የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ህዳር 5 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ህዳር 5 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ የውህደት ዝርዝር ጥናቱን በድምጽ ብልጫ አፀደቀ

በአብላጭ ድምፅ ከስምምነት የደረሰው ኢህአዴግ  የውህደቱን ጥናት ከኮሚቴው አባላት 6ቱ ተቃውመውታል።  ዝርዝሩን ኢ.ቢ.ሲ ዋቢ በመጥቀስ እንደሚከተለው ዘግቦታል።

ኮሚቴው በውህደቱ ማዕቀፍ ውሰጥ ትኩረት ሊደረግባቸው የሚገቡ ዋና ዋና ጉዳዮችን በስፋት እንስቶ መወያየየቱንም የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ ፍቃዱ ተሰማ በተለይ ለኢቲቪ ተናግረዋል::

በዚህም ህብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝም ተጠናክሮ በሚቀጥልበትና የራስ አስተዳደር በሚጎለብትበት ሁኔታ ላይ ኮሚቴው በዛሬው ስብሰባው ትኩረት ሰጥቶ በዝርዝር መወያየቱንም ገልፀዋል::

የቋንቋ ብዝሃነት ፣ የብሔር እና ሀገራዊ ማንነትን ሚዛኑን በጠበቀ መልክ እንዲጠናከር የሚሉት ጉዳዮችም በመድረኩ ላይ ምክክር ተደርጎባቸዋል ብለዋል አቶ ፍቃዱ::

በመሆኑም ሁሉንም ብሄር ብሔረሰቦች ያማከለ ፍትሃዊ ውክልና በአዲሱ ውህድ ፓርቲ ውጥስ እንድኖር በዝርዝር ተመክሮበታልም ብለዋል፡ ፡

በመጨረሻም የውህደቱን ጥናት ኮሚቴው በ6 ተቃውሞ በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል::

በነገው ዕለትም ለወደ ፊቱ ውህድ ፓርቲ በተቀረፀው ረቂቅ ፕሮግራም ላይ እንደሚወያይ አቶ ፍቃድ ተሰማ ለኢቲቪ ተናግረዋል::

256 የኦነግ ወታደሮች በፖሊስነት መመረቃቸው እያነጋገረ ነው

በትጥቅ ትግል ውስጥ ሰንብቶ በለውጡ ማግሥት ወደ ሃገር ቤት የገባው የኦነግ ታጣቂ ቡድን የነበሩ በርካታ ግለሰቦች ፖሊስ ሆነው መመደባቸው ከወዲሁ ግርምትን እየፈጠረ ነው::

በተለይም እነዚህ ታጣቂዎች በምዕራብ ወለጋ የተለያዮ ከተሞች ግጭት ሲፈጥሩና በህዝብና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲያደርሱ የከረሙ መሆናቸው መንግሥት ምን እየሠራ ነው የሚል ጥያቄን በዜጎች ዘንድ ፈጥሯል::

በአባ ገዳዎች ጥሪ ትጥቅ ፈተው በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ወደ ካፕም ከገቡት የኦነግ የቅርብ ወራት ተዋጊአባላት ውስጥ 256ቱ ናቸው የፖሊስነት ስልጠና ወስደው ተመረቁ የተባለው።

ከሰንቀሌ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ የተመረቁት የፖሊስ አባላቱ በካምፕ ቆይታቸው ህገ መንግስት እና የጦር መሳሪያ አጠቃቀምን ጨምሮ የፖሊስ ሳይንስ ስልጠናዎችን ወስደዋል ተብሏል::

የፖሊስነት ስልጠና ወስደው የተመረቁት አባላቱ ስነ ምግባርን በጠበቀ መልኩ የኀብረተሰቡን ሰላም ለማስጠበቅ አንደሚሰሩ ተናግረዋል:: በአሁኑ ወቅት ጫካ ውስጥ የሚገኙ ጓደኞቻቸውም በሰላማዊ መንገድለመታገል ትጥቅ ፈትተው እንዲገቡም ጥሪ አቅርበዋል።

የፓርቲ መበተን የወደፊት የአገሪቱን ዕጣ ፈንታ እንደማይወስን ገብሩ አሥራት ተናገሩ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በዛሬው ዕለት ስብሰባውን እያካሄደ ይገኛል። ኮሚቴው በሚያካሂደው ስብሰባ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ መክሮ የወደፊት አቅጣጫዎችን እንደሚያስቀምጥ የሚጠበቅ ሲሆን የውህደት ጉዳይ ዋነኛው አጀንዳ እንደሚሆንም እየተነገረ ነው።

ኢሕአዴግ ከግንባርነት ወደ ውህድ ፓርቲነት የሚያደርገው ጉዞ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ቢነሳም እውን ሆኖ አልታየም። የብሔር ድርጅቶች ግንባር የሆነው ኢሕአዴግ እውን ይዋሀዳል? የሚል ጥያቄ እየተነሳ ሲሆን፤ በቅርቡ ግንባሩ ከሕወሓት ውጪ ሊዋሀድ ይችል ይሆናል የሚል ጭምጭምታም ተነስቷል። በጉዳዩ ላይ የፖለቲካ ተንታኙ አደም ካሴ (ዶ/ር) እና የቀድሞው የሕወሓት ከፍተኛ አመራር አቶ ገብሩ አስራትን ቢቢሲ አነጋግሯቸዋል።

የኢሕአዴግ መዋሃድ ጫፍ የደረሰ ይመስላል የሚሉት የፖለቲካ ተንታኙ አደም ካሴ (ዶ/ር)፤ የኢሕአዴግ አባል የሆኑት ሦስቱ ፓርቲዎች አጽድቀውታል ተብሎ መወራቱ የሚያሳየው ውህደቱ የቀጠለ መሆኑን ነው ይላሉ። እንደ ፖለቲካ ተንታኙ ገለጻ ውህደቱን ሕወሓት ሲቃወመው ቢቆይም የሚቀር አይመስልም። ዶ/ር አደም፤ አንዳንድ ዝርዝር ጉዳዮችን አሁንም የማናውቅ መሆኑን በማንሳት፤ አዲሱን ውህድ ፓርቲ ጠለቅ ብሎ ለማየት ፈታኝ መሆኑን ያነሳሉ። የጋራ የሆነ ፕሮግራሙ ምን እንደሚመስል፣ በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ፓርቲዎቹ ምን እንደተስማሙ አለማወቃቸውን በመጥቀስ ስለ አዲሱ ውህድ ፓርቲ የሚኖረን ምስል ጎዶሎ እንደሆነና በተለይ ለኦዲፒም ሆነ ለአዴፓ መሠረታዊ የሚባሉና በግልጽ የሚታወቁ ጉዳዮች ላይ (እንደ አዲስ አበባ ያሉ) የወሰዷቸውን ውሳኔዎችን አልሰማንም ሲሉም ሃሳባቸውን ይገልጻሉ።

እንዲህ አይነት ሁለቱን ፓርቲዎች የሚያፋጥጡ ነገሮች ዘግይተው ሲሰሙ፤ በታችኛው አባላት ዘንድ ግርታና መከፋፈልን ሊፈጥር ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ። ውህደቱ ቢሳካ እና ኢሕአዴግ ከሕወሓት ውጪ ቢዋሀድ፤ አዲሱ ፓርቲ ከቁጥር እንዲሁም ከሌሎች ጉዳዮች አንጻር የሶማሊያና ሌሎች አጋር ተብለው የቆዮ ፓርቲዎች ስለሚቀላቀሉት ሊያካክሰው ይችላል ብለው ያምናሉ።

ከባድ ሊሆን የሚችለው፤ ሕወሓት በውህደቱ ውስጥ ካልተካተተ ከእርሱ ጋር የሚሠሩ ሌሎች ፓርቲዎችን መፈለግ ስለሚኖርበት ነው የሚሉት ዶክተር አደም፤ ሕወሓት በሃሳብ ወይንም በርዕዮተ ዓለም የሚመስሉትን የሚፈልግ ከሆነ፤ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ጎልተው የሚታዮትና በብሔር ፖለቲካ አስተሳሰብ አቋማቸው ከእርሱ ጋር የሚመስሉትን ኦነግ፣ አብንና ምናልባትም ኦፌኮ መሆናቸውን በምሳሌነት ይጠቅሳሉ።

እነዚህ ፓርቲዎች የብሔር ፖለቲካን መሰረት አድርገው የተደራጁ መሆናቸውና ጠንካራ ተገዳዳሪ መሆን ከሚችሉ ክልሎች መገኘታቸውን በመጥቀስ፤ ከድርጅቶቹ ጋር ለመሥራት ፍላጎት ሊኖር እንደሚችል ያላቸውን ቅድመ ግምት አስቀምጠው፤ በኦሮሚያም በአማራ ክልልም ከሕወሓት ጋር በሃሳብ የሚጣጣሙ ፓርቲዎች ቢኖሩም፤ ሁለቱም ክልሎች ላይ ያሉት ገዢ ፓርቲዎች ከክልላቸው ተቃዋሚዎች ጋር አብሮ ለመሥራት የመሰባሰብ አዝማሚያ ማሳየታቸው፤ ሕወሓት ግንባር የሚሆነው ፓርቲን እያሳነሰበት እንደሚሄድ አመላክተዋል።

ሕወሓት በሚቀጥሉት አምስት አስር ዓመታት በክልሉ ውስጥ ጠንክሮ ሊሄድ እንደሚችል የሚገልጹት ዶ/ር አደም፤ በሌላ ክልል ካሉ ፓርቲዎች ጋር በግንባር ለመሥራት ያለው ሁኔታ እንደሚታሰበው ቀላል አይሆንለትም በማለት “ሕወሓት ብቻውን የመሆን እድሉ ሰፊ ነው” ካሉ በኋላ፤ ከኢሕአዴግ ጋር ድርድር አድርጎ ለመቀጠል ወይም ከሌሎች ጋር በጋራ ለመሥራት ያለው ዕድል ፈታኝ ዳገት መሆኑን ተናግረዋል።

ሕወሓት በአገር ደረጃ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆኖ ለመቀጠል ትልልቅ ፓርቲዎች ውስጥ መግባት እንደሚጠበቅበት በማስታወስ፤ ያንን ከየትኛው ወገን፣ ግንባር፣ ጥምረት ጋር ሆኖ እንደሚያደርገው በሂደት ይታያል የሚሉት ዶክተር አደም”ሕወሓት በመግለጫ እንገነጠላለን ብሎ አያውቅም” ሲሉም ይከራከራሉ:: ካለው ሥርዓት አንጻር በክልል ደረጃ ያለውን ሥልጣን መጠየቁ መጥፎ አይደለም በማለትም አክለዋል።

በዚህ መካከል ግጭትና አለመግባባት ቢነሳ፤ አሁን ባለው የፌደራል ሥርዓት ውስጥ ግጭቶችን መፍቻ መንገድ የለም የሚሉት ዶ/ር አደም፤ ሁሉም በየክልሉ ‘ይኼ የኔ ነው፤ ይኼ የኔ ነው’ በሚልበት በአሁኑ ወቅት ግጭቶች እንደሚጠበቁ በማንሳት፤ በአሁኑ ሰዓት እንደ ቀድሞው ግጭቶቹን በፓርቲው በኩል የሚፈታ ሥርዓት አለመኖሩን በመጥቀስ ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል።

ከፓርቲው ውጪ ግጭቶችን መፍታት የሚያስችል የሕግ ሥርዓትን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን የሚናገሩት ፖለቲከኛው ዛሬ ሕወሓት አለኝ የሚለውን ቅሬታ ነገ ሌላ ክልል ሊያነሳው ስለሚችል፤ ዲሞክራሲያዊ አገር ለመገንባት ግጭቶችን መፍቻ መንገድ ማበጀት ይገባል ሲሉም ተናግረዋል::

“በኦሮሚያ ውስጥ ያለው ብሔርተኝነት ለዚህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ እርምጃ ትልቁ ፈተና ነው” ያሉት ዶ/ር አደም፤ በቀጣይ ምርጫ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን ላይ መቆየታቸውን ለማረጋገጥ፤ በክልላቸው ድጋፍ የማግኘት እድላቸው አጠራጣሪ በመሆኑ፤ ኢሕአዴግ ሲዋሃድ ከሌሎች አካባቢዎች በሚያገኙት ድምጽ እድላቸው ይሰፋል ብለዋል።

“ውህደቱ ከዐቢይ የሚያልፍ፣ በሀሳብ ላይ የተመሰረተ መሆን አለመሆኑ ላይ ጥያቄ አለን” በማለት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያየ ምክንያት በሥልጣን ባይቀጥሉ ውህደቱ ይቀጥላል ወይ? የሚለውን ለማየት፤ የአዲሱን ውህድ ፓርቲ ፕሮግራም ማየት አስፈላጊ መሆኑንም ይመክራሉ።

በሌላ በኩል የቀድሞው የሕወሓት ከፍተኛ አመራር አቶ ገብሩ አስራት፤ ስለ ውህደት ሲነሳ፤ የፓርቲዎች ሙሉ ስምምነት በሌለበት ሁኔታ ከሆነ በገዢ ፓርቲው ዘንድ ቀውስ እንዳለ አመላካች ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በእርግጥ በየትኛውም አገር የፓርቲ ግንባር ሊፈርስ፣ አዲስ ቅንጅት ሊፈጠር ይችላል ያሉት የቀድሞው ሕወሓት መሪ የአሁኑ የአረና አባል፤ ይህ ሂደት ወደ ኢትዮጵያ አውድ ሲመጣ አደጋ ሊያስከትል ይችላል ብለው ይገምታሉ።

“ኢትዮጵያ ውስጥ ገዢ ፓርቲ የመንግሥት መዋቅርን ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረ፣ ሕዝቡንም ለመቆጣጠር የሚሞክር ስለሆነ አንድ ፓርቲ ሲላላና ሲዳከም የሚፈጠሩ ችግሮች አሉ። ከአራቱ መስራች ድርጅቶች አንዱ ሕወሓት ከወጣ፣ [ውህደቱ] የተቀሩት ተወያይተው የተስማሙበት ካልሆነም ችግሩ ለሕዘብ የሚተርፍ ይሆናል። በኢትዮጵያ ፖለቲካ፤ ኢሕአዴግን ጨምሮ ፓርቲዎች የሚፎካከሩ ሳይሆኑ በጥቅም የተሳሰሩ እንዲሁም አንዱ ሌላውን እየጠለፈ የሚጥል” ነው ካሉ በኋላ እስካሁንም ገዢ ፓርቲው አለመስማማቱ፣ አንድ አለመሆኑ ኢትዮጵያን ብዙ ዋጋ እያስከፈላት ነው ሲሉአካሄዱን ይታቻሉ።

ኦቶ ገብሩ በመርህ ደረጃ ውህደትን እንደማይቃወሙና እንዲያውም ኢሕአዴግ ለውህደት ዘግይቷል ብለው እንደሚያስቡ ይናገራሉ። ሆኖም ግን በችኮላ፣ ለፓለቲካ ጨዋታ ሲባልና ስምምነት ሳይፈጠር መዋሀድ ዘላቂነት ይኖረዋል? ሲሉም ይጠይቃሉ። ኢሕአዴግ መዋሀድ ካለበት፤ የጋራ ፕሮግራም እና የጋራ ሕገ ደንብ መኖርን እንደ ቅድመ ሁኔታ ያስቀምጣሉ። ሕወሓት በውህደቱ አልሳተፍም ካለም መብቱ እንደሆነና ችግር እንደማይፈጠር እና ሆኖም ግን ጉዳዩ ችግር ሊያስከትል የሚችልባቸውን ሁለት አካሄዶች በተከታይነት ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ላይ ገልጸዋል።

“ቀሪዎቹ ሦስት ድርጅቶች እኔ ያልኩትን ብቻ፣ የኔን ርዕዮተ ዓለም ብቻ ተቀብለው ካልሆነ በስተቀር አልዋሀድም ከተባለ ስህተት ነው። ሁለተኛ፤ እኔ በዚህ ውህደት ከሌለሁ ትግራይም ትገነጠላለች የሚለው አካሄድም ስህተት ይመስለኛል።” ያሉት ገብሩ አሥራት፤ የፓርቲውን አለመስማማትና የሥልጣን ሽኩቻ ወደ ሕዝብ ወስዶ፣ እኔ እዚህ ሥልጣን መሀል ካልቆምኩ፤ ሕዝብም ይገነጠላል የሚለው አስተያየት የተሳሳተ እንደሆነ ጠቁመው ፤ ይህ ከምጣኔ ሀብት፣ ከደህንነት እንዲሁም ከዲፕሎማሲ አንጻርም ለትግራይ ሕዝብም ከፍተኛ ችግር የሚፈጥር ከመሆኑ ባሻገር ሕዝቡ ብዙ ታግሎ ያገኛቸውን ነገሮች የሚያሳጣ ነው ብለዋል።

“ሕወሓት ርዕዮተ ዓለሙን የማራመድ፣ ከመሰሉት ድርጅቶች ጋር የመጣመርም መብት አለው። ፓርቲ ሊበተን ይችላል፤ ይሄ ግን የአገርን እጣ ፈንታ መወሰን የለበትም። አገር ሊበተን ይችላል ማለትም አደገኛ ነው” በማለትአቋማቸውን የገለጹት የቀድሞው የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ፤ ውይይትና ድርድር ፈጽሞ እንደማይሆን ፣ከፓርቲ ወጥቶ አቋምን ማራመድ በፖለቲካ ያለ ቢሆንም፤ አሁን ላይ ሕወሓት እጅግ የተዳከመበት ሁኔታ ላይ ስላለየሚከተለውን ርዕዮተ ዓለም ይዞ ሕዝብን ያሰባስባል የሚል ዕምነት የለኝም ሲሉ አስታውቀዋል።

አንድ ፓርቲ ስለተሸነፈ፣ የፓርቲ አመራር ከሥልጣን ስለተወገደ የትግራይ ሕዝብ እድል በዛ መወሰን የለበትም የሚሉት አቶ ገብሩ፤ “መሰረቱ ሕዝብ ለሕዝብ አይጣላም፣ ሕዝብ ለሕዝብ አይዋጋም፣ ሕዝብ ለሕዝብ አይራራቅም” በማለት የኢትዮጵያውያን ተከባብሮ በአንድነት የመኖር መንፈስ ወደፊትም እንደሚቀጥል ጠቁመዋል::

እስክንድር ነጋ ዛሬ ምሽት ለአንድ ወር ቆይታ ወደ አሜሪካ አቅንቷል 

ጋዜጠኛና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ እስክንድር ነጋ ዛሬ (ቅዳሜ) ምሽት ወደ አሜሪካ ተጉዟል:: የባላደራው ምክር ቤት ሰብሳቢ ለአንድ ወር ብቻ አሜሪካን ሀገር እንደሚቆይና ከሠላሳ ቀናት በኋላ ኢትዮጵያ እንደሚመለስ ተናግሯል::

የኢትዮጲስ ጋዜጣ ባለቤትና በአዲስ አበባ ዙሪያ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኘው የባላደራው ምክር ቤት ሰብሳቢ እስክንድር ነጋ ወደ አሜሪካ የሚያደርገውን ጉዞ አስመልክቶ የሽኝትና የምስጋና ፕሮግራም በመኖሪያ ቤቱ ተዘጋጅቶለታል::

የአዲስ አበባ ወጣቶች በተለይም በፈረንሣይ ለጋሲዮን ልጆች ዋነኛ ተነሳሽነትና አስተባባሪነት የተዘጋጀው የሽኝት ፕሮግራም ዋነኛ ዓላማ ክቡር የሆነው ሕይወቱ ሳያሳሳው በአዲስ አበባ የባለቤትነት ጉዳይ ወሳኝ ነጥብ ይዞ በመነሳት ኅብረተሰቡን ከማነቃቃቱ ባሻገር የተደራጀና ሠላማዊ ትግል በተጠናከረ ሁኔታ እንዲካሄድ መሠረት በመጣሉ መሆኑን በእስክንድር ነጋ መኖሪያ ቤት ተገኝቶ የሽኝት ፕሮግራሙን የተከታተለው የኢትዮጵያ ነገ ሪፖርተር ዘግቧል::

በርካታ ወጣቶች “አዲስ አበባ ቤቴ” የሚል መልዕክት የሰፈረበት እና የእስክንድር ነጋና የምክትል ሰብሳቢው ኤርምያስ ለገሠ ፎቶ የታተመበት ቲሸርት ለብሰው የሽኝት ፕሮግራሙን ያደመቁ ሲሆን በዚህ መልክ ፕሮግራም ላዘጋጁለት ወጣቶች እስክንድር ነጋ ከፍ ያለ ምስጋና አቅርቦ ሠላማዊ ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል::

በምርጫው ቀን በሲዳማ ዞን ሥራና ትምህርት እንደማይኖር ተገለጸ

የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ በሚካሄድበት ቀን ፣ በዞኑ መደበኛ ሥራ እንደማይኖር የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

ህዝበ ውሳኔን እያስፈጸመ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለተለያዮ መገናኛ ብዙኃን በላከው መረጃየመራጮች ምዝገባ ሂደት በሁሉም ጣቢያዎች እየተጠናቀቀ መሆኑን ጠቁሞ፤ በዚህ መሰረትም የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ የፊታችን ረቡዕ ህዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም በተያዘለት የጊዜ ሠሌዳ መሰረት የድምጽ መስጠት ሂደቱ ይከናወናል ሲል አረጋግጧል።

የድምጽ መስጫ ቀኑ የሥራ ቀን ላይ በመዋሉ፣ በሂደቱ አፈጻጸም ቅልጥፍና ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር የሚችል መሆኑን ከግንዛቤ በማስገባት፣ በህዝበ ውሳኔው የተመዘገቡት ድምጽ ሰጪዎች በሥራ ሰሌዳቸው ምክንያት ድምጽ ለመስጠት እንዳይቸገሩ ፣ እንዲሁም እስከ አሁን በምንም ሁኔታ ያልደፈረሰውን የህዝበ ውሳኔውን ሂደት ሠላማዊነት ለማስቀጠል ሲባል በድምጽ መስጫው ዕለት በዞኑ መደበኛ ሥራ አይኖርም ተብሏል።

ምርጫ ቦርዱ ህዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም ሀዋሳ ከተማን ጨምሮ በሲዳማ ዞን ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ፣ ትምህርት ቤቶች ፣መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣እንዲሁም የንግድ ተቋማት ዝግ እንዲሆኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር በማድረግ ከውሳኔ ላይ መድረሱን ገልጿል።

በዚህ መሠረት በዞኑና በከተማ መስተዳደሩ የሚሠሩ ማንኛውም ተቋማት በምርጫና እና የፓለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ቁጥር 1162/2012 አንቀጽ 161 በተቀመጠው መሰረት ፤ ይህን ውሳኔ ለማስፈጸም እና ለመፈጸም የመተባበር ግዴታ ያለባቸው መሆኑን ከወዲሁ አውቀው ዝግጅት እንዲያደርጉ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስጠንቅቋል።

47 ነጥብ 4 ኪሎ ግራም ኮኬይን በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ተያዘ

በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የመንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናል፣ 47 ነጥብ 4 ኪሎ ግራም ኮኬይን ተብሎ የሚጠራ አደገኛ አደንዛዥ ዕፅ በቁጥጥር ስር ዋለ፡፡

አደንዛዥ ዕፁ በቁጥጥር ስር የዋለው ትናንት በጉምሩክ የኢንተለጀንስና ኮንትሮባንድ ክትትል መሪነት ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አመራርና ሠራተኞች ጋራ በቅንጅት በተሰራ ኦፕሬሽን መሆኑም ታውቋል። ከድርጊቱ ጋር በተያያዘም አምስት የብራዚል ዜግነት ያላቸው ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ተነግሯል።

ተጠርጣዎቹ በነበራቸው የሆቴል ቆይታ በእጅ በሚያዙ ሻንጣዎችና ቦርሳዎች፣ በድምሩ 47 ነጥብ 4 ኪ.ግ የኮኬይን አደንዛዥ ዕፅ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል ወደ ተለያዩ ሀገራት ለማዘዋወር ሲሞክሩ ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት ።

አደንዛዥ ዕፁን በማዘዋወር የተጠረጠሩት ግለሰቦች ከታች የሚከተሉት ናቸው፡-

1ኛ ዳያኔ ክሪስቲና ኮሬላንደሊማ፣ የፓስፖርት ቁጥር GA544267 ያላት ግለሰብ 7 ኪ.ግ ኮኬይን ከብራዚል ግሩ ኢንተርናሽናል ኤርፖርት በመነሳት ወደ ታይላንድ ባንኮክ ለማዘዋወር ስትሞክር፣

2ኛ ሉሴኔ ዳ ሲልፋኮስታ፣ የፓስፖርት ቁጥር GA480O98 ያላት ግለሰብ4ኪ.ግ ኮኬይን ከብራዚል ግሩ ኢንተርናሽናል ኤርፖርት በመነሳት ወደ ሩዋንዳ ኪጋሊ ለማዘዋወር ስትሞክር፣

3ኛ ማርሴላ ጊስላኔ ዳ ሲልፋ ሞደስቶ፣ የፓስፖርት ቁጥር GA318058 ያላት ግለሰብ4 ኪ.ግ ኮኬይን ከብራዚል ግሩ ኢንተርናሽናል ኤርፖርት በመነሳት ወደ ደቡብ አፍሪካ ጆሀንስበርግ ለማዘዋወር ስትሞክር፣

4ኛ ኢዝቅዔል ዳ ሲልቫ ሞሬራ፣ የፓስፖርት ቁጥር GA533118 ያለው ግለሰብ2 ኪ.ግ ኮኬይን ከብራዚል ግሩ ኢንተርናሽናል ኤርፖርት ወደ ሩዋንዳ ኪጋሊ ለማዘዋወር ሲሞክር፣

5ኛ ራይዛ ሲልቫ ኮሪያዶናሲሜንቶ የፓስፖርት ቁጥር GA375985 የያዘች ግለሰብ2 ኪ.ግ ኮኬይን ከብራዚል ግሩ ኢንተርናሽናል ኤርፖርት ወደ ሩዋንዳ ኪጋሊ ለማዘዋወር የሞከረች፡፡

የተያዘው አደንዛዥ ፅፅ ግምታዊ ዋጋው 109,040,000 ብር ሲሆን፥ ሁሉም መንገደኞች ከብራዚል ወደ አዲስ አበባ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር ኢቲ 507 የተጓጓዙ እንደነበሩ ይፋ ከሆነው መረጃ ለማወቅ ችለናል::

ተጠርጣሪዎቹን የያዘው አውሮፕላን ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ያርፍ የነበረው ከምሽቱ 12:45-1:00 ሰዓት ሲሆን ባልተለመደ መልኩ ዘግይቶ ሌሊት 5:55 ማረፉ ታውቋል።

በዚህ ምክንያት በጉምሩክ ኢንተለጀንስ ሠራተኞችም  ላይ ክትትል እየተደረገ እንደነበር እና ከ4:30 በኋላ ለብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የሰዓቱ ሽፍት አስተባባሪ መረጃውን በመለዋወጥ በቅንጅት የተሳካ ኦፕሬሽ መሠራቱን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታውቋል።

LEAVE A REPLY