ዝም እላለሁ ግሩም ተክለሃይማኖት

ዝም እላለሁ ግሩም ተክለሃይማኖት

በግሩም ተ/ሀይማኖት
በምላስ ጦር ሲወጉኝ ቁስሌን ችዬ
መሸሽ መርጨ ነገርን ችላ ብዬ
ያውሩ ብዬ ተውኳቸው ምንም ላያመጡ
ኩስ ሲቀቡ ስሜን እኔነቴን ላይለውጡ
ዝም…….አሁንም ዝም…..
ባይነቅዝም አይጎዳም
ዝምታ ውስጥ ቃላት አለ
ማንበብ መተርጎም ለቻለ
ባይገባቸው መልዕክቱ
ባይታያቸው ውበቱ
የዝምታዬ ውስጠቱ
ዝምታ ውስጥ ጩኸት አለ
ብሶት ቁስለትን ያዘለ….
ዝምታ ውስጥ ንቀት አለ
በአመል ምግባራቸው የበቀለ
ዝምታ ውስጥ ፍርሃት አለ
ከሰው ምላስ የሸሸ የተከለለ
ዝምታዬ ውስጥ አለ ፈንጅ
እንደ አቶን እሳት የሚፋጅ
ታፍኖ እኔኑ የሚፈጅ……
.
.
ዝም አይነቅዝም ብዬ
ባሳለፍኩኝ ሁሉን ችዬ
ሞኝ ነው አሉኝ ተላላ
ፈርቶ ነው ይበሉ ወይም ሌላ
ዝምታ ውስጥ ሰላም አግኝቼ
የእፎይታ አድማስ ገንብቼ
ዝምታዬ ውስጥ ሰምጨ
ከእነሱ ግስንግስ አለም መሸሽን መርጨ
ዝም እላለሁ ዝምታ ለምጄ
ያሉትን ይበሉ ብዬ ፈቅጄ

ግንቦት 17/2001

LEAVE A REPLY