የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ታህሳሥ 17 ቀን 2011 ዓ.ም

የኢትዮጰያ ነገ ዜናዎች || ታህሳሥ 17 ቀን 2011 ዓ.ም

የሜቴክና የሕወሓት ቀኝ እጅ አዜብ አስናቀ በ5 ቢሊዮን ብር ሙስና ተከሰሱ

በቀድሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ በነበሩት ኢንጂነር አዜብ አስናቀ ላይ ከባድ የሙስና ክስ ተመስርቶባቸዋል።

የሕወሓት አፍቃሪና የኢኮኖሚያዊ ዝርፊያው ዋነኛ አስፈጻሚ እንደሆኑ የሚታሙትና በወሳኝ የሓላፊነት ቦታ ላይ ለዓመታት ሳይነሱ ቁጭ እንዲሉ የተደረጉት ወ/ሮ አዜብ አስናቀ በለውጡ ማግስት በዐቢይ አሕመድ ትዕዛዝ በፍጥነት ከቦታቸው ቢነሱም በቁጥጥር ስር ውለው በህግ ፊት አለመዳኘታቸው ብዙዎችን ሲያነጋግር ቆይቷል።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ሕግ ህዝብ ግነኙነት ሓላፊ አቶ ዝናቡ ቱኑ ኢንጂነር አዜብ ላይ የተመሰረተው ክስ ከ5.1 ቢሊዮን ብር ውል ጋር የተያያዘ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ታላቁ የህዳሴ ግድብ ውሃ የሚያርፍበትን 123ሺህ ሄክታር በላይ ስፋት የሪዘርቨር ክሊሪንግ እና የባዮማስ ዝግጅት ሥራ፣ ደን የመመንጠር፣ የማጽዳት እና ከግድቡ ስፍራ የማጓጓዝ ሥራን ለማስፈጸም፤ ከኢፌዲሪ ብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር  (ሜቴክ) የተጨማሪ እሴት ታክስን ሳይጨምር በብር 5.1 ቢሊዮን ብር የጋራ ውል ስምምነት እንዲፈጸም ማዘዛቸው ተረጋግጧል።

ይህ የስምምነት ውል፣ በተገባበት የስምምነት ጊዜ እና ሂደት ባለመፈጸሙ በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ማድረሱን አቶ ዝናቡ ጠቁመው፤ በዚህ መሠረት የቀድሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ሥራ አስፈጸሚ የነበሩት ኢንጅነር አዜብ አስናቀ እና ሌሎች የዚህ ወንጀል ድርጊት ተሳታፊ ናቸው የተባሉ 50 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ እንዲመሰረትባቸው አድርጓል።

ኢንጂነር አዜብ አስናቀ በአሁኑ ወቅት በቁጥጥር ሥር ስለመዋላቸው የተጠየቁት የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ሕግ ህዝብ ግነኙነት አቶ ዝናቡ ቱኑ፤ “በእሱ ላይ ምላሽ መስጠት አልችልም” ብለዋል:: ሆኖም አንዳንድ ፍንጮች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ግለሰቧን ከመሸጉበት መቀሌ በቁጥጥር ስር ለማዋል የፌደራል ፖሊስና የደህንነት አባላት ወደ ሰፍራው ከሁለት ቀን በፊት መጓዛቸውን ይናገራሉ።

በኢንጂነር አዜብ እስናቀ የክስ መዝገብ የቀድሞ የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኮለኔል ሙሉ ወ/ገብርኤል እንደሚገኙበት የጠቆሙ ምንጮች አብዛኛዎቹ ተጠርጣሪዎች ከአዲስ አበባና ከሥራ ገበታቸው የተሰወሩት ሕወሓት ከአራት ኪሎ ቤተመንግሥት በተገፋ የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት መሆኑ ገልጸዋል።

የአዳማ  ሙስሊሞች የተቃውሞ ሰልፍ በፀጥታ ኃይሎች ተበተነ

– በሌሎች ከተሞች ሙስሊሞች ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል 

በተለያዩ የአገሪቷ ክልልሎች በመስጅዶች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት የሚያወግዙ ሰላማዊ ሰልፎች በዛሬው ዕለት ተካሂዷል።

ባለፈው ሳምንት በሞጣ ከተማ በአራት መስጅዶች ላይ የደረሰውን ጥቃት ለማውገዝ ከተደረጉት ሰልፎች አብዛኛዎቹ የተካሄዱት በአማራ ክልል በሚገኙ ከተሞች መሆኑን ያገኘናቸው መረጃዎች ይጠቁማል።

ያለመንግሥት ፍቃድና የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እውቅና አልሰጠሁትም ያለው፣ የተቃውሞ ሰልፍ ከተካሄደባቸው ከተሞች መካከል ደሴ፣ መርሳ፣ ወልዲያ፣ ባሌ እና በደሌ ቀዳሚዎቹ መሆናቸውን ኢትዮጵያ ነገ ከተለያዮ አካባቢዎች መረጃ ሰብስባለች።

በሌላ በኩል በአዳማ ከተማ ሲካሄድ የነበረው የተቃውሞ ሰልፍ በመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች እንዲበተን መደረጉን በከተማዋ ነዋሪ የሆኑ ታማኝ ምንጮች ገልጸውልናል::

ለተቃውሞ ሰልፍ አደባባይ የወጡ ነዋሪዎች “የሃይማኖት ተቋማት መቃጠል መንግሥት የሚያሳየውን ቸልተኝነት ያሳያል”፣ “ለሁሉም የእምነት ተቋማት ጥበቃ ይደረግላቸው” እንዲሁም “ሚዲያዎች ያለ አድልዎ በሃይማኖት ተቋማት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ይዘግቡ” የሚሉ መፈክሮችን ይዘዋል ታይተዋል።

በደሴ ከተማ የተካሄደውን ሰልፍ ሲያስተባበሩ ከነበሩት መካከል አቶ ከማል ሁሴን “ይህ ድንገተኛ ጥቃት አይመስልም። ያን ያክል ቁጥር ያለው ህዝብ እየጨፈረ መስጅድ ሲወድም፣ የሚያስቆም መንግሥት የለም ወይ? ይሄ ሆነ ተብሎ ድንገተኛ አደጋ ለማስመሰል ተሞክሯል። እዚህ ያለው ህዝብ የክልሉ መንግሥትን ጥፋተኛ አድርጓል” ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

በጥቃቱ ንብረታቸው ለወደመባቸው ግለሰቦች የክልሉ መንግሥት ካሳ እንዲከፍላቸው እየጠየቁ ናቸው።

ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈለገችና በደሴ ከተማ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የተሳተፈች ወጣት፤ የተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ በሰላም መጠናቀቁን ጠቁማ፤ “ጥቃቱ ሲፈጸም መንግሥት ባፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ለምን ተሳነው?” የሚለው የበርካቶች ጥያቄ ነው ስትል የሙስሊሙን ኅብረተሰብ ስሜት ገልጻለች።


ሁለት ቀን አዲስ አበባ የቆዮት፣ ፕ/ት ኢሳያስ አፈወርቂ ወደ ኤርትራ ተመለሱ

ከትናንት በስቲያ ጀምሮ በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ሲያደርጉ የቆዩት የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ዛሬ ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።

ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር ከመወያየታቸው በተጨማሪም በአዳማ፣ ቢሺፍቱ እና ዱከም የሚገኙ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎችን ጎብኝተዋል። ትናንት ደግሞ መሪዎቹ በጋራ በአዲስ አበባ አዲስ ለሚገነባው የኤርትራ ኤምባሲ ህንፃ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።

በአሁኑ የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጉብኝት፣ ሀገራቱ በርካታ የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር የሚያስችላቸው አቅም እንዳላቸው ተመልክተናል፤ ይህንንም ለመጠቀም ተወያይተናል ሲሉ ተናግረዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ።

” የአሁኑ የሁለት ቀናት ጉብኝቴ የሁለት ወራት ቆይታን ያህል ነው የተሰማኝ “ያሉት የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፤ ጉብኝቱ በበርካታ በድንገቴ አስደሳች ሁነቶች የተሞሉ ነው ካሉ በኋላ ለልዑካቸው ለተደረገው አቀባበልም ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ምስጋና አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንድአርጋቸውን ጨምሮ የተለያዩ የመንግሥት የሥራ ሓላፊዎች ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ልዑክ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አሸኛኘት አድርገውላቸዋል።


የዮንቨርስቲ ተማሪዎች ከ4 ሰዓት በላይ እንዳያመሹ መመሪያ ወጣ

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ከማደሪያ ክፍላቸው ውጪ የሚኖራቸው ቆይታ ከምሽቱ አራት ሰዓት እንዳያልፍ፣ ይህም በተቆጣጣሪዎች ወይም ፕሮክተሮች በየዕለቱ ክትትል እንዲደረግ መመሪያ ወጥቷል።

በተጨማሪም ዩኒቨርስቲዎች፣ ተማሪዎች ከንጋት 12:00 ሠዐት በፊትና ከምሽት 1:00 ሰዓት በኋላ ከግቢ ውጪ እንዳይገኙ የተወሰነ ሲሆን፤ ይህንንም በግቢዎቹ ጥበቃ የፈረቃ ሓላፊዎች፣ የፌደራል እና የክልል ፀጥታ አካላት በዚህ ላይ መረጃ ተሰጥቷቸው እንዲያስፈፅሙ መወሰኑን የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል።

በሚኒስቴሩ የኮሙኑኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ደቻሳ ጉርሙ ይህ ውሳኔ “ጊዜያዊ ነው” በማለት ችግር ያጋጠማቸው የትምህርት ተቋማት ሰላም ከተረጋጋ እንደሚነሳ አረጋግጠዋል::

ሚኒስቴሩ ያስቀመጠው የሰዓት ገደብ ለጥንቃቄ የተደረገ ነው ያሉት ሓላፊው፤ በደብረ ብርሃንና በወለጋ ዩኒቨርስቲዎች የተገደሉ ሁለት ተማሪዎች ከዩኒቨርስቲዎቹ ቅጽር ግቢ ውጪ መሆኑንም አስታውሰዋል።

ወለጋ ዩኒቨርስቲ ሞቶ የተገኘው ተማሪ የተገደለው አሳቻ ሰዓት መሆኑን በመጥቀስ፤ ጥፋተኛ ተብለው ከዩኒቨርስቲው የሚታገዱ ወይም የሚባረሩ ተማሪዎች ሌሎች አማራጮችን እንዳይጠቀሙ በሚቻለው አቅም ሁሉ ለተማሪዎቹ ሕይወት ሙሉ ጥንቃቄ ለማድረግ በሚል የተወሰነ እንደሆነም  ተናግረዋል።

በያዝነው ዓመት በዩኒቨርስቲ ውስጥ በተነሳ ግጭት ከሞቱት ተማሪዎች መካከል አብዛኞቹ በግቢው ውስጥ እንዲሁም በማደሪያ ክፍላቸው አካባቢ መሆኑን የተጠየቁት አቶ ደቻሳ “ግቢ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ለማሻሻል የፀጥታውን ሁኔታ አጠናክረናል፤ ውጪ ደግሞ እንዳይከሰት የተሻለ ጥንቃቄ ለማድረግ ይህ ውሳኔ ተወስኗል” ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በዩኒቨረስቲ ግቢ ውስጥ የተሻለ ጥበቃ አለ የሚሉት አቶ ደቻሳ የዩኒቨርስቲዎችን ሰላም ለማረጋገጥ በዩኒቨርስቲዎች በፌደራል ፖሊስ የሚካሄደው ጥበቃ ለውጥ እያመጣ ነው ካሉ በኋላ ለዚህም በአስረጅነት አዳዲስ ግጭቶች እየተነሱ አለመሆኑን ጠቅሰዋል።

በአማራና በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎችን ሰላም ለማጠናከር የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የሚያስተባብረው የዩኒቨርስቲ የቦርድ አመራሮችና ባለስልጣናት ከአካባቢ ሓላፊዎችና የአገር ሽማግሌዎች የተካተቱበት ኮሚቴ ተዋቅሮ፣ ሁሉንም የሚመለከታቸውን አካላት በማወያየት በዩኒቨርስቲዎች ዘላቂ ሰላም ማምጣት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እየሠሩ እንደሚገኙም አብራርተዋል

በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ በየትኛውም ደረጃ ያለ ግለሰብ የፀጥታ ችግርና ተጠያቂ የሚሆን ከሆነ ተጠያቂ እናደርጋለን ያሉት አቶ ደቻሳ፤ ሰላማዊ የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ አባላት ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ከዩኒቨርስቲ ለቅቀው ወደቀያቸው የሄዱ ተማሪዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ነበሩባቸው ተቋማት እንዲመለሱ እንፈልጋለን ብለዋል::

የፀጥታ ችግር የታየባቸው 22 ዩኒቨርስቲዎች ተለይተው እየተሠራ ነው ያሉት አቶ ደቻሳ በእነዚህ ዩኒቨርስቲዎች የተወሰዱ የማስተካከያዎች እርምጃዎችን በተመከለተ የተጠቃለለ መረጃ እጃቸው ላይ እንደገባ እንደሚያስታውቁ ተናግረዋል። በተያያዘ ዜናም በግጭቶች ምክንያት ተቋርጦ የነበረው ትምህርት በሁሉም የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ከሚቀጥለው ሳምንት ይጀመራል ተባሏል።


በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የጉዞ እቅድ መተግበሪያ ካርታ ዛሬ ይፋ ሆነ

በኢትዮጵያ የሕዝብ ትራንስፖርትን ለማሻሻል ይረዳል ተብሎ የታመነበት የጉዞ እቅድ መተግበሪያ (ዲጂታል ማፒንግ) ይፋ ሆነ።

የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ መፍትሄ ይዞ መንቀቀሳቀስ እንደሚገባ ካርታው ይፋ በተደረገበት ወቅት ተናግረዋል።

ከከተማ መስፋፋት እና የህዝብ ቁጥር እያደገ መምጣት ጋር ተያይዞ የአዳዲስ አካባቢዎች እና መኖሪያ ሰፈሮች መፈጠራቸውን ያስታወሱት ሚኒስትሯ፤ አዳዲስ የጉዞ መስመሮች መፈጠራቸውን እና በዚህ ሳቢያም የአውቶቡስና የታክሲ መስመሮችን ለማወቅ፣ ብሎም ለመጠቀም ፈታኝ እየሆነ መምጣቱን ነው የገለፁት። ይህን ችግር ለመቅረፍም ከናይሮቢ (ዲጂታል ማታተስ) እንዲሁም ካይሮ (የካይሮ ትራንስፖርት) ተሞክሮ በመውሰድ የአዲስ አበባን የህዝብ ትራንስፖርት የጉዞ እቅድ መተግበሪያ ካርታ (ዲጂታል ማፕ) ላይ ማስፈር መቻሉን አስታውቀዋል።

የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎትን ተደራሽ ከማድረግ አንጻር፣ በተለይም የህዝቡ የትራንስፖርት ተጠቃሚነትና የማጓጓዝ አቅም በየዓመቱ በአማካይ በ9 ነጥብ 3 በመቶ እድገት ማሳየቱ ተጠቅሷል። ሆኖም የብዙሃን ትራንስፖርት አቅርቦቱ ካለው ፍላጎት አንጻር ውስን እንደነበር በመድረኩ ላይ ተነስቷል።

የጉዞ መተግበሪያውን ለማከናወን በዋናነት የትራንስፖርት ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ፣ ከወርልድ ሪሶርስ ኢንስቲቲዩት እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን፤የአዲስ አበባ የቀላል ባቡር፣ የአንበሳ የከተማ አውቶቡስ፣ የሸገር የብዙሀን ትራንስፖርት እና የከተማ የሚኒባስ ታክሲ የአገልግሎት መስመር መነሻ፣ የመተላለፊያ እና የመዳረሻ እና ፌርማታ አካባቢ ቦታዎች መረጃን በአካል ተገኝቶ በመሰብሰብ ለማካተት ተችሏል ነው የተባለው።

ዛሬ የተጀመረው የጉዞ እቅድ መተግበሪያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከወርልድ ሪሶርስ ኢንስቲቲዩት እና በየክልሉ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመሆን፣ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከተሞች እንዲስፋፋ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

LEAVE A REPLY