ጠ/ሚ/ር አብይ ስልጣናቸውን “ሊነጠቁ “አይገባም … || ታምሩ ገዳ

ጠ/ሚ/ር አብይ ስልጣናቸውን “ሊነጠቁ “አይገባም … || ታምሩ ገዳ

በኦሮሚያ ክልል፣ ወለጋ፣ የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የሆኑ ሀያ ሰባት ወጣቶች በታጣቂዎች ታግተው ከተወሰዱ ከሀምሳ ሶስት ቀናት በላይ ቢያስቆጠሩም በወጣቶቹ ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ዶ/ር አብይ አህመድ ስልጣናችውን እና “ተጽኖ ፈጣሪ ክህሎታቸውን” ለመጠቀም አለመፈለጋቸው ወይም ችላ ማለታቸው በበርካታ ኢትዮጵያኖች ዘንድ ትልቅ ቅሬታ መፍጠሩ ተስተውላል።

ጠቅላይ ሚኒስተሩ የሚመሩት መንግስት ባለስልጣናት ሰለ የወጣት ተማሪዎቹ መታገትን በተመለከተ የተለያዩ መግለጫዎችን ቢሰጡም “ማየት ማመን ነው” እንዲሉ የአደጋው ቀዳሚ ተጠቂ የሆነት የወጣት ተማሪዎቹ ቤተሰቦች መግለጫዎቹ ልባቸውን ማረስረስ ቀርቶ በተቃራኒው ጥርጣሬያቸውን አጉልቶት ከማይፈልጉት የስጋት እና የጭንቀት ፍልሚያ ውስጥ እንዲገቡ አስገድዷቸዋል።

ታዲያ የአገሪቱ ጠ/ሚ/ር ፣ የጨቅላ ህጻናት ልጆች አባት፣ በቅደሙ ንግግሮቻቸው በታዋቂው ታይምስ፣በኒው አፍሪካ እና መሰል መጽሔቶች ዘንድ በአለማችን ሆነ በአፍሪካ አህጉራችን “ተጽእኖ ፈጣሪ/ influential people in the world 2019, “መሪዎች እና ታዋቂ ሰዎች መካከል ስማቸው ለመጠራት የበቃው፣ ለመገናኛ ብዙሐናቱ እና ለመረጃዎች ብዙ እሩቅ ያልሄኑት ዶ/ር አብይ አህመድ በዚህ ቀውጢ እና የጭንቀት ወቅት ከቤተመንግስታቸው ሰሜናዊ አቅጣጫ አራት መቶ ሰማኒያ ዘጠኝ ኪሜ ርቀት(ባህር ዳር ከተማ ) ላይ መሪር እንባ የሚያለቅሱት ወላጆችን ቢቻል በአካል በጥያራ አማካኝነት በረር ብለው በአካል በመገኘት ፣ካልሆነም ከቢሯቸው ድረስ አስጠርተው፣ ይህም ካልሆነ ሁነኛ እና ነገር አዋቂ ባለስልጣናትን ልከው ለሳምንታት ደብዛቸው ፣ድምጻቸው ስለጠፋው ወጣት ተማሪዎች ጉዳይ በምስጢርም ይሁን በግልጽ ለመወያየት የተዘጋ እና ድቅድቅ ጨለማ የወረረው በሩን ለመክፈት ለምን ትሳናቸው? ።

በዚህ የብሔራዊ፣ የሰብአዊ የሐዘን እና የውርደት ወቅት ደምቢዶሎ ላይ ደብዛቸው ለጠፋው ወጣት ተማሪዎቹ ሆነ የደም እምባ ለሚያነቡት ወላጆቻቸው ልባቸውን ሊያረጋጋ የሚችለው ነገር የመናኛ የካድሬዎች ሽንገላ እና ለጋዜጠኞች ሳይቀር የሚሰጡት ማስፈራሪያዎች አለመሆኑን ሁሉም ወገን ጠንቅቆ አውቆታል። ዶ/ር አብይ አህመድም ቢሆኑ በሁኔታው ዙሪያ ፈጥነው እውነታውን ከወጣት ተማሪዎቹ ቤተሰቦች ጋር ለመነጋገር አለመቻላቸው ፓርቲያቸው የሰጣቸውን የጠ/ሚ/ርነት ስልጣን ፣እና ፈጣሪ ያደላቸው “ተናግሮ የማሳመን፣አልቅሶ የማስለቀስ፣ስቆ የማስጨብጨብ” ክህሎት እና መክሊታቸውን አይናቸው እያየ ለእርያዎች አሳልፎ ከመስጠት አይተናነስም።

ከዛሬ አንድ አመት ከዘጠኝ ወራት በፊት አብዛኛው ህዝቡ በይሁንታ፣ ፈጣሪም በጸጋው የሰጦትን “ሙሴ ያው” ተልእኮንም ቢሆን ዛሬ ቀይ ምንጣፍ ቢያነጥፉላቸው ፣ነገ ጎራዴ መዘው ከሚፋለሙ ይል ስልጣን ወንበሮትን በኃይል ለመንጠቅ ከሚያሴሩ ፣የእውነተኛ ዲሞክራሲ መንፈስ ያልሰረጸባቸው አንዳንድ የዘመኑ አጭበርባሪ ፓለቲከኞች ጋር ደፋ ቀና ማለት ሳይሆን አፈሩን ያቅልላቸው እና “በውድቀቴ እና በከፍታዬ በጸሎቷ ከጎኔ አልተለየችኝም ነበር..” ከሚሏቸው ከወላጅ እናቶት እኩል ዛሬም ሆነ ነገ ከጎኖዎት የማይለዩት፣ስለ እርሶም ሆነ ስለቤተሰቦት ስኬት በጎ በጎውን የሚመኙት እነዚያ የደምቢ ዶሎ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች፣ ወላጆቻቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን አይዘንጓቸው።

የምስኪን ወላጆች እንባን ማበስ በፈጣሪም ይሁን በፍጡራኑ ዘንድ ትልቅ ዋጋ ያሰጣል። እርሶም ቢሆን በዚህ የጭንቀት፣ የውዥንብሮች እና የመላምቶች ጋጋታ የበዛበት ወቅት ከዝምታዎት ድባብ ወጥተው እንደ የአንድ ታላቅ፣ ገናና አገር እና ህዝብ መሪ፣ እንደ አንድ ወላጅ አባት ማድረግ እና ማለት የሚገባዎትን እንዲችሉ የኢትዮጵያ እና የህዝቦች አምላክ ይርዳዎት።

LEAVE A REPLY