የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ታህሳሥ 6 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ታህሳሥ 6 ቀን 2011 ዓ.ም

መንግሥት ከትግራይ ባለሥልጣናት እርቅ ሊያደርግ ይገባል ሲል ክራይስስ ግሩፕ አሳሰበ

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ሽግግር ሃዲዱን እንዳይስት መንግሥት፣ የፖለቲካ አመራሮችና ዓለም አቀፍ አጋሮች አስፈላጊ ነገሮችን እንዲያደርጉ ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ ጠይቋል።

በዓለም ዙሪያ የሚከሰቱና ሊከሰቱ የሚችሉ ቀውሶችን የሚከታተለው ተቋም ኢትዮጵያን በተመለከተ ዛሬ ባወጣው ዘገባ ላይ በተለይ ከመጪው ምርጫ በፊት ሊደረጉ ይገባሉ ያላቸውን ነገሮች በዝርዝር አስቀምጦ፤ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ለውጥ በአገር ውስጥና በውጪ ተስፋን የፈነጠቀ ቢሆንም አደገኛና ከፋፋይ ሁኔታንም ደቅኗል በማለት ስጋቱን አጋርቷል።

ጥቅምት ወር ላይ ኦሮሚያ ውስጥ የተቀሰቀስው ተቃውሞ የደም መፋሰስን ማስከተሉን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የተከሰቱ ግጭቶች በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞትና በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩት ደግሞ መፈናቀል ምክንያት መሆናቸውን ያመላከተው ሪፖርቱ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለሦስት አስርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በብቸኝነት አገሪቱን ሲመራ የነበረውን ኢህአዴግን ለመለወጥ የወሰዱት እርምጃ ያለውን መከፋፈል የበለጠ ሊያሰፋው ይችላል ነው ያለው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩና አጋሮቻቸው እያካሄዱ ካለው የለውጥ እርምጃ አንጻር በኦሮሞ ቡድኖች መካከል እንዲሁም በአማራና በትግራይ ክልል አመራሮች መካከል ያለውን ውጥረት ለማርገብ ጥረት ማድርግ እንዳለባቸው በመምከር፤ ነገር ግን ውጥረቶቹ እየተባባሱ የሚሄዱ ከሆነ ይደረጋል የተባለው ምርጫን ማዘግየት ሊያስፈልግ እንደሚችል አሳስቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደስልጣን ከመጡ በኋላ የወሰዷቸው ተከታታይ የለውጥ እርምጃዎች በአገር ውስጥና በውጪ ትልቅ ተቀባይነትን እንዳስገኘላቸው የጠቀሰው የክራይስስ ግሩፕ ሪፖርት፤ ነገር ግን እርምጃዎቹ የነበረውን ሥርዓት በማስወገድ የመንግሥትን አቅም እንዳዳከመው ከመጠቆሙ ባሻገር፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ወደ ስልጣን ያመጣው ሕዝባዊ ተቃውሞን ያንቀሳቀሰው የብሔርተኝነት እንቅስቃሴ “አዲስ ጉልበት እንዲያገኝ አድርጎታል” ብሏል።

አክሎም በግንቦት ወር እንደሚካሄድ በሚጠበቀው ምርጫ እጩዎች ከየመጡበት የብሔር ቡድን ድምጽ ለማግኘት ፉክክር ስለሚያደርጉ ግጭቶች ሊከሰቱ እንደሚችሉም ግምቱን አስቀምጧል::

በተጨማሪም በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ እየጨመረ የመጣው በአብያተ ክርስቲያናትና በመስጊዶች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት በእምነቶች መካከል ያለው ውጥረት እየጨመረ መምጣቱን ከመጠቆሙ ባሻገር አገሪቱ ባለባት ችግር ላይ ሌላ ፈተናን የሚጨምር ነው የሚለው የክራይስ ሪፖርት፤ ሌላኛው የውጥረት ምንጭ ብሎ ሪፖርቱ ያስቀመጠው ጉዳይ ደግሞ አገሪቱ የምትከተለው የብሔር ፌደራላዊ ሥርዓት ጉዳይ ነው። ይህንን በሚደግፉና በሚቃወሙ ወገኖች መካከል ያለው ክርክር በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ “ዋነኛ የመፋለሚያ ምክንያት” መሆኑን አስታውቋል።

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት ግንባር ሌሎች አጋር ድርጅቶችን አካትቶ አንድ ወጥ አገር አቀፍ ፓርቲ ለመሆን ከወሰነ በኋላ ድጋፍና ተቃውሞ እንዳጋጠመው፣ ውህደቱ ከላይ በኢህአዴግ የተያዘው የመንግሥት ቢሮክራሲ ውስጥ ተጨማሪ ውጥረት ሊፈጥር እንደሚችልም አመልክቷል።

በዚህም መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የአማራና የትግራይ አመራሮች ግንኙነታቸውን የሚያሻሸል ውይይት እንዲያደርጉ ግፊት ማድርግና በኦዲፒ ውስጥም ሆነ ከሌሎች የኦሮሞ ተቃዋሚ አባላት ጋር በመነጋገር ልዩነቶች ከኃይል ይልቅ በምርጫ ውጤት መፍትሄ እንደሚያገኙ መተማመን ላይ መድረስ ይጠበቅባቸዋል የሚለው ሪፖርት፤ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአማራና በኦሮሞ አመራሮች መካከል የሚካሄዱ ውይይቶች እንዲቀጥሉ በማድረግ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች የሚስተዋሉ ውጥረቶችን ማርገብ ይጠበቅባቸዋል ሲል መክሯል።

መንግሥት ከትግራይ አንጻር እርቅ የሚያወርድ እርምጃን በመውሰድ ከቀድሞ ባለስልጣናት አንጻር የሚነሱ ክሶችን ተመልሰው እንዲያጤኑ ሊያደርግ ይችላል። ከዚህ በተጨማሪም ሽግግሩን ተከትሎ የተፈጠረውን አደገኛ የሆነውን የትግራይ መገለል መንግሥት ሊያጤነው ይገባል። የትግራይ አመራሮችም በበኩላቸው እንደማይቀበሉት ያሳወቁትን ከአማራ ክልል ጋር የሚወዛገቡበትን የይገባኛል ጥያቄዎች ለመመለስ የተቋቋመውን የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽንን በተመለከተ ውሳኔያቸውን መለስ ብለው ማስተካከል ይኖርባቸዋል በማለትም አስጠንቅቋል::

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩና አጋሮቻቸው ውህድ ፓርቲ በሚመስርቱበት ሂደት ውስጥ የብሔር ፌደራሊዝሙ ሊቀር ይችላል በሚል የተፈጠረውን ስጋት በጥንቃቄ ማስወገድ ይጠበቅባቸዋል የሚለው ክራይስስ ግሩፕ፣ በሕገ መንግሥቱ ላይ ማንኛውም አይነት ማሻሻያ የሚደረግ ከሆነ የሚመለከታቸው ወገኖች በሙሉ የሚሳተፉበት እንደሚሆን በግልጽ ማስቀመጥ ያስፈልጋል ብሏል።

ሪፖርቱ እንደሚለው ምርጫው በተያዘለት ጊዜ የሚካሄድ ከሆነ ቀደም ብሎ ቁልፍ ተቃዋሚ ኃይሎችንና ሲቪል ማህበራትን በማሳተፍ ከምርጫው በፊትና በኋላ ሊከሰቱ የሚችሉ ግጭቶችን ለማስወገድ ተከታታይ ውይይቶችን ማድረግ ያስፈልጋል።

ነገር ግን መከፋፈልና ግጭትን የሚያስከትል የምርጫ ዘመቻ የሚያይል ከሆነ መንግሥት ከዋነኛ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ድጋፍ በመጠየቅ ምርጫው ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍና ብሔራዊ ውይይት እንዲካሄድ ሊጠይቅ ይችላል።

ሪፖርቱ ለኢትዮጵያ መንግሥት ካቀረበው ሃሳብ በተጨማሪ ለአገሪቱ ዓለም አቀፍ አጋሮችም ጥሪ አቅርቧል።

በዚህም መሰረት አጋሮች የሚይዙት አቋም በመሬት ላይ ያለውን አሳሳቢ ሁኔታን መሰረት ያደረገ መሆን አለበት ብሏል። ስለዚህም ለሽግግሩ በይፋ ድጋፋቸውን በመግለጽ በዝግ ደግሞ ሁሉም ወገኖች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማግባባት ይጥበቅባቸዋል ብሏል።

ከዚህ ባሻገርም በመጪዎቹ ወራት የፖለቲካውና የደህንነቱ ሁኔታ የማይረጋጋ ከሆነ ምርጫው እንዲዘገይ ሃሳብ ሊያቀርቡ ይችላሉ።

የውጪ አጋሮች የሚሰጡት ተከታታይ የገንዘብ ድጋፍ እስፈላጊነትን የጠቀሰው ሪፖርቱ፣ የተዳከሙ ተቋማትን ለማጠናከር፣ የኢኮኖሚ መዋቅር ለውጥ ለማምጣት እንዲሁም በለውጡ ወቅት የሚከሰትን የወጣቱን ቅሬታና ተቃውሞ ለመቀነስ ይረል።

ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለው ለውጥ ለብዙዎች ተስፋን የሰጠ እንደሆነ የጠቀሰው ሪፖርቱ የሚታዩ ምልክቶች ግን ለቀድሞ ከፍተኛ ባለስልጣናት አሳሳቢ ናቸው ብሏል። የእንዳንዶች ስጋት የተጋነነ ቢሆንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጀመሩት የለውጥ ሂደት ላይ ጥንቃቄን በማከል ወሳኝ የሆኑ ደጋፊዎችን አሳትፈው መጓዝ እንደሚያስፈልጋቸው አመልክቷል።

በተጨማሪም ሁሉንም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለማሳተፍ የሚያደርጉትን ጥረት በማጠናከር፣ በሚወዛገቡ የክልል ልሂቃን መካከል ውይይቶች እንዲቀጥሉ በማድረግ፣ የገዢው ግንባር ውህደት አገሪቱን እንደማያናጋ የሚያረጋግጡ እርምጃዎችን መውሰድና ለአሁን በሕገ መንግሥቱና በብሔር ፌደራሊዝም ላይ የሚደረጉ መደበኛ ድርድሮችን ለሌላ ጊዜ ማቆየት እንደሚያስፈልግ የክራይስስ ግሩፕ ሪፖርት ይመክራል።

አማራና ኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ እየመከሩ ነው

በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ይገኛል። የውይይት መድረኩ በሁለቱም ክልሎች ባሉ ዩኒቨርስቲዎችበሚከሰቱ ግጭቶች ዙሪያ በመምከር የመፍትሄ ሃሳብ ለመጠቆም ያለመ ነው ተብሏል።

በተጨማሪም ውይይቱ በክልሎቹ ህዝቦች መካከል ያለውን የእርስ በርስ ግንኙነትና ትስስር ይበልጥ በማጠናከር ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ያስችላል ተብሎ ታምኖበታል።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ተቀራርበው በቅንጅት እንዲሠሩ እና የፖለቲካ ዓላማቸውን እና ተግባራቸውን በተለያዩ አካባቢዎች ለደጋፊዎችቻው እንዲያሳውቁ በር ከፋች ነው መባሉንም ሰምተናል።

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ሊቀ መንብር አቶ ዳውድ ኢብሳ እና የአማራ ማህበራዊ ራዕይ ሊቀመንር አቶ ስዩም መንገሻ የፖለቲካ ፓርቲዎቹን ወክለው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ የውይይት መድረኩ ፖለቲከኞች ከጥርጣሬ መንፈስ ወጥተው በቅንጅት እና በመግባባት መሥራት እንዲችሉ ያደርጋል ነው ያሉት።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በሁለቱም ክልሎች በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የሚስተዋለውን የተማሪዎች ሞት እና ግጭት ከምንጩ ለማድረቅ የበኩላቸውን ድርሻ ይወጣሉ ሲሉም ቅድመ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

ፕ/ት ሳህለወርቅ የዓመቱ 100 ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ሆነው ተመረጡ

የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ከ100 በፎርብስ መጽሔት የ2019 የዓለማችን ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች መካከል አንዷ ሆነው መመረጣቸው ታውቋል።

ዓለም ዐቀፍ ተቀባይነት ያለው ፎርብስ መጽሔት በየዓመቱ በሚያወጣው የዓለማችን ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች መካከል የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንቷ ሳህለወርቅ ዘውዴ ከመቶዎቹ ተጽዕኖ ፈጣሪዎቹ ውስጥ 93ኛ ደረጃን እንደያዙ አስታውቋል።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ከአህጉረ አፍሪካ ብቸኛዋ ሴት ተመራጭ እንደሆኑም ከመረጃው መገንዘብ ተችሏል:: በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ውስጥ በከፍተኛ ዲፕሎማትነት ለረዥም ዓመታት ሀገራቸውን በማገልገል አመርቂ ሥራ ያከናወኑ መሆኑ አይዘነጋም::

ኢትዮጵያ አርብ ዕለት በምታመጥቀው ሳተላይት 11ኛዋ የአፍሪካ ሀገር ትሆናለች

ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም የፊታችን አርብ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሳተላይት የምታመጥቅ መሆኑ ተረጋግጧል::ኢትዮጵያ ሳተላይት በማምጠቅ ከአፍሪካ 11ኛዋ ሀገር ትሆናለች ነው የተባለው።

ኢትዮጵያ ሳተላይት ለማምጠቅ በእጅጉ ዘግይታለች የሚለው መረጃ በአንጻሩ  የአፍሪካ ሀገራት እ.አ.አ በ1990ዎቹ መጨረሻ ሳተላይት ማምጠቅ እንደጀመሩ አረጋግጧል።

በዚህም መሠረት:-

ግብፅ – በ1998

ደቡብ አፍሪካ- በ1999

ሞሮኮ – በ2001

አልጀሪያ- በ2002

ናይጀሪያ- በ2003

ጋና- በ2017

አንጎላ – በ2017

ኬንያ፦ በ2018

ሩዋንዳ – በ2019

ሱዳን – 2019 ሳትላይት ያመጠቁ ቀዳሚ የአፍሪካ አስር ሃገራት ሆነው ተመዝግበዋል::

በዚህ መሠረት አንጎላ እ.ኤ.አ በ2017 ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሕዋ ያመጠቀቻት ሳተላይት ለአራት ወራት ያህል ብቻ አገልግላ ነው ሥራ  ያቆመች መሆኑ ታውቋል።  “አንጎሳት 1″በመባል የምትጠራው የአንጎላ ሳተላይት በወቅቱከካዛኪስታን ነበር ወደ ሕዋ የተላከችው ።

300 ሜትር ያህል የምትረዝመው የአንጎላ ሳተላይት ወደ ሕዋ ለመገናኛ አገልግሎት ለማዋል የተላከች ነበረችም ተብሏል። ሳታላይቷ የቴክኒክ እክል የገጠማት ከመጠቀች በኋላ ሲሆን፥ ተደጋጋሚ ሙከራ ቢደረግም ግንኙነቷ መቋረጡን ያሳወቀችው ሩሲያ ፤ ለአንጎላ በገባችው ዋስትና መሠረት ያለምንም ወጪ በ2020 ምትክ ሳተላይት እንደምትገነባላት ማረጋገጫ ሰጥታለች።

ኢትዮጵያ ከአራት ቀናት በኋላ አርብ ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓም (ከቻይና ታይዋን) ሳተላይት ልታመጥቅ ዝግጅቷን አጠናቃለች። ይህም ከአፍሪካ ሳተላይት በማምጠቅ 11ኛዋ ሀገር ያደርጋታል ነወ የተባለው።

ሳተላይቷ ታህሳስ 10 ቀን ከማለዳው 12 ሰዓት ከ21 ደቂቃ ስትመጥቅ በቀጥታ ሂደቱ በቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት ይተላለፋል ተብሎ ይጠበቃል።

LEAVE A REPLY