የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ህዳር 26 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ህዳር 26 ቀን 2011 ዓ.ም

ለማ መገርሳ ያላመኑበትን ፓርቲ ወክለው ከአሜሪካ ባለሥልጣናት ጋር እየተወያዮ ነው

በአሜሪካ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ለማ መገርሳ ከሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሓላፊ ቲቦር ናጂ ጋር መወያየታቸው ተነገረ፡፡ በውይይቱ በአፍሪካ ቀንድ የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ  ትኩረት ሰጥተው መክረዋል ነው የተባለው።

በሶማሊያ፣ በሱዳንና በደቡብ ሱዳን  የተሰማራው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ፤ ለቀጠናው ገንቢ አስተዋፅኦ እያበረከተ እንደሆነም በውይይታቸው ላይ ማንሳታቸውን መረጃዎች እየጠቆሙ ያሉት።

በኦቦ ለማ መገርሳ የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ ፤ ለሁለቱ አገራት 9ኛው የሁለትዮሽ የመከላከያ ኮሚቴ ዓመታዊ ስብሰባ ወደ ስፍራው ማቅናቱ ይታወሳል። በስብሰባውሁለቱ አገራት በቀጣናው የጸጥታና ደህንነት፣ የመረጃ፣ ሰላም ማስከበር እና መከላከያ ጉዳዮች ዙሪያ ገንቢ ምክክር አድርገዋል።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ለኢትዮጵያ ልዑክ በዋሽንግተን በሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ ወታደራዊ ኃይሎች የጋራ ዋና መሥሪያ ቤት በወታደራዊ ሥነ ስርዓት የክብር አቀባበል እንደተደረገለትም ተገልጿል።

ሰሞኑን ኢሕአዴግ በውህደት ወደ ብልፅግና ፓርቲነት የሚያደርገውን ጉዞ በተመለከተ በግልፅ በሚዲያ ላይ ልዮነታቸውን ከማሳየት ባሻገር የመደመር ፍልሰፍናን የተቹት ለማ መገርሳ ወደ አሜሪካ በመሄድ እየተነጋገሩ ያሉት በሥራ ጉዳይ ቢሆንም ያላመኑበትንና ብዙኃኑ ኅብረተሰብን ተስፋ በአቋማቸው ተስፋ ያስቆረጡበትን ፓርቲ ወክለው መወያየታቸው በርካቶችን እያነጋገረ ነው::

ኢትዮጵያዬ ላይ አልደራደርም በሚል ጠንከር ያለ የቀደመ ንግግራቸው በኢትዮጵያ ሕዝብ ልብ ውስጥ ገብተው የነበሩት የለውጡ ቡድን ፊታውራሪ ኦቦ ለማ መገርሳ በቅርቡ በሰጡት አስተያየት ውህደቱ የኦሮሞ ሕዝብን ጥቅም ይጋፋል የሚል ስሜት ከማስተጋባታቸው ባሻገር የታገልነው የኦሮሞ ሕዝብን መብት ለማስከበር ነው በሚል ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በመወዛገባቸው ሰውየው እንዴት ላላመኑበት ፓርቲና ሃገራቸው ሊሠሩ ይችላሉ በማለት ኢትዮጵያውያን በመጠየቅ ላይ ናቸው::

ምሁራን ፣ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች  8 ቀን አብረው በማደር ፤ ኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በኋላ ምን እንደምትሆን መከሩ 

ከተለያዩ ማኅበረሰብ ክፍሎች የተወጣጡና ቁጥራቸው ከሃምሳ በላይ የሆነ ፣ በኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ሚና ይኖራቸዋል የተባሉ ፖለቲከኞች፣ ምሁራን፣ አክቲቪስቶች፣ ጋዜጠኞችና የተለያዮ ግለሰቦች ፤ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ለ11 ቀን አብረው ውለው፣ 8 ቀን አብረው አድረው ስለኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታ መምከራቸው ተሰማ።

እነዚህ በኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ ቁልፍ ሚና አላቸው የተባሉ አካላት፣ ምክክራቸውን ሲያደርጉ መገናኛ ብዙኃን እንዳይገኙ፣ ታዛቢዎችም እንዳይኖሩ ተደርጎ ነበር። 50 የሚሆኑትን ተሳታፊዎች ለመምረጥ ስድስት ወር ፈጅቷል ያሉት አዘጋጆቹ፤  የመጨረሻዎቹን ተሳታፊዎች ለመምረጥ150 ሰዎችን ማነጋገር አስፈልጎ እንደነበርም አስታውቀዋል። እነዚህ የምክክሩ ተሳታፊዎች በመጨረሻም ኢትዮጵያ የዛሬ 20 ዓመት ሊገጥማት ይችላል ያሏቸውን አራት ዕጣ ፈንታዎች ማስቀመጣቸውንም ቢቢሲ አዘጋጆቹን በማነጋገር ዘግቧል።

በወርክሾፑ ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት 20 ዓመታት ውስጥ ምን ምን ዓይነት ዕጣ ፈንታዎች ይጠብቋታል የሚለው ተነስቶ ውይይት ተደርጎበታል ያሉት የወርክሾፑ አዘጋጆች ከሆኑት መካከል አንዱ አቶ ንጉሡ አክሊሉ ናቸው።

ዝም ብለን ብንቀጥል ምንድን ነው የምንሆነው? ዝም ብለን ጊዜ የሚያመጣውን ከምንጠብቅ እየገነባን ብንሄድ የት ጋ ልንደርስ እንችላለን? የሚለውን 50ዎቹ ተሳታፊዎች ከተነጋገሩ በኋላ አራት ዕጣ ፈንታዎችን ለይተው አውጥተዋል ይላሉ። ተሳታፊ ምሁራኑ ይህንን በሚያደርጉበት ወቅት ግን የወርክሾፑ አዘጋጆች ሀሳብም ሆነ አስተያየት አይሰጡም ያሉት ደግሞ አቶ ሞኔኑስ ሁንደራ ናቸው። አቶ ሞኔኑስ ከወርክሾፑ አዘጋጆች መካከል አንዱ ሲሆኑ ውይይቱም ሆነ ሀሳቡ ከራሳቸው ከፖለቲከኞቹ የሚመጣ ብቻ መሆኑን ተናግረዋል። የአዘጋጆቹ ድርሻ የነበረው የስብሰባውን ሪፖርት መጻፍ፣ ለሁሉም ተሳታፊዎች መላክና እነርሱ በሚሰጡት አስተያየት መሰረት የተስማሙበት እየቀጠለ እንዲሄድ ማድረግ እንደነበርም በግልፅ አስቀምጠዋል::

በዚህ መሠረት ሁሉም የተስማሙበት ሰነድ ከ20 ጊዜ በላይ አስተያየት በመስጠት መመላለሳቸውን፣ በስህተት የገቡ እንዲወጡ፣ የተዘነጉ እንዲገቡ እየተደረገ የሁሉም ሀሳብ ተካትቶ የመጨረሻው ሰነድ መውጣቱ ታውቋል። የውይይቱ ተሳታፊዎች ኢትዮጵያን የዛሬ 20 ዓመት ሊገጥማት ይችላል ያሏቸውን እጣ ፈንታዎች በሰባራ ወንበር፣ በአጼ በጉልበቱ፣ በየፉክክር ቤትና በንጋት መስለው አቅርበዋል በማለት አቶ ሞኔኑስ ሁንደራ የነበረውን ሂደት ያስታውሳሉ።

የዕጣ ፈንታዎቹ ስያሜዎችን ሲያብረራሩም፤ ሰባራ ወንበር ተብሎ የተሰየመው ኢትዮጵያ አሁን ባለው ሁኔታ ከቀጠለች የዛሬ 20 ዓመት የመንግሥት ሥልጣን ቢኖርም ሀገርን ወደ ሚፈልገው ጎዳና ለመምራት አስቸጋሪ ይሆናል በሚል መሆኑን ጠቁመው ፤ የፖለቲካ ኃይሎች፣ ብሔር ብሔረሰቦችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ሀገርን ወደ ቀና ጎዳና መምራት የሚያስችል ፍላጎት ቢኖራቸውም አቅም ግን አይኖራቸውም ሲሉ ይተነብያሉ። ከዚህ የተነሳ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ፣ ማኅበራዊና ደህንነት ሁሉ ይሽመደመዳል ይላሉ።

“አጼ በጉልበቱ” ተብሎ የተሰየመውን ዕጣ ፈንታ ሲያብራሩ፤በኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ሰዓት እየታየ እንዳለው ዜጎች የተለያየ ጥያቄ እያነሱ ነው ፣ መንግሥት እነዚህን ጥያቄዎች ለመፍታት የሚሠጠው ምላሽ ወሳኝ ነው ፤ አሁን ያለው ስጋት ጥያቄዎቹ እየበዙ ሲሄዱ መንግሥት ጥያቄዎቹን ለማፈን ጠመንጃ ቢጠቀም፣ ቢያስር ወደ የኃይል አገዛዝ የማምራት ዕጣ ፈንታ ይኖራል ሲሉ ተሳታፊዎቹ ሌላ ግምት ማስቀመጣቸውን ይናገራሉ።

‘የፉክክር ቤት’ በሚል በተቀመጠው ዕጣ ፈንታ ሊከሰት የሚችለው ፤ ብሔር ብሔረሰቦች ከአጼ በጉልበቱ አገዛዝ ለመውጣት የሚያደርጉት እና መብታቸውን ለማስከበር በሚወስዱት ርምጃ መሆኑን አቶ ሞኔኖስ ያስረዳሉ ። ብሔር ብሔረሰቦች በየግል የራሳቸውን አገር ለመመስረት ይንቀሳቀሳሉ። አገራዊ አስተሳሰብ እየቀረ ሁሉም በየብሔሩ እያሰበ የሚሄድበት ሁኔታ፤ በዚህም አተካሮና ፉክክር ውስጥ ተገብቶ የጋራ አገር ይረሳል፤ አገርም ወደ መፍረስ ትሄዳለች የሚል ስጋት እንዳለም ይጠቁማሉ።

በመጨረሻ የተቀመጠው ዕጣ ፈንታ ‘ንጋት’ የሚል ሲሆን ፤አሁን አገር ያለችበትን ሁኔታ ተሳታፊዎቹ በጨለማ መስለውታል ። በዚህ ወቅት እስር፣ ግድያ፣ መከፋፈል፣ እርስ በርስ መጠራጠር እና ሌሎች ስጋቶች ተጋርጠው ይታያሉ ፤ይሁን እንጂ እነዚህ ጥያቄዎች በሂደት እየተመለሱ ፣መተማመን እየተፈጠረ፣ መነጋገር ከተቻለ ፌደራሊዝምና እርሱን የሚያጠናክሩ ተቋማት እየዳበሩ፣ ጨለማው ተገፍፎ ብርሃን ይወጣላታል ተሳታፊዎች ግምታቸውን ማስቀመጣቸው ታውቋል።

ከእነዚህ ከአራት እጣ ፈንታዎች መካከል ሦስቱን ተሳታፊዎቹ ፈጽሞ እንደማይፈልጓቸው ማስቀመጣቸውን የሚናገሩት አቶ ንጉሡ፤ ‘ንጋት’ ግን ሁሉንም የሚያስማማ በመሆኑ ፣ በንጋት ውስጥ ሊያይዋት የሚፈልጓትን ኢትዮጵያ ለመስራት እና ለቀጣይ ትውልድ ለማውረስ እንደሚሰሩ በመግለጽ የሚችሉትን ሁሉ ለማድረግ የአቋም መግለጫ ማውጣታቸውን ‘ንጋት’ የተሰኘው እጣ ፈንታ እንዲሁ በቀላሉ ማግኘት እንደማይቻል በመግለጽ መነጋገር፣ መደማመጥ ብሔራዊ መግባባት እንደሚያስፈልገው ግን አዘጋጆቹ አስታውቀዋል። ያስረዳሉ።

የትብብር መንፈስ መፍጠር፣ እየሰጡ መቀበልና ማመቻመች ስለሚያስፈልግ በቀጣይ በሀገሪቱ ውስጥ ለሚኖሩ ድርድርና እርቆች እድል የሚሰጥ ነው የሚሉት አወያዮቹ ፤ የፓርቲ አመራሮች እዚህ የወሰኑትን የ’ንጋት’ ዕጣ ፈንታ ለአባላቶቻቸው በመንገር የማስረጽ ሥራ እንደሚሰሩ ይናገራሉ። ‘ንጋት’ን ወደ ሕዝቡ ለማስረጽ የተለያዩ ሥራዎችን እንደሚሰሩ የሚናገሩት አቶ ንጉሡ፤ የስብሰባው 50 ተሳታፊዎችም ይህንኑ እንደሚያደርጉ ቃል መግባታቸውን አብራርተዋል።

የእዚህ ትልቅ ሃገራዊ ፋይዳ ያለው ረዥም ጊዜ የፈጀ ውይይት አዘጋጆች ዘጠኝ ጓደኛሞች ናቸው። በተለያየ የህይወት አውድ ውስጥ የሚውሉ ቢሆንም ሲገናኙ ግን ስለ አገራቸው ዘወትር ያወራሉ ፣ ይመክራሉ። እነርሱም ሆኑ ሌሎች ስለኢትዮጵያ በሚያወሩት ጉዳይ ግን ደስተኞች አልነበሩም።ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ በተከሰተው ሕዝባዊ ተቃውሞና በነበረው ብሔር ተኮር ግጭት ምክንያት ብዙዎች የኢትዮጵያን ዕጣ ፈንታ ከሊቢያና ከሶሪያ ጋር እያዛመዱ የሚያወሩ መበራከታቸው በጥልቀት ለሃገራቸው እንዲያስቡና ከሚታየው የግጭት መስመር ለማውጣት የተለያዮ አካላትን አሰባስቦ ማነጋገር መሆኑን በማመን ይህንን መድረክ እንዳመቻቹ ለማወቅ ተችሏል::

የኦነግ ወታደሮች በደብረ ጉራቻ ከተማ አራት ፖሊሶች ላይ ጥቃት አደረ

በገብረ ጉራቻ ከተማ በታጣቂዎች በተከፈተ ተኩስ አራት የመንግሥት ጸጥታ አስከባሪ አባላት ላይ ጉዳት መድረሱ ተነገረ።

ትናንት (ሃሙስ) ምሽት 2፡30 ገደማ በሰሜን ሸዋ ዞን ኩዩ ወረዳ ገብረ ጉራቻ ከተማ የተፈጸመው ጥቃት ፖሊስ ጣቢያ ፊት ለፊት መሆኑን የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ደረጄ ደንደዓ አብራርተዋል። ጥቃቱ የመንግሥት የጸጥታ አስከባሪ አካላትን ለመግደል ያለመ መሆኑንም አመላክተዋል::

የግድያ ሙከራው ኢላማ ከነበሩት መካከል የኩዩ ወረዳ ፖሊስ ሓላፊ ዋና ሳጅን አዱኛ ደቀባ እና አብረዋቸው የነበሩ ሌላ የወረዳው ፖሊስ አባል እንደሚገኙበትም ታውቋል። የፖሊስ አባላቱ እራት በልተው ወደ ፖሊስ ጣቢያ ግቢ እየገቡ ሳለ ጥቃቱ መፈጸሙን የሚናገሩት የኩዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደረጄ፤ በፖሊስ አባላቱ ላይ በሁለት አቅጣጫ ተኩስ እንደተከፈተባቸው አስታውቀዋል።

“ዋና ሳጅን አዱኛ እግራቸውን ነው የተመቱት። አብሯቸው የነበረው የፖሊስ አባል ደግሞ እጁን ነው የተመታው” የሚሉት ዋና አስተዳዳሪው፤ የተኩስ ድምጽ ሰምተው ወደ በስፍራው የተገኙ ሌሎች ሁለት የቀበሌ ሚሊሻዎች ላይም ተኩስ ተከፍቶ ጉዳት ደርሶባቸዋል” በማለት ትናንት ምሽት በገብረ ጉራቻ ከተማ የተፈጠረውን ክስተት ለቢቢሲ አይፋ አድርገዋል።

በአራቱም የጸጥታ አስከባሪ አካላት ላይ የደረሰው ጉዳት ለህይወት የሚያስጋ አለመሆኑን እና ሦስቱ እግራቸው ላይ አንዱ ደግሞ እጁ ላይ ጉዳትእንዳጋጠማቸው ያስረዱት ሓላፊ ፤ “ሁለቱ በከተማችን በሚገኘው ሆስፒታል የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው ሲሆን፤ ሁለቱ ደግሞ ለተጨማሪ ህክምና ወደ አዲስ አበባ ተልከዋል” ሲሉ ገልፀዋል።

በኩዩ ወረዳ ጸጥታ አስከባሪዎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ሲፈጸሙ ይህ የመጀመሪያው አይደለም ፤ የቀድሞ የወረዳው ፖሊስ ሓላፊ ጨምሮ ሁለት የፖሊስ አባላት ከወራት በፊት በታጣቂዎች በተተኮሰ ጥይት ተገድለዋል። በተያያዘበወረዳው ቆላማ ቀበሌ ውስጥ ሁለት የቀበሌ ሚሊሻዎች ከሁለት ልጆቻቸው ጋር ተገድለው እንደነበር አስተዳዳሪው አስታውሰዋል።

የኩዩ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ደረጄ ለዚህ ሁሉ ወንጀል ተጠያቂ የሚያደርጉት በቀድሞ የኦነግ ጦር ስር የነበሩ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎችን ነው። ትናንት ጥቃት ያደረሱት ታጣቂዎች ተከታትሎ መያዝ አለመቻሉትን የተናገሩት አስተዳዳሪው ፖሊስ የግድያ ሙከራውን እየመረመረ ነው ብለዋል::

በአምቦ ዮንቨርስቲው በጽንፈኞች አማካይነት ተቋርጦ የነበረው ትምህርት ጀመረ

በአምቦ ዩኒቨርሲቲ መደበኛ የመማር ማስተማሩ ሂደት ሰላማዊ በሆነ መንገድ እየተካሄደ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ታደሰ ቀነአ ገለፁ።

ከአካባቢው ማኀበረሰብ እና ከተማሪዎች ጋር በተደረገ ውይይት የመማር ማስተማሩ ሂደት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ሰላማዊ በሆነ መንገድ እየተካሄደ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል። በሂደትም ግጭትን ለመከላከልና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን አጠናክሮ ለማስቀጠል ከተማሪዎች ጋር መግባባት ላይ መደረሱንም ተናግረዋል።

በስፍራው ቅኝት ያደረገው ባልደረባችንም የመማር ማስተማር ሂደቱ በአራቱም የዩኒቨርሲቲው ግቢዎች ሰላማዊ በሆነ መንገድ እየተካሄደ መሆኑን መታዘብ ተችሏል። ላለፉት ሳምንታት የነበረው ስጋት አለመኖሩን ጠቅሰው፥ አሁን ላይ የመማር ማስተማር ሂደቱ ሰላማዊ መሆኑን አስተያየታቸውን የሰጡ ተማሪዎች ተናግረዋል። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሰላም እንዲሰፍንም መነጋገር እና ተቀራርቦ መሥራት እንደሚገባ የዮንቨርስቲው ፕሬዝዳንት መክረዋል::

የፌደራል ማረሚያ ቤት በአ/አ ውስጥ ተጨማሪ እስር ቤት እያስገነባ ነው

የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የታራሚዎችን ሰብኣዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት አያያዝ የተሻለ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን ገለፀ።

የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ጀማል አባሶ ከታራሚዎች ሰብኣዊ መብት አያያዝ ጋር በተገናኘ፣ ከዚህ ቀደም ይደርሱ የነበሩ ችግሮችን ሙሉ በሙለ ማስወገድ መቻሉን በመጠቆም ፤ ታራሚዎች ላይ አንዳንድ የማይገቡ ተግባራትን በማድረግ ጫና ሲፈጥሩ የሚገኙ የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ሠራተኞች ላይም ዕርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል።

ከሰብኣዊ መብት አያያዝ በተጨማሪ ታራሚዎች በማረሚያ ቤት ሊያገኟቸው የሚገቡ እንደ ትምህርት እና የሕክምና አገልግሎቶችንም አስተዳደሩ በሚገባ እያከናወነ መሆኑን፣በዚህ መሰረትም በቀን ከ 250 እስከ 300 የሚሆኑ ታራሚዎች ከ17 በላይ በሚሆኑ የመንግሥት ሆስፒታሎች የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረጉን ከፋና ብሮድካስት ዘገባ መረዳት ችለናል።

በጉዳይ ላይ አስተዪየታቸውን የሰጡ ታራሚዎችም  ፤ ከዚህ ቀደም በማረሚያ ቤቶች የነበረው አያያዝ ችግሮች እንደነበሩበት አስታውሰው ፤ አሁን ላይ ግን እነሱ ያሉበትን ቃሊቲ ማረሚያ ቤት መነሻ በማድረግ የማረሚያ ቤት አያያዙ እየተሻሻለ ነው ብለዋል። የህክምና አገልግሎት እና የትምህርት አሰጣጥ ላይም ታራሚዎቹ ጥሩ አገልግሎት በማግኘት ላይ መሆናቸውን መስክረዋል። ሆኖምየሚኖሩባቸው ቤቶች ንፅህና እና ጥበት እንዲሁም የሚማሩባቸው መጽሐፍት ለበርካታ ዓመታት ያገለገሉ መሆናቸውን በቅሬታነት አቅርበዋል።

በታራሚዎቹ ቅሬታ መስማማቱን የገለጸው የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ችግሩን ለማስተካከል በመዲናዋ ዘመናዊ እና የራሱ ቤተ መጽሐፍ የያዘ ማረሚያ ቤት እያስገነባ መሆኑን ጠቁሞ ፤ ግንባታው በመጠናቀቀቅ ላይ የሚገኘው ይህ አዲስ ማረሚያ ቤት አምስት ሕንጻዎችን እንደያዘ ፣ እያንዳንዱ ህንፃም የማንበቢያ ክፍል እንዳለው አስታውቋል። የማረሚያ ቤቱን አዲስ ቤተ መጽሐፍት ለማጠናከር ከተለያዩ አካላት እየተሰጡ ካሉ መጽሐፍት በተጨማሪ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የአቅሙን እገዛ እንዲያደርግ ተጠይቋል።

LEAVE A REPLY