የሕግ የበላይነት ዛሬ ካልተከበረ እልቂቱ ይቀጥላል || ዶ/ር አክሎግ ቢራራ

የሕግ የበላይነት ዛሬ ካልተከበረ እልቂቱ ይቀጥላል || ዶ/ር አክሎግ ቢራራ

እኔ በምኖርበት በአሜሪካ አገር ዲያስፖራ ተብልን የምንጠራው ሁሉ ግራ ተጋብተናል። መተማመን የለም። አገራችን እየጠፋች፤ ዘውግና ኃይማኖት ተኮር ጭካኔ፤ ግፍና በደል በግልጽ እየተካሄደ ለመሰብሰብ፤ በጋራ ለመጮህ፤ ወንጀለኞችን ለይቶ ለማውገዝ አልቻልንም። አብዛኛዎቻችን ዝምታን መርጠናል፤ አቋም ከመውሰድ ተቆጥበናል። ህሊናችን የሚያስገድደንን ከማድረግ ይልቅ “እከሌ ይቀየምብን ይሆናል” በሚል ስንኩል አመለካከት ተበክለናል።

ምንም ልንክደው የማንችለው ሃቅ አለ። ይኼውም፤ ብሄር ተኮሩን ሕገመንግሥትና የብሄር አጥር የሆነውን የክልል አስተዳደር ተገንና ደጀን በማድረግ በሰማንያ ስድስት ንጹህ ኢትዮጵያዊያን ላይ ግድያ ተፈጽሟል። ብሄርና ኃይማኖት ተኮሩ ጭካኔ በመሬት ላይ ሲፈጸም፤ ታዛዢና አጎብዳጅ አንሆንም ብለው ለወንድማማችነት፤ ለእውነተኛ ፍትህ፤ ለብሄራዊ አንድነት የቆሙም ዘውጋቸው ኦሮሞና ሌላ የሆኑ ንጽሃን ወገኖቻችን ተገድለዋል። ግፍ፤ ጭካኔ፤ እልቂት ዘውግ የማይለይ የወንጀለኞች ስራ እንደተፈጸመ በመሬት ላይ ታይቷል። ለዚህ መፍትሄው አብሮና ተባብሮ ጨካኞቹን ለፍርድ ማቅረብ ብቻ ነው። አዝጋሚነትና ቸልተኛነት በምንም አያዋጣንም።

“የፌደራሉ መንግሥት ነኝ” ብሎ ራሱን የሰየመው ኢህአዴግ፤ ሃላፊነት ይህን ተራ ውንብድና፤ ይህን ሕገወጥነት፤ ይህን ግፍና በደል፤ ይህን እልቂት፤ ይህን የኃብት ውድመት ወዘተ፤ በቸልተኛነት፤ በለዘብተኛነት፤ በመንፈሳዊ ፍልስፍና፤ ወንጀለኞችን በማባበል ለመፍታት እንደማይችል ተገንዝቦና አምኖ፤ እርምጃ መውሰድና ግዴታውን መወጣት ነው። ግዳዩ ለይደር የሚባል አይደለም። እርምጃ መወሰድ ያለበት አሁን እንጅ ኢትዮጵያ የመንን ከሆነች በኋላ አይደለም። የጠ/ሚንስትር ዶር ዐብይ የኢህአዴግ አመራር ታሪካዊ ግዴታ ሕግን ማስከበር እንጅ፤ ጨካኞችን ማባበልና ማስታመም ሊሆን አይችልም። ኢትዮጵያን ለመታደግና መላውን ንጹህ ዜጎቿን ከባሰ አደጋ ለመከላከል ከተፈለገ ቆራጠኛነት፤ ብልሃት፤ ወሳኝነትና የፌደራል ፖሊስ፤ የደህንነትና የኢንተልጀንስ፤ የመከላከያ፤ የፍርድ ተቋማትን በሙሉ በተቀነባበረ ደረጃ መጠቀም የወቅቱ ጥያቄ ነው። ይህ ካልተደረገ ሌላው ቀርቶ መንግሥትም ይገለበጣል። አገር ትፈርሳለች፤ እልቂት ይስፋፋል። የሞራል ብቃት አስፈላጊ መሆኑን እንደገና አሳስባለሁ።

ባለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ እንዳሳሰብኩት ሁሉ፤ ኢትዮጵያ የተከበበች አገር እየሆነች ነው። የዩጋንዳው ፕሬዝደንት ሙሰቨኒ፤ የግብጹ ፕሬዝደንት ሲሲና ወድቃለች የምትባለው፤ በዝቅተኛ ዘገባ አራት መቶ ሽህ ዜጎቿ የተጨፈጨፉባት የደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልቫ ኬር የጋራ የውስጥ ሴራ በማቀናጀት የተሃድሶ ግድቡ እንዳይሰራ በማደም፤ ኢትዮጵያን የጦር አውድማ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ይህ የሶስት አገሮች የተንኮል ቁርኝት (Axis of Evil Regimes) እንዴት ይሰራል? እያንዳንዱ መሪ የራሱን ስልጣንና ጥቅም ስኬታማ ለማድረግ የግብጽን ሴራ በመስራት ላይ ይገኛል። ግብጽ የጥቁር አፍሪካን አገሮች የምታሽከረክርበት የመሳሪያ፤ የመረጃና የገንዘብ አቅም ፈሰስ ታደርጋለች። ሙሰቬኒና ሳልቫ ኬር ለህዝባቸው ኑሮ መሻሻል ደንታ የላቸውም። መረጃዎች የሚሉት ትክክል ከሆነ የዩጋንዳ ሕዝብ በሙሰቬኒ ላይ መነሳት አለበት። የደቡብ ሱዳን ሕዝብ ከግብጽ ጋር ከሚኖረው ግንኙነት በበለጠ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ወንድማማችነት ቢመርጥ እንደሚሻለው የዲፕሎማሲ ጫና ማድረግ ያስፈልጋል። ግብጽና ሌሎች የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም የሚጻረሩ ኃይሎች ሁሉ በልዩ ልዩ ቦታዎች መሳሪያ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ የሚያደርጉትን ሴራ ማቆም ያስፈልጋል። ደቡብ ሱዳን የግብጽ ተወካይ ሆና የመሳሪያ መሸጋገሪያነቷን ማቆም አለባት፤ ሰሜን ሱዳንም እንደዚሁ። የኢትዮጵያ መንግሥት አቋሙን በግልጽና በማያሻማ ደረጃ ለዩጋንዳና ለደቡብ ሱዳን ሕዝብ ማሰማት አለበት። ከበባው የህልውና ጉዳይ ነው።

የኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶች አመች እድል አጋጥሟቸዋል። አመቻቹ የአገር ውስጥ ኃይል በሰሜን ህወሓት ነው። በማህል አገር ዋናው አንቀሳቃሽ ጃዋር፤ ተከታዮቹና በማያገባቸው ጣልቃ እየገቡ ቅማንትና አማራ፤ አማራና አገው ወዘተ እያሉ እርስ በእርሱ እንዲጋጭ የሚያደርጉት ኃይሎች ናቸው። ለመሆኑ፤ ጃውር ሞሃመድን በቅማንትና በአማራ ሕዝብ መካከል ጣልቃ ገብቶ ተቆርቋሪ ያደረገው ማነው፤ ለማን ጥቅም፤ በማን ውክልና? ህወሓት፤ ግብጾች፤ ለትምህርቱ እድል የሰጡት ግለሰቦችና ተቋሞች? ከጀርባ ያለው አጥፊ ኃይል ክትትል እንዲደረግበት እጠቁማለሁ።

ግብጾች በኢትዮጵያ ላይ ሆነ ብለው እቅድ ማውጣታቸውን በተደጋጋሚ አሳስቤ ነበር። አልጀዚራ ካታር ጋብዞኝ ሄጀ በነበረበት ወቅት፤ የግብጽ ባለሞያዎችና ተባባሪዎቻቸው nile Hydro power hegemenony ስኬታማ እንዲሆን መፍቀድ አደገኛ ነው እያሉ ሲያባብሉ አይቻለሁ፤ ተከራክሬያቸዋለሁ፤ ኢትዮጵያ የራሷን ጥቅም የማስከበር መብት አላት ብየ ነበር። ያኔ፤ ኃይለማርያም ደሳለኝ ይመጣል የሚል፤ ካልመጣ ለኢትዮጵያ የሚከራከር ባለሞያ ይልካል ተብሎ ተወርቶ አንድም ሰው አልመጣም። ይህ ተከታታይ የመንግሥት አመራር ክፍተት የሚያሳየው አንድ ሁኔታ አለ። ይኼውም፤ የኢትዮጵያ ዘላቂ ክብርና ጥቅም ሊከበር የሚችለው ለአገሪቱና ለመላው ሕዝቧ ወገናዊና ታማኝ የሆነ መንግሥት፤ አመራርና የማይበገሩ ተቋማት ሲኖሯት ብቻ ነው።

ለኢትዮጵያና ለመላው ሕዝቧ ተቆርቋሪ የሆነ መንግሥት ሊያደርጋቸው የሚችለው ስልቶች አሉ። ለምሳሌ፤ ኢትዮጵያ ግብጽን በዘላቂነት ውሃ እንዳይኖራት ለማድረግ የሚያስችሉ ልዩ ልዩ መንገዶች እንዳሏት ማሳየት አንዱ አልት ነው። ከታላቁ ግድብ ውጭ የውሃን ምንጮችን ለመስኖ ስራ ለመገደብ ይቻላል። ጨው ለራስህ ስትል እንዲሉ፤ ግብጽ ለራሷ ዘላቂ ጥቅም ስትል የኢትዮጵያን ሕዝብ እርስ በእርሱ እንዲገዳደል የምታደርገውን ሴራ እንድታቆም ሁላችንም ግዴታችን መወጣት አለብን፤ ድምጻችንን በማሰማት። ወጣቱን ትውልድ በማስተማርና አቅሙን ጠንካራ በማድረግ። የስራ እድል በመፍጠር። ኢኮኖሚውን በማሳደግ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ተከብሮ፤ የኢኮኖሚው ተካፋይ ሆኖ  ከተባበረ ማንም አያሸንፈውም። እንሰብሰብ፤ እንደራጅ፤ አናመንታ፤ የከበባውን አደጋ እናስብበትና ለጋራ አገር የጋራ መፍትሄ እንፈልግ እላለሁ።

ህወሓት የተከተለው መሰሪና አጥፊ መስመር አንድ ነው። ጃዋር፤ ኦነግ፤ ህወሓትና ሌሎች ጽንፈኞችና አመጸኞች አማራውን የጥላቻ ኢላማ አድርገው እንዲጋለጥ ተከታታይ ዘመቻ የከፈቱበት መሰረታዊ ምክንያት ይህ ታላቅ ሕዝብ በማንኛውም ኢትዮጵያ ከሁሉም ኢትዮጵያዊያን ወንድሞቹና እህቶቹ ጋር ተዛምዶና ተዋልዶ የመኖር ባህሉ ጠንካራ ስለሆነ ነው። በተጨማሪ፤ ይህ ሕዝብ ከማንኛውም እሴት በላይ ለኢትዮጵያንና ለኢትዮጵያዊነት ምሰሶ ስለሆነ ነው።

በአጠቃላይ ስመለከተው፤ በህወሓት የበላይነት የሚገዛው ኢህአዴግ ጭካኔ ሲያካሂድ ስናሳይ የነበረው ወኔ የውሃ ሽታ ሆኗል። ህወሓቶች በመቀሌ ቢሸፍቱም፤ የዘረጉት ድርጅታዊ መዋቅር፤ የፈጠሩትና ያሰራጩት የዘረኝነት መርዝ አሁን እንደተከሰተው የአንበጣ ወረራ በየአካባቢው ተስፋፍቷል። ይህ ህገወጥነትና ስርዓት አልበኛነት በተለያዩ መሳሪያዎች ስኬታማ እየሆነ ነው። ጌታቸው ረዳና ጃዋር ምን ግንኙነት አላቸው፤ ምን ይዶልታሉ፤ ማንን ለመጉዳትና ማንን ለመጥቀም? የጃዋር ደጋፊዎች ማስታወስ ያለባቸው ህወሓት በኦሮሞ ንጹህ ሕዝብ ላይ የፈጸመውን ጭካኔ ነው። በአንድ ወቅት ብቻ የህወሓት አልሞ ተኳሺዎች ሰባት መቶ ንጹሃንን ጨፍጭፈዋል። ይህ አይደገምም ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው።

የጥፋት መስፈርቶች ምንድን ናቸው?

  1. በተቀነባበረ የማህበረሰባዊ ሜድያ (A coordinated and well-financed cyber warfare) አማካይነት፤
  2. በመንደሮች፤ በትንንሽና በታላላቅ ከተሞች ተምሮ ስራ በሌለው ወጣት ትውልድ የመንጋ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ቅሰቀሳና አቅም ግንባታ አማካይነት፤ የስራ እድል መፍጠር ፖሊሲ አስቸኳይ መሆኑን ያመለክታል፤
  3. የዚህን ግዙፍ የማህበረሰብ ካፒታል የሞባይል፤ የእንቅስቃሴ፤ የመጓጓዥያና የመሳሪያ አቅም በመደጎም፤ በአንዳንድ ቦትዎች የቀን አበልና ሌላ ድጋፍ በመስጠት፤ የተሰረቀውና የሚዘረፈው ኃብት ለጥፋት እየዋለ መሆኑ ይታያል፤
  4. የወጣቱን ትውልድ የዘውጋዊነት ስሜት፤ የኃይማኖት ልዩነት ስሜት በማባባስ (Inflaming and inciting ethno nationalism and religious fanaticism among unemployed youth and calling for a Caliphate alternative in Ethiopia)፤ የኢህአዴግ አመራር ገንቢ አማራጮችን ለማቅረብ አለመቻሉ ይታያል፤
  5. የጸጥታ መበከል (የአካብቢና የፌደራል ፖሊስ፤ የደህንነትና የመከላከያ ወዘተ ኃይሎችን ተባባሪ በማድረግ)፤ ጠንካራ፤ ህብረብሄራዊና ተገዢነታቸው ለኢትዮጵያ ብቻ የሆኑ ተቋማት ገና አለመመስረታቸውን የሚያሳይ ሁኔታ ይታያል፤
  6. ከላይ እንደጠቀስኩት፤ ኢትዮጵያ እንድትፈራርስ የሚመኙ የውጭ ኃይሎችን አጋርና ተባባሪ በማድረግ፤ በተለይ ታላቁ የኢትዮጵያ የተሃድሶ ግድብ ስኬታማ እንዳይሆን የማትፈልገውን የግብጽን ዓላማ የሚደግፉ ኃይሎችን በማቀናጀት፤ ህወሓት፤ ጃዋርና ሌሎች ጽንፈኞች ቢቀበሉም ባይቀበሉም ተባባሪ መሆናቸው ይታያል፤
  7. በሰላምና በወዳጅነት የሚኖረውን የክርስትና፤ በተለይ የኢትዮጵያ ተዋህዶ እምነት ተከታዮችን ከእስልምና ተከታዮች ወንድሞቹ ጋር እንዲጋጩ በማመቻቸት፤ ግጭቶት ከዘውግ ልዩነት ባሻገር የኃያማኖት ልዩነት ጉልህ ሆኖ የእርስ በእርስ ጦርነት እንዲከሰት በመቀስቀስ፤ በባሌ የተካሄደው የአስር አቋምች መግለጫ ይኼን ያጠናክራል፤ ይህን አደጋ የተገነዘቡ አባቶችና እናቶች መመካከር መጀመራቸው ጥሩ ዜና ነው፤
  1. በህወሓት፤ በኦነግ አክራሪ ቡድን፤ በቄሮና በሌሎች ጽንፈኞች፤ በጠባብ ብሄርተኞችና የሚካሄደውን ሰላማዊ ለውጥ በሚያወግዙና በሚጠሉ ኃይሎች መካከል ያለውን ግንኙነት በማጠናከር “መንግሥት የለም”፤ ህወሓቶችና አጋሮቻቸው ሥልጣን ካልያዙ በስተቀር ኢትዮጵያ ትፈራርሳለች የሚለውን የመልሶ መቋቋም ስልት በማጠናከር፤
  2. “ሁለት ወይንም ሶስት መንግሥታት አሉ” የሚለው ትርክት እንዲዛመት በማድረግና የኢትዮጵያ ጠላቶች “ኢትዮጵያ ባለቤት የላትም” ብለው እንዲያምኑ በማድረግ፤ የዚህ መስመር አለቃዎች ህወሓት በመቀሌ፤ አዲሱ ልዑል (The New Prince) ጃዋር ሞሃመድ በአዲስ አበባና በመላው ኦሮምያ የተከሰተውን በማጋነን፤ ለሰማንያ ስድስት ንጹህ ኢትዮጵያዊያን መቅሰፍት የሆነውን ወንጀል በመፈጸም፤
  3. ይህንን የተቀነባበረ ሴራ ስኬታማ ለማድረግ የፌደራሉ መንግሥት ተቋማት አቅም እንዲበተኑ በሚያደርግ ስልት በየአካባቢው አመጽ እንዲከሰት በማድረግ፤ አንዴ አማራ ክልል፤ ሌላ ጊዜ ቤኒ-ሻንጉል ጉሙዝ፤ አዲስ አበባ፤ ድሬ ዳዋ፤ ሃረርና ኦሮምያ ወዘተ (spontaneous disobedience, agitation, disoonance and public unease)፤ በማካሄድ፤
  4. ሕዝብ በመንግሥት ላይ እምነት እንዳይኖረው፤ የዋጋ ግሽፈት እንዲጨምር፤ ሕዝብ እንዲማረር፤ ኢኮኖሚው እንዲዳከም፤ ኢንቬስተሮች እምነት እንዳይኖራቸው፤ ገንዘባቸውን እንዲያሸሹ፤ ለወጣቱ ትውልድ የስራ እድል እንዳይፈጠር፤ ወጣቱ ተስፋ እንዳይኖረው በማድረግ ወደ አላስፈላጊ ጉዞ እንዲሸጋገር በማድረግ፤ ወዘተ፤ ወዘተ፤ ወዘተ፤ እና
  5. አገር ውስጥና ውጭ የምንኖረው ኢትዮጵያዊያን በአንድነት እንዳንነሳ የተለያዩ የሃሰት ትርክቶችን በማሰራጨት የሚሉት መስፈርቶች ይገኙበታል።

ኢትዮጵያ ወደ የት እያመራች ነው?

በአጭሩ፤ ወደ አገር አቀፍ ህገወጥነት፤ ስርዓት አልበኝነት በመሸጋገር ላይ ናት። የአሜሪካ የአፍሪካ እዝ (United States High Command in Africa) የበላይ የሆነው ጀኔራል ስትፈን ታውሰንድ ወደ አዲስ አበባ የሄደበት ዋና ምክንያት አሜሪካኖች ከእልቂቱ ጀርባ የሚካሄደውን አስጊ ሴራ ስለሚያውቁ ነው ብል አልሳሳትም። ኢትዮጵያ ከፈረሰች መላው የአፍሪካ ቀንድ ይፈርሳል፤ ጀሃዲስቶች ካልፌት የሚመሰርቱበት ሁኔታ ይመቻቻል። አሜሪካ ኢትዮጵያ እንዳትፈራርስና በአፍሪካ ቀንድ እልቂት እንዳይካሄድ የምትፈልግ መሆኗን ለማሳየትና የኢንቬስትመንትና የገበያ ጥቅሟ እንዳይበከል የምትመኝ መሆኗን በሌላ መንገድም አሳይታላች።

በ November 6, 2019, የታላቁን የኢትዮጵያን የተሃድሶ ግድብ በሚመለከት በዋሽንግተን ዲሲ ግብጽና ኢትዮጵያ የጋራ ችግራቸውን በውይይትና በመከካከር እንዲፈቱ የተደረገው ውይይትና ስምምነት ተጨማሪ ምሳሌ ነው። ሁለቱ አገሮች የቀጥታ ውይይት እንዲያደርጉና ችግሮችን በስምምነት እንዲፈቱ የሚለው ስምምነት ለሁሉም አገሮች ጠቃሚ ነው። ኢትዮጵያ የራሷን ጥቅም ለማስከበር የምትችልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ግድቡ ስኬታማ እንደሚሆን አልጠራጠርም። ስለዚ፤ አክራሪዎችና ጽንፈኞች ከዚህ ድርድር ሊማሩ ይችላሉ።

የትግራይ ሆነ የኦሮሞ የአማራ ሆነ የአፋር፤ የደቡብ ሆነ የጋምቤላ ወዘተ ሕዝብ በስሙ ከፋፋይና ጽንቸኛ የሆኑ ኃይሎችን መታገል የሚኖርበት ዋናው ምክንያት አደጋው ሁሉንም ዜጎች ስለሚመለከታቸው ነው።

ዘገባው ወደ ዘውግ ተኮሩ (ጀኖሳይድትንተናየ ይወስደኛል።

ንጹህ ዜጎች ያለምንም ጥፋት በገጀራ፤ በዱላና በሌላ መሳሪያ በተጨፈጨፉ ግለሰቦች ላይ የተካሄደውን ጭካኔ የተሞላበትን እልቂት በአንድነት ሆነን ለማውገዝ አለመቻላችን ያሳፍራል፤ ያሳስባል። የተጨፈጨፉት ግለሰቦችና ቤተሰቦች ኢላማ የሆኑበት መሰረታዊ ምክንያት ምንድን ነው?

ካልፈራን በስተቀር፤ መልሱ አንድ ነው። አማራው፤ የአማርኝ ቋንቋ፤ የኢትዮጵያ ተዋህዶ እምነት ኃይማኖትና ተከታዮች፤ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት የሚያምኑ ሁሉም የዘውግና የኃይማኖት ተከታዮች በጀምላ ተጨፍጭፈዋል። ያካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ንብረታቸው ወድሟል፤ ተሰደዋል። ጉዳት የደረሰው የግድያው የዘውግና የኃይማኖት ስርጭት የሚያሳየው ይኼን ነው። አንድ ግለሰብ ኦሮሞም ቢሆን ጉራጌ ወይንም ሌላ የግድያው ተሳታፊና ደጋፊ ካልሆነ ለጥቃት ይጋለጣል። ስለዚህ፤ ከጀርባ ያለው አጀንዳ ከዘውግ በላይ የኃይማኖት ይዘት ያለው እየሆነ ሄዷል። ሌላው ቀርቶ አዲስ አበባ የደም መፋሰስ እልቂት እንዲካሄድ የሚደረገው ሴራ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ፈጽሞ ለማፈራረስ የሚደረግ ሴራ አካል ነው።

ድሃና ኋላ ቀር በሆነችው ኢትዮጵያ የሕግ ወጥ መሳርያ ንግድ ተፋፍሞ የሚካሄደው ለምንድን ነው፤ ከጀርባ ሆኖ ንግዱን የሚያካሂደው ኃይል ማነው? ብለን ራሳችን መጠየቅ ግዴታችን ነው። መሳሪያውን ቱርክም ሆነ ግብጽ ትሽጠው ያገር ወስጥ ሸማች ያስፈልጋል። ቀስቃሽ ያስፈልጋል፤ አመቻች ያስፈልጋል። በእኔ ጥናት፤ ምርምርና ግንዛቤ መሰረት፤ ጥሪው አገር አድን ጥሪ ነው። ምክንያቱም የእርስ በእርስ ጦርነት ቢካሄድ ማንም ብሄር አሸናፊ ሆኖ ሊወጣ አይችልም። ሁሉም ተጠቂ ይሆናል።

ሁሉን አቀፍ አስተሳሰብ፤ ሁሉን አቀፍ አደረጃጀት በጥበብና በብልሃት መስራት አለብን። የአማራው ጥያቄ የብቸኛነት ጥያቄ አይደለም፤ ሁሉም የሚኖርባትን ብሄራዊ አንደነቷ የተጠበቀና የጠነከረች፤ ፍትሃዊና ዲሞክራሳዊ ኢትዮጵያን መመስረት ወሳኝ ነው የሚል አቋም ነው።  ይህ መርህ የአንድ ብሄር ወይንም የአንድ ኃይማኖት ጉዳይ ሳይሆን የሁላችንም ነው። ስለዚህ፤ የምንጠቀመው ቋንቋ ሁሉ በጥንቃቄ መመረጥ አለበት። ጃዋር የሚናገረውን ለመቋቋምና ተቀባይነት እንዳይኖረው ለማድረግ ከፈለግን ጃዋርን መሆን የለብንም። ህወሓትን ተክተን ሌላ ህወሓት መፍጠር የለብንም። አለያ፤ የጠላቶች ወንፊት መሆናችን ይቀጥላል። ግብጽ የምትፈልገው ይኼን ነው።

ታላቋን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን እናስቀድም።

ለዚህ ነው፤ በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ የምንኖር ኢትዮጵያዊያን ሁሉ፤ ከመቸውም ጊዜ በላይ ዛሬ ከዘውግና ከኃይማኖት፤ ከጥቅምና ከመደብ ባሻገር ማሰብ ያለብን ቅስቀሳውና ሴራው በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ላይ ያነጻጸረ መሆኑን ማወቅ አስፈላጊና ወሳኝ ነው። ላጠናክረው የምፈልገው የወቅቱ ተግዳሮት የአንድ ዘውግ አይደለም፤ የኢዮጵያ የመኖር አለመኖር ጥያቄ ነው። ስለሆነም፤ ሁሉም ያገባዋል፤ የማያገባው አጥፊውን ክፍል ብቻ ነው።

በቅርቡ የተካሄደው እልቂት ልክ ቦዝንያና ሩዋንዳ እንደተከሰተው የዘውግና የኃይማኖት ድርብ እልቂት (It is an indicator of impending genocide) ምልክት ነው።

ጀኖሳይድ ማለት የዘር ወይንም የብሄር ማጥፋት ወንጀል ማለት ነው። “Genocide is intentional action to destroy a people (usually defined as an ethnic, national, racial, or religious group) in whole or in part. The hybrid word “genocide” is a combination of the Greek word γένος (“race, people”) and the Latin suffix -caedo (“act of killing”). The term genocide was coined by Raphael Lemkin in his 1944 book Axis Rule in Occupied Europe.” ፊሊፕ ሳንድስ የተባለው ጸሃፊ East West Street በተባለው መጽሃፉ የጀኖሳይድን ምልክቶች አሳይቷል። በሩዋንዳ ነፍሰ ገዳዮቹ ቅድመ ሁኔታዎችን ሲያመቻቹ የጠሏቸውን ዜጎች እየለዩ  የውጅንጀላ ስሞች ይሰጧቸው ነበር። ልክ ዛሬ ጽንፈኞች መጤ፤ ነፍጠኛ፤ ጡት ቆራጭ፤ ወራሪ፤ ወዘተ እንደሚሉት።

በ 1948 የተባበሩት መንግሥታት የደነገገው የጀኖሳይድ መመሪያ እንዲህ የሚል ነው። “Genocide  are acts committed with intent to destroy, in whole or in part, a national, ethnic, racial or religious group, as such” including the killing of its members, causing serious bodily or mental harm to members of the group, deliberately imposing living conditions that seek to “bring about its physical destruction in whole or in part”, preventing births, or forcibly transferring children out of the group to another group.”

ይህ ሰብሳቢ ዓለም አቀፍ ህግ ነው ሆሎኮስትን፤ የአርመኖችን እልቂት እና ሌሎችን የሚመራውና የሚዳኘው። በአሜሪካ የጥንት ነዋሪዎችን እልቂት፤ በሰርብያ የቦስንያኖችን እልቂት፤ በጓቴማላ የጥንት ነዋሪዎችን እልቂት፤ በካምቦድያ የንጹህ ሕዝብን እልቂት፤ በዳርፉር ባሽር የተከሰሰበትን እልቂት፤ በሩዋንዳ ሁቶዎች የፈጸሙትን እልቂት፤ በበርማ የሮሂንጋዎችን እልቂት የሚመራውና የሚዳኘው ይኼው ህግ ነው። ጥናቶች የሚያሳዩት ከ1956 እስከ 2016 ባለው ጊዜ ውስጥ 43 የዜጎች እልቂቶች ተካሂደዋል፤ 50 ሚሊየን ንጹሃን ተጨፍጭፈዋል። አምሳ ሚሊየን ሌሎች ተፈናቅለዋል። ብዙ ወንጀለኞች ለፍርድ ቀርበዋል። ገና ያልተፈረደባቸውም አሉ። በኢትዮጵያም ቁጥሩ በትክክል የማይታወቅ የአማራ፤ የአኟክ፤ የኦሞ ሽለቆ ወዘተ ሕዝብ በገፍ ተጨፍጭፏል። የአማራው ሕዝብ ቁጥር በስድስት ሚሊየን እንዲቀንስ ተደርጓል።

የጀኖሳይድ ምልክቶቹ ጥያቄዎች ምን ይመስላሉ?

በልዩ ልዩ አገሮች እልቂቶችን ተከታትሎ፤ ለምሳሌ በአገራችን የአኟኮችን ጭፍጨፋ፤ ጠቃሚ ጥያቄዎችን ለመመሪያ ያቀረበልን ዶር ግሬገሪ ስታንቶን የሚከተሉትን 10 ጥያቄዎችና መርሆዎች እንድናስብባቸው ይጠቋማል፤

  1. CLASSIFICATION (ምደባ)፤ ሕዝብን በዘውግና በኃይማኖት መለያየት፤ “እኛና እነሱ” የሚል ክፍፍል ማራመድ፤
  2. SYMBOLIZATION (ምሳሌ)፤ የዘውግና የኃይማኖት መለያዎችን ማጋነን፤ የሚጠሉትን ተቋም ማቃጠል፤ ምልክቶችን መፋቅ፤ ማፍረስ፤ ተከትዮች “እየለዩ ማውደም” የሚል መርህ እንዲከተሉ ማድረግ፤
  3. DISCRIMINATION (መለየት/ መበደል)፤ የህግ አፈጻጸም፤ የአስተዳድር፤ የፖለቲካ ሥልጣን፤ የመሬት ይዞታ አድልዏና ኢ-ፍትሃዊነት ማሳየት፤ “በዚህ መሬት ልትኖር አትችልም፤ ወደመጣህበት ሂድ” ማለት፤
  4. DEHUMANIZATION (ሰብእንትን መግፈፍ)፤ ሰውን እንደ እንስሳ ማረድና ማሳረድ፤ መጨፍጨፍ፤ የሌለ መለያ እየሰጡ ማንቋሸሽ፤ ያልተደረገ ታሪክ ፈጥሮ ማባዛት፤ የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ማዘውተር፤ ግለሰቦችን ማዋረድ፤ ስልጣንን ለተንኮል መጠቀም፤
  5. ORGANIZATION (መደረጀት)፤ ጀኖሳይድ ያለ ድርጅት አይካሄድም፤ መንግሥትንና ህግን የሚጻረር አካል መኖር አለበት፤ “እናንተን እንጅ እኛን ሕጉ አይመለከተንም” የሚል እምቢተኛነት ማንጸባረቅ፤ ለዚህ አልገዛም፤ አልዳኝም የሚል መሪና ቀስቃሽ አካል ወሳኝ ነው፤
  6. POLARIZATION (ዝንፈት)፤ ጽንፈኝነትና ጥላቻ መመሪያ ይሆናል፤ ከሌሎች ጋር አትጋቡ፤ አትነግዱ፤ መሬት አትሽጡ፤ ቤት አታከራዩ፤ ተባባርዎችን እንደ ከሃዲ ቁጠሯቸው፤ ወዳጅነት ንፈጓቸው የሚሉ ትርክቶችን ማስተጋባት ቁልፍ ባህሪና መመሪያ ነው:: የዘውግ ጥላቻን ያዘመቱት ጣልያኖች ቢሆኑም፤ በሕገ መንግሥቱ መከፋፈልን ተቋማዊ ያደረገ ህወሓት መራሹ ኢህአዴግ ነው። ይህን ፈለግ ተከትለው ጃዋርና ቄሮ ከሚያደርጉት ጋር ይዛመዳል። ለዚህ ነው፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የገንዘብ ምንጭ ከየት እንደሆነ፤ የሜድያውን ስርጭት አፍራሽነት አደጋ ማወቅና ማገድ የሚኖርበት፤
  7. PREPARATION (ዝግጅት)፤ አጥፊዎች ጥፋታቸውን የሚያካሂዱት በዝግጅትና በውጭ የተቀነባበረ ድጋፍ ነው። የኢትዮጵያን ችግር ሁሉ የሚያይዙት ክሚጠሉት ዘውግ፤ ኃይማኖትና አመለካከት ጋር ነው። በሩዋንዳ ቱትሲዎች ጠላት ናችሁ ተብለው ተጨፈጨፉ፤ ዓለም ቸል ብሎ ተመለከተ፤ ከስምንት መቶ ሽህ በላይ ንጽህ ዜጎች ተጨፈጨፉ። በተመሳሳይ በኢትዮጵያም በአማራው ህዝብ ህልውናና የኢትዮጵያን ብሄራዊ እንድነት በሚደግፉ ላይ ሁሉ እልቂት ተካሂዶባቸዋል። የቅርቡ እልቂት ዋና ምሳሌ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት ማድረግ ያለበት ውሳኔና እርምጃ ኢትዮጵያ ርዋንዳ ከመሆኗ በፊት የማያወላውል እርምጃ መውሰድ እንጅ እልቂት ከተካሄደ በኋላ አይደለም።
  8. PERSECUTION (ማሳደድ)፤ ኢላማ የሆኑትን ዜጎች ከቀያቸው ማባረር፤ ስደተኛ እንዲሆኑ ማድረግ፤ በረሃብ እንዲሰቃዩ፤ ቤትና ንብረት እንዳይኖራቸው ማስገደድ፤ ንብረታቸውን መውረስና ማውደም ጀኖሳይድ እየተቃረበ መሄዱን ያመለክታል። የተባበሩት መንግሥታት አቋም የሚወስድበት ወቅት ይኼ ወቅት ነው።
  9. EXTERMINATION (ጥራት፤ እልቂት)፤ እልቂት የገፍ ግድያ ነው (Wholesale massacre) በዓለም ሕግ የሚታወቀው ጀኖሳይድ ተብሎ ነው። ዜጎች ከእንስሳ ባላነሰ ደረጃ ይታረዳሉ። ይህን ጭፍጨፋ ሊያቆመው የሚችል የታጠቀ ኃይል ብቻ ይሆናል። ምክንያቱም የሚጨፈጨፉት ህጻናት፤ ሴቶች፤ ሽማግሌዎችና ሌሎች ያልታጠቁና ያልተዘጋጁ ንጽሃን ናቸው። ለእንሱ መድረስ ያለበት የፈደራሉ መንንግሥት ነው።
  10. DENIAL (ክህደት)፤ ጀኖሳይድ ከተካሄደ በኋላ ጨፍጫፊዎች ሁሉ ወንጀሉን ይክዳሉ፤ “ የእኔ እጅ የለበትም” ማለት የተለመደ ክስተት ነው። አጥፊዎች ያላጠፉ ወገኖችን መክሰስ ይጀመራሉ። በተለይ ከጀርባ ሆነው ጭፈጨፋው እንዲካሄድ ያደረጉ ግለሰቦችና ስብስቦች ክህደትን እንዳማራጭ ይጠቀማሉ። በተጨማሪ፤ አጥፊዎች ይደበቃሉ፤ አቅም ያላቸው ይሰደዳሉ። ሌሎቻችን ማድረግ ያለብን፤ ጀኖሳይይድ ያካሄዱትን ወይንም ለማካሄድ የሚዘጋጁትን የትም ሆነ የትም ቢሆን በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ ነው።

ለማጠቅለል፤ ጀኖሳይድ ከመካሄዱ በፊትና እንዳይካሄድ ከተፈለገ፤ የኢትዮጵያ መንግሥትና የክልል ባለሥልጣናት ማድረግ ያለባቸው ከላይ የተጠቀሱትን መስፈርቶች መሰረት አድርገው ወንጀል የሰሩትን በሃላፊነት ለፍርድ ማቅረብ ነው። ሕግ ይከበር ከተባለ ወንጀል የሰሩ ለፍርድ ይቅረቡ የሚለው ስኬታማ መሆን አለበት። መንግሥት ሕግን ካላስከበረ ወደፊት የሚከሰተው እልቂት ከመቸውም የባሰ እንደሚሆን አስቅድሞ ለመገመት ይቻላል። እልቂት ከተካሄደ ደግሞ መታሰብ ያለበት አገራችንን አናጣታለን የሚለውን ክስተት ማሰብ ታሪካዊ ግዴታችን መሆኑን ነው ።

በተጨማሪ፤ እልቂቱን የሚከታተሉ ታዛቢዎች፤ አገር ወዳዶችና የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች መረጃዎችን ስልት ባለው መንገድና ዘዴ ዛሬ መሰብሰብ አለባቸው።

መረጃዎችን መሰብሰብ ወሳኝ የሚሆነው በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶችና በሌሎች ተቋማት (International Criminal Court and International Tribunals) ክስ አቅርቦ ስኬታማ ውጤት ለማግኘት መረጃዎች፤ ቪዲዎች፤ ኢሜይል፤ የአይን ምስክሮች፤ መቃብሮች፤ የተቃጠሉ ተቋማትና ንብረቶች፤ የጋዜጣና ሌሎች ዘገባዎችን መሰብሰብ ወሳኝ ነው። ጋዜጠኞች፤ ብሎገሮች፤ ምሁራንና ሌሎች መረባረብ ግዴታቸው ነው። ምክንያቱም፤ እውቀትና መረጃ የሌለበት ክስ ስኬታማ የመሆን እድሉ ዝቅተኛ ስለሆነ ነው። ከራሳችንም ታሪክና ልምዶች ለመማር ባንፈቅድም፤ ከአይሁዶች የእልቂት ታሪክና የህልውና ልምዶች ልንማር መቻልና መፍቅድ ግዴታችን መሆኑ ግልጽ እየሆነ ሄዷል።

LEAVE A REPLY