በኮሮና ቫይረስ በአንድ ቀን 97 ሰዎች ሞቱ፤ የሃገራት ጥንቃቄ ቀጥሏል

በኮሮና ቫይረስ በአንድ ቀን 97 ሰዎች ሞቱ፤ የሃገራት ጥንቃቄ ቀጥሏል

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በቻይና ትናንትና በኮሮና ቫይረስ ብቻ በአንድ ቀን 97 ሰዎች ሞቱ:: ይህ ቁጥር እስካሁን በቀን ውስጥ ከተመዘገበው ከፍተኛው እና አስከፊው ነው ተብሏል።

በኮሮና ቫይረስ የሟቾች ቁጥር 908 የደረሰ ቢሆንም፣ በየቀኑ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ግን ለውጥ አላሳየም እንዲያውም መረጋጋት አሳይቷል እየተባለ ይገኛል። በአጠቃላይ በቻይና በቫይረሱ የተያዙት ሰዎች ቁጥር 40 ሺ 171 የደረሰ ሲሆን ፤ 187 ሺ 518 ግለሰቦች ደግሞ በቅርብ የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው ነው።

የዓለም ዐቀፉ የጤና ድርጅት ቫይረሱ ያለበትን ሁኔታ የበለጠ ለመመርመር በቅርቡ የህክምና ባለሙያዎችንና ተመራማሪዎችን የያዘ ቡድን ልኳል። ከቻይና መንግሥት የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው እስካሁን ድረስ በቫይረሱ የተያዙ 3 ሺ 281 ግለሰቦች ህክምና ተደርጎላቸው ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል።

የቻይና አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግና በተጨማሪም ቫይረሱ እንዳይዛመት ተብሎ ሥራ እንዲቋረጥ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም፤ በዛሬው ዕለት ሚሊዮኖች ወደ ሥራ ገበታቸው ተመልሰዋል። ነገር ግን የሥራ ቦታ እንደ ቀድሞው አይሆንም፤ ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላበት፣ እንዲሁም የሥራ መግቢያና መውጪያ ሰዓት እንደ አስፈላጊነቱም የሚቀያየር ይሆናል፤ አንዳንድ የሥራ አይነቶችም ለተወሰነ ጊዜ ተዘግተው ይቆያሉ ተብሏል።

በኮሮና ቫይረስ የሟቾች ቁጥር በጎርጎሳውያኑ 2003 የተነሳው የሳርስ ወረርሽኝ ከቀጠፈው ህይወት እንደበለጠ ተገልጿል። የቫይረሱ መነሻ በሆነችው ሁቤ ግዛት የሟቾች ቁጥር 780 እንደደረሰና ቅዳሜ ዕለትም በግዛቷ 81 ሰዎች እንደሞቱ የጤና ባለሙያዎች አስታውቀዋል። ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው በሁቤዋ ግዛት ውሃን ከተማ ሲሆን፤ የአስራ አንድ ሚሊዮን ህዝብ መኖሪያ የሆነችው ውሃን ለሳምንታትም የጉዞ፣ የመውጣትና የመግባት እግድ ተጥሎባታል።

ከሳምንት በፊት ዓለም  ዐቀፉ የጤና ድርጅት የኮሮና ቫይረስን የዓለም የጤና ስጋት ነው ብሎታል። ቫይረሱ ከቻይና ወደ 27 አገራት የተዛመተ ቢሆንም ፣ ከቻይና ውጭ ያለው የሟቾች ቁጥር ሁለት ነው፤ አንደኛው በሆንግኮንግ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በፊሊፒንስ መሆኑ ታውቋል።

በተጨማሪም ወደ ሆንግ ኮንግ የገባች መርከብ መንገደኞችና ሠራተኞቹ በጥርጣሬ ምክንያት በለይቶ ማቆያ ለተወሰነ ጊዜ እንዲቆዩ ቢደረግም ከምርመራ በኋላ እንዲወርዱ ተፈቅዶላቸዋል። ይህቺ መርከብ እንድትለይ የተደረገችው ከዚህ ቀደም በአንዲት የጃፓን መርከብ ላይ ስምንት ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ተይዘው በመገኘታቸው ነው።

በጃፓን በመርከቡ ውስጥ ካሉ መንገደኞች መካከል በቫይረሱ የተያዙ መኖራቸው መረጋገጡን ተከትሎ መርከቧ ተለይታ እንድትቆይና መንገደኞችም እንዳይወርዱ ተደርገዋል። ደቡብ ኮሪያ በበኩሏ ቫይረሱ ይዛመታል በሚል ፍራቻ ማንኛውም መርከብ ሃገሯ እንዳይገባ እግድ መጣሏ ተሰምቷል።

LEAVE A REPLY