በቴፒው ግጭት የሞቱት ሰዎች ቁጥር 8 ደርሷል ከሞቱት ውስጥ የልዩ ኃይል አባላት...

በቴፒው ግጭት የሞቱት ሰዎች ቁጥር 8 ደርሷል ከሞቱት ውስጥ የልዩ ኃይል አባላት ይገኛል

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የዞንነት የመዋቅር አደረጃጀት ጥያቄን መሠረት አድርጎ አለመረጋጋት ውስጥ በነበረችው ቴፒ ከተማ፤ ጥር 26/2012 ዓ.ም የልዩ ኃይል አባል መገደላቸውን ተከትሎ በተቀሰቀሰው ግጭት ቢያንስ 8 ሰዎች መሞታቸውን  የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

አንድ የቴፒ ከተማ ነዋሪ ረቡዕ ከሰዓት በኋላ በተከሰተው ግጭት 8 ሰዎች መሞታቸውን እና ቢያንስ 12 የሚሆኑ ነዋሪዎች ደግሞ የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸው ለቢቢሲ ገልጿል። በሌላ በኩል ፋና ብሮድካስቲንግ የደቡብ ክልል የፀጥታ እና አስተዳደር ቢሮን ጠቅሶ ባለፉት 2 ሳምንታት ቴፒ ከተማን ጨምሮ በተፈጠረው ግጭት የ7 ሰዎች ሕይወት አልፏል ሲል ዘግቧል።

ሌላኛው የቴፒ ነዋሪ ደግሞ ለቢቢሲ ረቡዕ ዕለት ለተፈጠረው ችግር ዋነኛ መንስዔው ከአንድ ወር በፊት በአካባቢው የተፈጠረው የጸጥታ ችግር እንደሆነ ጠቁሞ፤ “ከአንድ ወር በፊት 1 ልጅ በአካባቢው ተገድሏል። ይህንን ተከትሎ በቴፒ የአገልግሎት ተቋማትና መንገዶች ለ21 ቀናት ተዘጋግተው ነበር” ብሏል:: ይህ የቴፒ ነዋሪ ረቡዕ ዕለት ግን የተዘጉት አገልግሎቶች እንደ አዲስ ተከፍተው ሰውም ወደ መደበኛ እንቅስቃሴው መግባት ጀምሮ እንደነበርና ነገር ግን ከቀኑ 10 ሰዓት አካባቢ የአካባቢው የልዩ ኃይል አዛዥና አንድ ሌላ የልዩ ኃይል አባል ወደ አንድ ምግብ ቤት በማምራት፤ ምግብ በመመገብ ላይ የነበረን ወጣት ‘ትፈለጋለህ’ በማለት መጥራታቸው በአካባቢው ግጭት አንዲቀሰቀስ አድርጓል ነው የተባለው።

“በዚህ ወቅት አለመግባባት ተፈጥሮ ልጁ ሲቪል ወደ ለበሰው የልዩ ኃይል አዛዥ በማምራት በስለት ወግቶት ሸሸቶ አመለጠ” በማለትም የግጭቱን መነሻ የአካባቢው ነዋሪ ተናግሯል። በስለት የተወጋው ጸጥታ አስከባሪ ኃይል አባል ሕይወቱ ማለፉን እና ከዚያ በኋላ በተወሰደ እርምጃ የተቀሩት ሰዎች ሕይወት ማለፉን እና ሰዎች መቁሰላቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ጠቁመዋል።

የሸካ ዞን ፕሬስ ሴክሬታሪያት አቶ አስማማው ኃይሉ ለቢቢሲ  ሲናገሩ ሟች የሃምሳ አለቃ ዘማች ቁንሲል መሆናቸውን እና በደረሳቸው ጥቆማ መሰረት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል በሚንቀሳቀሱበት ወቅት በጥይት ተመትተው ተግድለዋል ብለዋል። የሃምሳ አለቃው የተገደሉት ቆጫ በር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ አደባባይ ላይ ነው።

አቶ አስማማው ጨመረው እንደተናገሩት፤ ክልሉ የመዋቅር ጥያቄን አልቀበልም ብሎ ምላሽ ሰጥቶ እንደነበረ  አስታውሰዋል:: ‘የዞን አስተዳደር ጥያቄያችን ይመለስልን’ የሚለው የነዋሪው ጥያቄ ለጸጥታ መደፍረስ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ። ጥያቄው ለዓመታት የዘለቀ ነው የሚሉት ነዋሪዎቹ በቴፒ ወረዳ ዙሪያ ያሉትን 22 ቀበሌዎች ጨምሮ የአስተዳደር መዋቅሩ ወደ ዞን ከፍ እንዲል የነዋሪዎች ጥያቄ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከቅርብ ወራት በፊትም የሰላም ሚንስትሯና የክልሉ ገዥ ፓርቲ ሊቀ መንበር በሥፍራው ተገኝተው ከሕዝቡ ጋር ተወያይተው ምላሽ እንደሚሰጥበት ቃል ገብተው ቢሄዱም እስካሁን ምላሽ አለማግኘታቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

LEAVE A REPLY