቺስ ከጓደኞቻቸው ጋር ቤት ውስጥ ሳሉ ከምሽቱ 1 ሰዓት ገደማ ስልክ ተደውሎላቸው ነበር። “የደወለለት የሚያምነው ጓደኛው” ነበር የሚሉት ወ/ሮ መሰረት፤ አቶ ገመቺስ ስልክ ለማውራት ከቤት ከወጡ በኋላ የተኩስ ድምጽ እንደሰሙ ይናገራሉ። “የተኩስ ድምጽ ሰምተን ስንወጣ ገመቺስን መሬት ላይ ወድቆ አገኘሁት” ሲሉ የተከሰተውን ይገልጻሉ። ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ያዋለው ግለሰብ ለአቶ ገመቺስ ደውሎ የነበረው ሰው እንደሆነም አስታውቀዋል።

አቶ ገመቺስን ወደ ሆስፒታል እንደወሰዷቸው ተናግረው፤ “ሆስፒታል ከደረስን በኋላ በቂ አገልግሎት አልተደረገም” ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል። የነቀምቴ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ዳምጠው ጋረደው፤ አቶ ገመቺስ ሆስፒታል ከደረሱ በኋላ ከአንድ ደቂቃ ከ20 ሰከንድ በማይበልጥ ጊዜ ውስጥ ሕይወታቸው እንዳለፈ አስታውሰው፤ “በአጭር ጊዜ ተገቢው ህክምና ተደርጓል” በማለት ወቀሳውን አጣጥለዋል።

“ግራ እጁ ላይ ሁለት ጊዜ በጥይት ተመቷል። ትከሻው ላይም በጥይት ተመቶ በብብቱ በስተግራ በኩል ጥይቱ ወጥቷል” ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ታፋቸው አካባቢ ሁለት ቦታ መመታታቸውን እና ጥይቶቹ የገቡበት እና የወጡበት ቦታ ይታይ እንደነበረም በወቅቱ መናገራቸው አይዘነጋም።

ወ/ሮ መሰረት እንደሚሉት፤ አቶ ገመቺስ ሕዳር 5 ቀን 2011 ዓ. ም. ነቀምቴ ከተማ ውስጥ፣ ምሽት ላይ ‘አስክ’ በሚባል ትምህርት ቤት መኪናቸውን አቁመው ሲወጡ የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸው ነበር። “ያኔ ክስተቱን ለፖሊስ ሪፖርት ብናደርግም ያገኘነው መፍትሔ አልነበረም” ካሉ በኋላ ከሁለት ሳምንት በፊት ከመገደላቸው አስቀድሞ ስጋት እንዳላቸው እንደገለጹም አስታውሰዋል።

ከግድያ ሙከራው በኋላም ለኢትዮ ቴሌኮም የዝውውር ጥያቄ ማቅረባቸውን እንዲሁም ሌላ ሥራ እያፈላለጉ እንደነበር የሚያስረዱት የሟች ባለቤት “ለኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስኪያጅ ፍሬሕይወት ታምሩ እዚህ መኖር ስጋት ውስጥ እንደጣለው ተናገሮ ነበር” ካሉ በኋላ ኢትዮ ቴሌኮም ቦታ እንፈልግልሀለን የሚል ምላሽ እንደሰጣቸው ገልጸዋል። ቦታ እንፈልግልሀለን ቢሉም ከቃል ባለፈ ሊሳካ ግንአልቻለም ይላሉ።

የኢትዮ ቴሌኮም ሥራ አስፈፃሚ ቢሮ ሓላፊ ወይዘሪት ጨረር አክሊሉ፤ አቶ ገመቺስ ዝውውር ጠይቀው እንደነበር አረጋግጠው፤ በምዕራብ ዞን ይሠሩበት ከነበረው አንድ ደረጃ ዝቅ ብለው፣ አዲስ አበባ እንዲሠሩ እንደተነገራቸው እና አቶ ገመቺስ ግን እንዳልፈለጉ ገልጸዋል።

“ጥያቄውን ከአንድ ዓመት በፊት አቅርበው ነበር። እሳቸው የጠየቁት ቦታ እስኪገኝ አዲስ አበባ በሌላ ቦታ እንዲሠሩ ሥራ አስኪያጇ ፈቅደው ነበር። ውሳኔውን ግን  አልተቀበሉም”ሲሉም የኢትዮ ቴሌኮም ሥራ አስፈጻሚ  ጠቁመዋል::አቶ ገመቺስ በተደጋጋሚ የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸው ለምን ነቀምቴ ውስጥ ቆዩ? ለሚለው ጥያቄባለቤታቸው ጠይቀን፤ “በሁኔታዎች ተገዶ እንጂ ወዶ አልቆየም” ሲሉ ይከራከራሉ።

የሁለት ልጆች አባት የነበሩት አቶ ገመቺስ፤ በኢትዮ ቴሌኮም ለአሥር ዓመታት ሠርተዋል። ወ/ሮ መሰርት “መንግሥት ችግሩን አይቶ ቢፈታ ኖሮ የገመቺስ ልጆች አባት አልባ አይሆኑም ነበር” በማለት ለግለሰቡ ሕልፈተ ህይወት የኢትዮ ቴሌኮም ሓላፊዎችን ተጠያቂ አድርገዋል።

ዮኔስኮ ለሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የሚውል ገንዘብ በስጦታ አበረከተ

የዓለም አቀፉ የሳይንስ፣ የትምህርት እና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ልማት የሚውል 74 ሺህ የአሜሪካን ዶላር መመደቡን የፓርኩ ጽሕፈት ቤት ገለጸ።

ባለፈው ዓመት ብሔራዊ ፓርኩ የእሳት ቃጠሎ ከደረሰበት የፓርኩ አካል መካከል 65 በመቶው ሳር ስለነበር በፍጥነት ማገገሙም እየተነገረ ነው፡፡ በተለይም ሳር በል ለሆኑ የፓርኩ እንስሳት ምቹ የሳር መኖ መውጣቱን ነው የሰሜን ተራሮዎች ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበባው አዛናው ያመላከቱት።

የደረሰው የእሳት ቃጠሎ የከፋ የሚባል አሉታዊ ተጽዕኖ አላሳደረም፤ ድርጊቱ ባልታወቀ መንገድ የተፈጸመ እና ሳይንሳዊ መንገዱን ያልተከተለ መሆኑ እንጂ ቃጠሎ በሳይንሳዊ መልኩ እንደሚመከር ያስታወሱት ሓላፊ ፤ተፈጥሮ የነበረው ችግር ዳግም እንዳይፈጠር የሕዝቡን የመልካም አስተዳድር ችግሮች አስቀድሞ ለመፍታት፣ ማኅበረሰቡን በልማት እና በአካባቢጥበቃ ለማሳተፍ፣ የአካባቢውን የፀጥታ አካላት ከፓርኩ ስካውቶች ጋር በማገናኘት በየቀጠናው ጥብቅ የቁጥጥር ሥራ ለማከናወን በትኩረት እንደሚሠራም አስታውቀዋል።

ችግሩ በተደጋጋሚ የሚከሰትባቸውን ቦታ እና ጊዜ በመለየትም 24 ሰዓት ጠበቅ ያለ ቁጥጥር እንዲደረግ ይሠራል ያሉት አቶ አበባው፤ ዓለም አቀፉ የሳይንስ፣ የትምህርት እና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) ብሔራዊ ፓርኩን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማልማት እና ለመንከባከብ የሚያግዝ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉንም ጠቁመዋል።

ዩኔስኮ ለባለሙያዎች ስልጠና እና ለቁሳቁስ ማሟያ የሚሆን 74 ሺህ የአሜሪካን ዶላር እንደመደበና ባለሙያዎች የእሳት አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ ውጤታማ የመቆጣጠር ሥራ ማከናወን የሚያስችል ስልጠና በኬንያ መውሰዳቸውንም ገልጸዋል። የሰለጠኑት ባለሙያዎችም እስከ ሕዳር 20 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ በሀገሪቱ ከሚገኙ ብሔራዊ ፓርኮች ለተውጣጡ ባለሙያዎች የአሰልጣኞች ስልጠና በደባርቅ ከተማ ይሰጣሉ::

በተያያዘ ዜና በብሔራዊ ፓርኩ 38 ሺህ የሚጠጉ የተለያዩ ሀገር በቀል ችግኞች በክረምቱ ተተክለዋል፤ 25 ሺህ ሄክታር የፓርኩ መሬትም በችግኞች ተሸፍኗል መባሉ ተሰማ።

በችግኝ ተከላ ዘመቻውም የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር ጨምሮ የክልል እና የፌዴራል የመንግስት የሥራ ሓላፊዎች፣ ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ እና ሌሎችም አካላት ተሳትፈውበታል:: በአካባቢው ወጣቶች አማካይነት የማረም እና የመኮትኮት ስራ እየተከናወነ ያሉት ሓላፊ የተተከለው ችግኝ የጽድቀት መጠን እንዲጨምር ከዘርፉ ባለሙያ ጋር ለመሥራት መታሰቡንም አስታውቀዋል።

ከውጭ በመጡ ዶክተሮች በየካቲት 12 ሆስፒታል የአንገት ቀዶ ህክምና እየተሰጠ ነው

 በየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ከውጭ ሀገር በመጡና በትውልደ ኢትዮጵያውን በጎ ፍቃደኛ ሐኪሞች ከአንገት በላይ የቀዶ ህክምና አገልግሎት በዘመቻ መልክ መሰጠት ጀምሯል።

በየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ከአንገት በላይ ቀዶ ህክምና ታካሚዎች ቁጥር ከፍተኛ ከመሆኑና  ጋር ተያይዞ በሚፈጠረው የታካሚና ሐኪም ጥመርታ አለመመጣጠን ምክንያት ታካሚዎች ረዘም ላለ ጊዜ ለመቆየት ሲገደዱ ነበር።

ይህንን ችግር በተወሰነ መልኩ ለማቃለል ባለፉት ዓመታት የውጭ ሀገርና ትውልደ ኢትዮጵያውን የህክምና ባለሙያዎችወደ ሀገራችን እየመጡ ከአንገት በላይ የቀዶ ህክምና አገልግሎት በበጎ ፍቃድ በመስጠት፣ በዘርፉ በከፍተኛ ሁኔታ የሚስተዋለውን የታካሚዎች እንግልትና ቅሬታ በማስቀረት የላቀ አስተዋፅኦ ሲያደርጉ መቆየታቸው አይዘነጋም።

በዚህ መሰረትም በሆስፒታሉ ከአንገት በላይ ቀዶ ህክምና ለማድረግ ለረጅም ግዜ ሲጠባበቁ የቆዩ ታካሚዎችን ቁጥር ለመቀነስ ከስዊድን ሀገር የመጡ የውጭ ሀገርና ትውልደ ኢትዮጵያውን የህክምና ባለሙያዎች ከህዳር 1 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ እንደ አስፈላጊነቱ ለ 15 ቀን የሚቆይ ከአንገት በላይ ቀዶ ህክምና በዘመቻ መልክ እየተጡ ይገኛጨሉ።

በህክምና ዘመቻው እስከ 300 የሚደርሱ ታካሚዎች ቀዶ ህክምና ያገኛሉ ተብሎ የሚጠበቅ መሆኑን ከሆስፒታሉ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል። ዋዉይህም ሆስፒታሉ ያለበትን ከአንገት በላይ ቀዶ ህክምና ታካሚዎች ቁጥር በመቀነስና የተገልጋይ እርካታን ከመጨመር ባሻገር እጅግ ውስብስብ የሆኑ፣ ባሉት ባለሙዎችና የህክምና ቁሳቁሶች ማከም ያልተቻሉ ህመሞችን በማከም የዕቀውትና የልምድ ሽግግርን ተግባራዊ ያደርጋል። የበጎ አድራጎት ልዑካን ቡድኑም ባለፉት ዓመታት እንዳደረጉት እጅግ ጠቃሚ የሆኑ የቀዶ ህክምና ቁሳቁሶችን በእርዳታ መልክ አንደሚለግሱም ተሰምቷልጰ።

LEAVE A REPLY