የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ታህሳሥ 2 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ታህሳሥ 2 ቀን 2011 ዓ.ም

ዶ/ር ደብረጽዮን አልሞቱም ያለው የትግራይ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ዋልታን እንደሚከስ አስታወቀ

ዛሬ ዶክተር ደብረጽዮን ባልታወቀ ምክንያት መሞታቸውን በድረገጹ ላይ ይፋ ያደረገው ዋልታ የኢንፎርሜሽን ማእከል ዘገባ ውሸት መሆኑን ያረጋገጠው የትግራይ ኮሙኒኬሽን ክስ እንደሚመሰርት ይፋ አድርጓል።

ዋልታ በበኩሉ መረጃው በፌስ ቡክ ገጹ በኩል የተላለፈው ከተቋሙ እውቅና ውጭ መሆኑን ገልጿል።

የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ዋልታ ኢንፎርሜሽን። ማዕከልን እንደሚከስ የወጣው መግለጫ ሙሉ ክፍል እንደሚከተለው ይነበባል ፡ –

ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማእከል የተባለ የመገናኛ አውታር የትግራይ ብሄራዊ ክልል መንግስት ም/ርእሰ መሰተዳደር ክቡር ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል ሂወታቸው አልፈዋል ብሎ በዛሬው እለት ያሰራቸው ነጭ የፈጠራ ወሬ ፈፅሞ ሀሰት መሆኑን ለመላው ህዝባችን ማሳወቅ እንወዳለን፡፡

ዋልታ ኢንፎረሜሽን ማእከል የተባለ የመገናኛ አውታር waltainfo.com በሚል ፌስቡክ ገፁ ላይ ዛሬ ታህሳስ 03/2012 ዓ/ም ከሰአት በኅላ ያሰራጨው ሀሰተኛ የአሉባልታ ወሬ፣ ይህ የመገናኛ አውታር ባለፉት አመታት በትግራይ ህዝብ ላይ የብሄር ተኮር ጥቃት እንዲደርስ ስያካሂደው የነበረ ዘመቻ ኣካል መሆኑን ሊታወቅ ይገባል፡፡

በመጨረሻም የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማእከል የተባለ የመገናኛ አውታር በህግ የሚጠቅይ መሆኑን ይገልፃል፡፡

የትግራይ ክልል ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ
መቐለ
ታህሳስ 03/2012

“ለማ መገርሳ  በሕይወት እያለ ሐውልት ሊቆምለት የሚገባው ጀግና ነው” ጃዋር መሐመድ 

በጽንፈኛነት የሚከሰሰውና ሰሞኑን ከአሜሪካ ወደ አዲስ አበባ የተመለሰው ጀዋር መሐመድ የኦቦ ለማ መገርሳ ደጋፊ መሆኑን በይፋ ገልጿል። ለማ መገርሳ አሁን ባለው ፖለቲካ ትልቅ ክብር የሚሰጠው ሰው ነው የሚለው ጃዋር መሐመድ ” በሕይወት እያለ ሐውልት ሊቆምለት የሚገባ ሰው ነው” ሲልም ውህደቱንና ብልፅግና ፓርቲን ያብጠለጠሉትን የመከላከያ  ሚኒስትር አቋም የሚጋራ መሆኑን አስታውቋል::

“ባለፈው ኹለት ዓመት የነበረው ግጭትና ውጥረት እንዲሁም የደረሰበትን መዋረድ በጣም ጥቂት ሰዎች ናቸው ሊቋቋሙና ፈገግ እያሉ ማሳለፍ የሚችሉት:: አሁንም ቢሆን የትግል አጋሩ የሆነውን የዐቢይን ብልፅግና መመስረቱን ጠብቆ ነው እንጂ የተቃወመው፣ ቀድሞ ቢናገር ኖሮ ብልፅግና የሚባል ነገር አይኖርም፣ ሊያቆመው ይችል ነበር:: ድርጅቱ ተመስርቶ ካለቀ በኋላ ነው አቋሙን ግልፅ ያደረገው:: የራሱን ሞራልና ሕሊና ጠበቀ፣ የወንድሙንና የትግል ጓዱን ፍላጎት ጠብቆ ነው ያደረገው” ሲልም ለለማ መገርሳ ብስለት የተሞላበት አካሄድ አድናቆቱን ገልጿል::

“በዚህ ውሳኔያቸው ዙሪ ምንም ማለት አልፈልግም:: ነገር ግን ባለፉት የፖለቲካ ዘመናት የለማ መገርሳን ያህል የኢትዮጵያ ባለውለታ የለም:: እናንተ የምታውቁትና የማታውቁት፣ ትእግስትና ቁርጠኛነት ያለው ሐቀኛ ሰው ነው:: እኔ በእድሜ ቢሆን ባለን ግንኙነት ዐቢይን ነው የምቀርበው:: ለማ ጭምት ስለሆነ መደበኛ ሥራ እንጂ ብዙ ቅርበት የለንም” በማለት ለብዙ ንጹኃን ዜጎች እልቂት ዋነኛ ተዋናይ የሆነው ጃዋር መሐመድ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበ ግንኙነት ያለው የሚያስመስል አስተያየቱን ለአዲስ ማለዳ ሰጥቷል::

ይሁን እንጂ ሀቁ ከዚህ ፈጽሞ የራቀ ነው የሚሉ ምንጮች ጃዋር መሐመድ በተለያዮ የሥራ ምክንያቶች ዶክተር ዐቢይ አሕመድን ለሁለት ጊዜያት ያህል ብቻ ለአጭር ደቂቃዎች እንዳገኛቸው ለቤተመንግሥቱና ለኦዴፓ ቅርብ የሆኑ የኢትዮጵያ ነገ ምንጮች አረጋግጠዋል።  ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጃዋር መሐመድ ይታደምባቸዋል የተባሉ የተለያዮ ሃገራዊና ክልላዊ (የኦሮሚያ) ፕሮግራሞችን መሰረዛቸውና ለመገኘት ፍቃደኛ አለመሆናቸው ግለሰቡን በተደጋጋሚ አበሳጭቶታል በማለት ምንጮቹ ገልጸዋል::

በአንድ ወቅት ለአቶ ሽመልስ አብዲሳና አዲሱ አረጋ “እሱ ከማን በልጦ ነው ከእኛ የሚሸሸው?” የሚል የንዴት ትችት ማቅረባቸውን ያስታወሱ የዜና ምንጮቻችን ጃዋር በአንጻሩ ከለማ መገርሳ ጀነራል ብርሃኑ ጁላና ከሌሎች ከፍተኛ የጦር መኮንን ከሆኑ የኦሮሞ ተወላጆች ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳለው ይጠቁማሉ:: ማንም እንደፈለገ በማይመላለስበት መከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ እንዳሻው የሚገባውና  የሚወጣው ጃዋር ከለማ ጋር ቅርበት የለኝም ማለቱ ሀሰት ከመሆኑ ባሻገር ጃዋር ከመከላከያ ሰዎች ጋር ስር የሰደደ ግንኙነት ማሳያው እሱ በጠራው አመፅ ላይ በተለያዮ የኦሮሚያ ክልሎች ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ሲጨፈጨፉ መከላከያ እንዳይገባ የዘገየበት አንዱ ምክንያት ነው ይላሉ::

“አሁን ለማ ላይ የሚደረገው ዘመቻ የኔን አቋም በድጋሚ ያረጋገጠ ነው:: ኦሮሞ ከሆንክ፣ ለመርህ እና ለሕዝብህ የቆምክ ከሆንክ ፣ ኢትዮጵያ ብለው የሚምሉ ሰዎች በሙሉ ይጠሉሃል:: የሚጠሉህ ለማ ስለሆንክ ገመዳ ስለሆንክ አይደለም ፤ ለኦሮሞ ሕዝብ መብትና ለእኩልነት የምትቆም ከሆነ ኃይሌ ፊዳን እንደጠሉት ታደሰ ብሩን እንደሰቀሉት ሌንጮ ለታን እንዳብጠለጠሉት ያብጠለጥሉሀል” ያለው ጃዋር መሐመድ “ለማን እላይ ሰቅለው ይዘውት የነበሩትን ሰው ለመርህ ስለቆመ ብቻ ዛሬ የሚደረግበት ዘመቻ ሳይ ለዚህ ትውልድ ምን ዓይነት አዲስ ትምህርት መጣ ነው ያልኩት:: የእሱን ያህል የአገር ባለውለታን ምንም አያደርገውም:: ይልቁንም ያጠነክረዋል:: ግን ለተወሰኑ ልሂቃን ኪሳራ ነው: የሚመስለኝ:: ለማ ግን ወደፊት ከፍተኛ ድርሻ ይዞ እንደሚቀጥል አልጠራጠርም” ብሏል ::

ሱዳን ያወጣችው አዲስ ሕግ ኢትዮጵያውያን ላይ እንደማይተገበር የሀገሪቱ መሪ አረጋገጡ

በሱዳን በቅርቡ የወጣው ሕግ ኢትዮጵያውያንን የሚመለከት እንዳልሆነ እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለስልጣን መሥሪያ ቤቶች ጋር በመነጋጋር እስሩ እንደሚቆም የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዳላ ሐምዶክ አስታወቁ፡፡ በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አምሳደር ሽፈራው ጃርሶ ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ጋር መወያየታቸው ተሰምቷል፡:

በምክክሩ አምባሳደሩ በቅርቡ የሱዳን መንግሥት ያወጣውን የውጭ ዜጎች በተለያዩ የንግድ ሥራዎች እንዳይሠማሩ የሚያግደውን ሕግ አፈጻጸም ተከትሎ ፣አፈሳና እስርን ጨምሮ በዜጎቻችን ላይ የተለያዩ እንግልቶች እየደረሱባቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡:

አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶ “ቡጣቃና” የመኖሪያ ፈቃድ ባላቸው ዜጎች ላይ ጭምር የሚጣለው ከ50 ሺህ እስከ 100 ሺህ ጁኔህ  (የሱዳን ገንዘብ) የሚደርስ የተጋነነ ቅጣትና በፍርድ ቤቶች አካባቢ ያለተገቢ ማጣራት በቅጽበት የሚሰጡ ፍርዶችን አስመልክቶ  ፤ ከዚህ ቀደም ለሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች ባላሥልጣናት ማሳወቃቸውን በማውሳት ጠቅላይ ሚኒሰትሩ በትኩረት እንዲያዩት እና እልባት እንዲሰጡት ግፊት አዘል ጥያቄ አቅርበውላቸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክም በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካካል ያለውን ጠንካራ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት አስታውሰው በሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከራሳቸው አልፈው ለአገሪቱ ኦኮኖሚ ጉልህ አበርክቶ ያላቸው መሆኑን መስክረዋል፡፡ በተጨማሪም በቅርቡ የወጣው ሕግ ኢትዮጵያውያንን የሚመለከት እንዳልሆነ እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለስልጣን መሥሪያ ቤቶች ጋር በመነጋጋር አፈሳው እንዲቆም እና በፍርድ ቤቶችና በጸጥታ አካላት የሚደርሱ ጥፋቶችን አስመልክቶ ሪፓርት እንዲቀርብላቸው መመሪያ አሰተላልፊያለሁ ብለዋል፡፡ ጉዳዩ በአጭር ጊዜ ውስጥ እልባት እንደሚያገኝም አረጋግጠዋል።

አምባሳደር ሽፈራው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አህመድ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ (ዶክተር)የላኩላቸውን መልዕክትም አድርሰዋል ፡፡

ፕ/ት ሣህለወርቅ ዘውዴ ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ሥራ አስኪያጅ ጋር ተወያዮ

ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ሥራ አስኪያጅ ዴቪድ ቢዝሊ ጋር ተወያዮ፡፡ በውይይታቸው ላይ ድርጅቱ በኢትዮጵያ እያደረገ ስላለው እንቅስቃሴ እና ለወደፊትም ሊሠራቸው ባሰባቸው እቅዶች ዙሪያ በጥልቀት ተነጋግረዋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ በተለያዩ የአስቸኳይ ምግብ አቅርቦት እና በምግብ እህል ራስን በሚያስችሉ መርሃ ግብሮች ላይ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል። ድርጅቱ ለ1 ነጥብ 7 ሚሊየን ሰዎች የኢትዮጵያ መንግሥት በሴፍትኔት ፕሮግራም በኩል የሚያቀርበውን ድጋፍም በከፍተኛ ሁኔታ እያገዘ መሆኑ ታውቋል።

በኢትዮጵያ ከሚገኙ የተለያዩ ሀገራት ስደተኞች ውስጥም 700 ሺህ የሚሆኑትን የምግብ አቅርቦቶችንም ለማሟላት በላቀ ደረጃ እየሠራ ነው ተብሏል::

ታከለ ኡማ ከብሔራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽን አባላት ጋር ተወያዮ

ኢንጅነር ታከለ ኡማ ከብሄራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽን አባላት ጋር ተወያዩ፡፡ የኮሚሽኑ አባላት በሀገሪቱ ብሄራዊ መግባባትን ለማስፈን በሚያከናውኗቸው ተግባራት የከተማ አስተዳደሩ ትብብርና ድጋፍ እንዳይለያቸው መጠየቃቸውም ተሰምቷል፡፡

ኮሚሽኑ ቁርሾዎችንና ቅራኔዎችን ለመፍታት እያደረገ ያለውን ዝግጅትና ጥረት   ያደነቁት ከንቲባው የከተማ አስተዳደሩ ለኮሚሽኑ ሀሳብ ስኬት ድርሻውን እንደሚወጣ ይወጣል ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡

የብሄራዊ እርቀ ሰላም ኮሚሽን አባላት ከክልል መስተዳድር አመራሮችና እና ከከተማ መስተዳድር አመራሮች ጋር ትውወቅና ውይይት እያደረጉ መሆናቸው ታውቋል፡፡

የዴንማርክ መንግሥት ለቀጣዮ ምርጫ የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገች

ዴንማርክ ለቀጣዩ ሃገራዊ ምርጫ የ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ስምምነት ተፈራረመች

አውሮፓዊቷ ዴንማርክ ቀጣዩን ሃገራዊ ምርጫ ለመደገፍ የሚውል የ1 ነጥብ 5 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የድጋፍ ስምምነት ፈጸመች ። የድጋፍ ስምምነቱን በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር ካሪን ፖልሰን እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተወካይ ቱርሃን ሳልህ መፈራረማቸው ተሰምቷል።

የዛሬው ስምምነት የዴንማርክ የትብብር ሚኒስትር ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት የዴንማርክ መንግሥት በገባው ቃል መሰረት የተለገሰ እንደሆነም ነው የተነገረው።

አምባሳደር ፖልሰን በኢትዮጵያ የሚደረገው ምርጫ ሃገሪቱ ወደ ሰላምና ብልጽግና ለምታደርገው ጉዞ ወሳኝ መሆኑን አመላክተው ፤ ከዚህ አንጻር ሃገራቸው ምርጫው ነጻና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር ትሰራለች ሲሉ አስረድተዋል።

ድጋፉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም በኢትዮጵያ ዴሞክራሲን ለማጠናከር ለሚያካሂደው ፕሮጀክትማስፈጸሚያ የሚውል ነው ተብሏል።

ፕሮጀክቱ ከፈረንጆቹ ከ2019 እስከ 2022 የብሄራዊ የምርጫ ቦርድን አቅም ለመገንባት የሚተገበር እንደሆነም ተረጋግጧል። ፕሮጀክቱ ግልፅ፣ ነጻ እና ሁሉን አቀፍ የሆነ ምርጫን ማካሄድ፣ የህዝብ ተሳትፎን ማሳደግ፣ በምርጫ ወቅት የሚነሱ ግጭቶን ቀድሞ በመለየትና በመቆጣጠር ምላሽ መስጠት የሚቻልበትን አግባብ መፍጠርን አላማው ያደረገ ነው ተብሏል።

ጀነራል ካሊፍ ሃፍታር ወታደሮቻቸው ትሪፖሊን ሙሉ ለሙሉን እንዲቆጣጣር አዘዙ

ሊቢያዊው የጦር ጀነራል ካሊፍ ሃፍታር ወታደሮቻቸው የሊቢያን መዲና ትሪፖሊን በቁጥጥራቸው ሥር እንዲያውሉ ተጽእኖ ፈጣሪው የጦር ጀነራል ይህን መልዕክታቸውን ያስተላለፉት በቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት ንግግራቸው ላይ መሆኑ ታውቋል።

ጀነራሉ ከዚህ ቀደም በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው ይህን መሰል መልዕክት አስተላልፈው አያውቁም ። የጀነራል ሃፍታር መልዕክት በትሪፖሊ ከተማ ነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ድንጋጤን እንደፈጠረ መረጃዎች እየጠቆሙ ነው።

ተፈሪው ጀነራል በተባበሩት መንግሥታት እውቅና ባለው መንግሥት ሥር የምትተዳደረውን ትሪፖሊን ለመቆጣጠር ከወራት በፊት የጦር እርምጃ ሲወስዱም መቆየታቸው አይዘነጋም። ትሪፖሊን የሚያስተዳድረው መንግሥት ግን የጀነራል ሃፍታር ወታደሮች ትሪፖሊን እንዳይቆጣጠሩ የመከላከል እርምጃዎችን ሲወስድ ታይቷል።

በተለይ በደቡባዊ ወደ ትሪፖሊ በሚወስዱ አቅጣጫዎች ላይ የጀነራሉ ወታደሮች ብዙ ሽንፈቶችን ተከናንበዋል ነው የተባለው። የፖለቲካ ተንታኞች የአሁኑ የጀነራሉ መልዕክት ጦራቸው ሙሉ ኃይሉን ተጠቅሞ መዲናዋን ለመያዝ መወሰኑን ያመላክታል ሲሉ ቅድመ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

ፊልድ ማርሻል ካሊፍ ቤልቃሲም ሃፍታር የአሜሪካ እና የሊቢያ ጥምር ዜግነት ያላቸው የሊቢያ ብሔራዊ ጦር የመሰረቱ እና የሚመሩ ተጽእኖ ፈጣሪ የጦር አለቃ ናቸው።

ጀነራል ካሊፍ የሊቢያ መንግሥትን ከሚቀናቀኑ ሁለት ቡድኖች መካከል ከአንደኛው ጋር ጥምረት በመመስረት  ፣ የትጥቅ ትግል እያደረጉ ናቸው። ጀነራሉ ከወራት በፊት ”አሸባሪዎች እና ወንጀለኛ ቡድኖች” ባሏቸው አካላት ላይ ጥቃት መሰንዘር ጀምረዋል።

በጦር አዛዡ ጀነራል ካሊፍ ሃፍታር የሚመራው ጦር ከወራት በፊት በወሰደው እርምጃ በነዳጅ ሃብታቸው የበለጸጉ ደቡባዊ የሊቢያ ክፍሎችን ተቆጣጥሯል።

በሊቢያ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ብዙ ንጹሃን ዜጎች ህይወታቸውን እያጡ ነው። በተለይ ደግሞ በመንግሥት ተቋማት እና በእስር ቤቶች ላይ በሚፈጸሙ ጥቃቶች በርካቶች የተገደሉ ሲሆን፤ የተባበሩት መንግሥታት እውቅና ያለው መንግሥት በተደጋጋሚ ለሚፈጸሙት ጥቃቶች በጀነራል ካሊፍ ሃፍታር የሚመራውን ቡድን ተጠያቂ አድርጓል።

LEAVE A REPLY