በ451 ሚሊዮን ብር የተገነባው የገናሌ ዳዋ III ግድብ ዛሬ ተመረቀ

በ451 ሚሊዮን ብር የተገነባው የገናሌ ዳዋ III ግድብ ዛሬ ተመረቀ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ እንዲሁም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብረሃም በላይን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሓላፊዎች ተገኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር “የጀርመነውን ጨርሰን ሪባን እንቆርጣለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም ብለን ነበር፤ የዛሬው የገናሌ ዳዋ III የውሃ ኃይል ማመንጫ ምረቃ የዚህ አንድ ማሳያ ነው”ከማለታቸው ባሻገር ግድቡ በመመረቁ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲሁም ለባሌ እና ጉጂ ዞን ነዋሪዎች እንኳን ደስ አላችሁ፣ እንኳን ደስ አለን በማለት መልእክት አስተላልፈዋል።

ዛሬ የተመረቀው ግድብ ከኃይል ማመንጨት በተጨማሪ በመስኖ ልማት በርካቶችን የመመገብ አቅም አለው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ  አሕመድ “ኃይል ወሳኝ ፍላጎታችን ነው፤ ይህንን ለማሳካት የሚመለከታቸው ተቋማት ለሚሠሩት ሥራ መንግሥት በቅርበት አመራር ይሰጣል” ነው ያሉት። አሁን የተሠራውን መመረቅ ብቻ ሳይሆን ትኩረታችን የገናሌ ዳዋ ስድስት የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድብን እንዴት መጀመር እና መጨረስ አለብን? የሚለው ላይ መሆን አለበት ሲሉም ማስጠንቀቂያ አዘል መልእክት አስተላልፈዋል። ዶክተር ዐቢይ የገናሌ ዳዋ ስድስት ከ1 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ያላነሰ ወጪን የሚጠይቅ እንደሆነም ገልጸዋል።

በግድቡ ልማት ላይ በርካታ የውጭ ባለሀብቶች ለመሳተፍ ፍላጎት አሳይተዋል፤ ነገር ግን መንግስት ከኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች ጋር የማልማት ፍላጎት አለው የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ ስለዚህ የኢትዮጵያ ባለሀብቶች ከመንግሥት ጋር በመሆን በሽርክና የገናሌ ዳዋ ስድስት የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድብን እንዲያለሙ ጥሪ አቅርበዋል።

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፤ ኢትዮጵያ ዝቅተኛ የኃይል ተደራሽነት ካላቸው አገራት አንዷ ነች ያሉ ሲሆን፤ ይህንን ለማሻሻል የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል። አሁን ላይ ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ኃይል ተደራሽ የሆነው 45 በመቶ ለሚሆነው ብቻ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ በዛሬው እለት የተመረቀውም ይህንን በማሻሻል ረገድ የራሱን ድርሻ እንዳለው ነው ያመላከቱት።

ሚኒስትሩ በታዳሽ ኃይሎች ላይ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን በመግለፅ በተለይም በተፋሰሶች ላይ የአዋጭነት ጥናት እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 4 ሺህ 400 ሜጋ ዋት እያመረተች መሆኑን በማንሳት፤በቀጣይም የህዳሴ ግድብና ኮይሻን ጨምሮ ከሌሎች ታዳሽ ኃይሎች 7 ሺህ 300 ሜጋ ዋት ለማምረት እየሠራች ትገኛለች ነው ተባለው።

የህዳሴ ግድብ በቀጣይ ዓመት መጨረሻ ላይ በሁለቱ ተርባይኖቹ ኃይል ማመንጨት እንዲጀምር እንዲሁም በ2015 ዓ.ም የግድቡ ግንባታ ሙሉ በሙሉ እንዲጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን እና መንግሥትም ተገቢውን ድጋፍ እና ክትትል እንዲያደርግም በመነገር ላይ ነው።

በዛሬው እለት የተመረቀው የገናሌ ዳዋ III የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድብ 254 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅምእና 2 ነጥብ 57 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ የመያዝ  አቅም እንዳለው ከተደረገው ገለጻ መረዳት ችለናል።

የኃይል ማመንጫው የተገነባው ዝናባማ በሆነው በኦሮሚያ ክልል በጉጂና ባሌ ዞንኖች መካከል መሆኑ የማመንጨት አቅሙን ቋሚና የተሻለ ያደርገዋል ተብሎ ታምኖበታል። ለግንባታው 451 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ የተደረገ ሲሆን፣ 60 በመቶው ከቻይናው ኤክዚም ባንክ በብድር ፣ እንዲሁም ቀሪው 40 በመቶው ደግሞ በመንግሥት ወጪ የተሸፈነ ነው።

ይህ ፕሮጀክት በ4 ዓመት እንዲጠናቀቅ ውል ታስሮ የነበረውበ2003 ዓ.ም ቢሆንም የግንባታው አካል የሆነ 2 ኪሎ ሜትር ዋሻ ቁፋሮ ወቅት ባጋጠሙ አለቶች እንዲሁም ከካሳ አከፋፈል ጋር  በተያያዙ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እስካሁን ድረስ ሊዘገይ መቻሉ ታውቋል።

LEAVE A REPLY