ታከለ ኡማ የ20/80 ቤቶችን አስረክበናል ሲሉ የተሳሳተ መግለጫ ሰጡ

ታከለ ኡማ የ20/80 ቤቶችን አስረክበናል ሲሉ የተሳሳተ መግለጫ ሰጡ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ከንቲባ ታከለ ኡማ ባለፈው አመት የካቲት ወር ማገባደጃ ለባለ እድለኞች እጣ ከወጣባቸው 32 ሺህ 653 13ኛው ዙር የ20/80 የጋራ መኖርያ ቤት ኮንደሚኒየሞች፤ ለባለእድለኞች ምንም የማስተላለፍ ሥራ ሣይሠራ  “አብዛኞቹን ቤቶችየማስተላለፍ ሥራ ተጀምሯል፤ ርክክብም እየተፈጸመባቸው ነው” ብለው መናገራቸው ከፍተኛ መደናገርና ቅሬታ አስነሳ።

የጋራ መኖርያ ቤቶች እጣ ከወጣባቸው በኋላ የኦሮሞ መብት ተሟጋች ነን በሚሉ ግለሰቦች ፣ “ቤቶቹ የተሠሩት የኦሮምያን ወሰን አልፈው ነው ፣ ቤቶቹ ሢሠሩ ለተነሱ አርሶ አደሮች የተከፈለው ካሳም በቂ አልነበረም” በሚል ባስነሱት ተቃውሞ ቤቶቹ ለባለ እድለኞች እንዳይተላለፉ መደረጉ አይዘነጋም።

የኦሮምያና አዲስ አበባን የወሰን ጉዳይ እንዲፈታ የመፍትሄ ሀሳብ የሚያቀርብ ኮሚቴ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ቢቋቋምም ፤ እዚህ ግባ የሚባል ውጤት አላመጣም። እነዚህ አዝጋሚ ሁኔታዎች ባሉበት ምክትል ከንቲባ ታከለ የ20/80 ቤቶቹ እየተላለፉ ነው ማለታቸው ባለ እድለኞቹን የመንግስት ቢሮዎችን ማንኳኳት እንዲጀምሩ አድርጓቸዋል ተብሏል።

ምክትል ከንቲባው ተመሳሳይ ይዘት ያለው መግለጫ ሁለት ጊዜ ያህል በኣአደባባይ ስጥተዋል። መጀመርያ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ፊት ቀርበው የአስተዳደሩን የሥራ አፈጻጸም ሲያቀርቡ፤ በአዲስ አበባና በኦሮምያ ክልል የአስተዳደር ወሰን ችግር ምክንያት ያልተላለፉት የ20 /80 የጋራ መኖርያ ቤቶች ዘጠኝ ሺህ ብቻ እንደሆኑ ገልጸዋል። ከሳምንት በፊት ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ላይ ቀርበው በሰጡት ቃለ መጠይቅ ላይ በ13ኛው ዙር እጣ ከወጣባቸው የ20/80 የጋራ መኖርያ ቤቶች ውስጥ ከዘጠኝ ሺህ ቤቶች ውጭ ሌሎቹ ቤቶች ላይ መንግስት የማስተላለፍ ሥራን እየሠራ እንደሆነ የሚያሳይ መልእክት ያለው ነገር ተናግረው ነበር።

ይሄን ተከትሎም ባለፈው አመት እጣ የወጣባቸው የቤቶች20/80 የጋራ መኖርያ ቤት እድለኞች ተደራጅተው ለመንግስት ጥያቄን ማቅረብ ጀምረዋል። ከቤት እድለኞቹ መካከል ከሶስት መቶ በላይ የሆኑት ተደራጅተው እሮብ እለት በአዲስ አበባ የቤቶች አስተዳደርና ልማት ቢሮ ተገኝተው ቅሬታቸውንና ጥያቄያቸውን ማቅረባቸውን ዋዜማ ራዲዮ ዘግቧል።

የቤቱ ባለ እድለኞች ለቤቶች አስተዳደር ቢሮው ያቀረቡት ጥያቄ ፣ ” የ20/80 ቤቶቹ ለኛ ለባለእድለኞቹ ሳይተላለፉ በምክትል ከንቲባው እየተላለፉ እንደሆነ የተናገሩበት መነሻው ምንድነው? የከተማ አስተዳደሩ የበላይ ባለስልጣን እንዲህ አይነት መረጃ ከሰጡስ እንዴት ለኛ እስካሁን እንዴት ጥሪ አልተደረገም ? ችግር አለባቸው የተባሉት ዘጠኝ ሺህ ቤቶችስ ተለይተው ታውቀዋል ወይ ? በትክክልስ መች ነው ቤቶቹን የከተማ አስተዳደሩ የሚያስረክበን ? ” የሚሉት ይገኙበታል።

እሮብ እለት በአዲስ አበባ የቤቶች አስተዳደርና ልማት ቢሮ ሓላፊን አግኝተው ማነጋገር እንዳልቻሉ የገለጹት ቅሬታ አቅራቢዎች በቀጣይ ሳምንት አርብ የካቲት 6 ቀን 2012 አ.ም የከተማው ከፍተኛ ባለስልጣናትና የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት ቅሬታ አቅራቢዎቹም ጥያቄያቸውን አቅርበው ውይይት እንደሚያደርጉ እንደተነገራቸውም ነው የጠቆሙት።

ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ከጋራ መኖርያ ቤቶቹ ጋር በተያያዘ የተዛነፈ መረጃ መስጠት ለምን እንደፈለጉ ግልጽ አይደለም።

ስለ 20/80 ቤቶቹ መተላለፍ ብቻም ሳይሆን የልማት ተነሽ ለተባሉ አርሶ አደር ቤተሰቦች ለካሳነት የተሰጡት ቤቶች መጠንንም ከእጥፍ በላይ ቀንሰው ነው ሲገልጹ የተሰሙት።

ተጠሪነቱ ለእርሳቸው የሆነው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ግብር እና የአርሶ አደር ልማት ኮሚሽን የዚህ አመት እቅዱ 23 ሺህ የጋራ መኖርያ ቤቶችን ለልማት ተነሽ ለተባሉ አባወራዎች እስከ ቤተሰቦቻቸው መስጠት መሆኑን ዋዜማ ራዲዮ በጽሁፍ የተደረገፈ መረጃውን መሠረት አድርጎ ዘግቧል።

LEAVE A REPLY