የምስጋና መልዕክት || ኤርሚያስ አመልጋ

የምስጋና መልዕክት || ኤርሚያስ አመልጋ

ባልፈጸምኩት ወንጀል ወህኒ ከወረድኩበት ዕለት አንስቶ እየተመላለሳችሁ የጠየቃችሁኝ፣ ለአንድ አመትከሁለት ሳምንታት ያህል ያለመሰልቸት በመገናኛ ብዙሃንና በማህበራዊ ድረገጾች ስለእኔ ድምጻችሁን ከፍ አድርጋችሁ ያሰማችሁ፣ ባገኛችሁት አጋጣሚ ሁሉ ፍትህ እንዳገኝ ስትወተውቱ የነበራችሁ የማውቃችሁም ሆነ የማላውቃችሁ ወዳጆቼ ሆይ፣ እነሆ ከልብ የሆነ ምስጋናዬን ተቀበሉኝ!….

ተፈጥሮዬ ሆኖ በብዙዎች ዘንድ ስሜትን የሚረብሽ፣ ምቾት የሚነሳ ወይም መጥፎ ተደርጎ የሚታይ ነገርሲያጋጥመኝ፣ ነገርዬውን ስለቀጣዩ የተሻለ ለውጥ በጥሞና የማሰቢያና የማብሰልሰያ መልካም አጋጣሚ ለመለወጥ ነው የምተጋው፡፡ በእስር ላይ በቆየሁባቸው 14 ወራት የእስር ቆይታዬ በንዴት እና በቁዘማ አልያም ራሴን ደካማና ተሸናፊ አድርጌ እያየሁ በመብሰልሰል ያሳለፍኩት አንድም ቀን የለም!

በእስር በቆየሁባቸው ጊዚያት ሁሉ፣ ከውስጤ አውጥቼ ዙሪያዬን የምረጨው በጎ ሃይልና ቀና ስሜትን ነበር፤ በዚህም በቂሊንጦ ግቢ ውስጥ ቀና መንፈስና የንቃት ስሜት ከፍ እንዲል ማድረግ ችያለሁ። ከታራሚዎች አንስቶ እስከ ጥበቃ እና የአስተዳደር ሰራተኞች፣ በዙሪያዬ የነበሩት ሁሉ ያለአግባብ እንደታሰርኩ የተረዱ እና የእኔ ቀና አመለካከትና የንቃት ስሜት የተጋባባቸው ነበሩ፡፡

ታላላቅ ስራዎቼን አቋርጬ በአንዲት ጠባብ ክፍል ውስጥ ብታጎርም፣ አእምሮዬ አንድም ቀን ስራ ፈትቶ አያውቅም ነበር፡፡ በእያንዳንዷ ቀን 8 ሰዓታትን ያህል በንባብ ነበር የማሳልፈው፡፡

በእስር ቤት ቆይታዬ በየሳምንቱ የታተሙትን ሁሉንም የ“ዘ ኢኮኖሚስት” መጽሔት ቅጾች እና ያነበብኳቸውን ከ30 በላይ መጽሐፍት ጨምሮ፣ በሳምንት ቢያንስ 200 ገጾች ያህል አነብብ ነበር፡፡ በየዕለቱ ለአንድ ሰዓት ያህል ስፖርት እሰራ ነበር፡፡

የማላውቃቸውን ሰዎች ጨምሮ ሊጠይቁኝ የሚመጡ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ጎብኝዎችን ማስተናገድም ሌላኛው የዕለት ከዕለት ህይወቴ አካል ነበር፤ በየዕለቱ ከ3 ሰዓታት በላይ ከጠያቂዎች ጋር አሳልፍ ነበር፡፡

በተረፈ ግን፣ ለምን ታሰርኩ ብዬ በመብሰልሰል አልያም መቼ ይሆን የምፈታው እያልኩ በመጨነቅ ያጠፋሁት ግዜ አልነበረም፡፡ በመታሰሬ ምክንያት ስለተሰናከሉብኝ ስራዎቼም ሆነ ከንቱ ስለቀሩብኝ ግዙፍ የቢዝነስ ፕሮጀክቶቼ በማሰብና በመጨነቅ ያባከንኩት ግዜ አልነበረም፡፡

እያንዳንዱን ቀን በጸጋ እናበመልካም ስሜት እየተቀበልኩ፣ የራሱን መልካም ነገር እንዲፈጥር በማድረግና በበጎ ተሞክሮነት በመውሰድ ነበር የምሸኘው፡፡ መረጋጋቴን የሚነጥቀኝም ሆነ ፍጹም የሆነ ሰላሜን የሚነሳኝ ምክንያትና ሃይል ስላልነበረ፣ እንቅልፍ ሲወስደኝ እንኳን እንደ ህጻን ልጅ ነበር – ለ8 ወይም 9 ያህል ሰዓታት፡፡

ያለፈውን አመት ዘወር ብዬ ስመለከተው፣ ብዙ ነገር በውስጤ ይመላለሳል፡፡ በመታሰሬ ደስተኛ ነበርኩ
ለማለት ባልደፍርም፣ መጥፎውን አጋጣሚ ወደ መልካም ዕድልነት በመቀየር ለንባብ፣ ለማሰላሰልና ለላቀ እድገት ፈር በመተለም ልጠቀምበት በመቻሌን ደስ ይለኛል፡፡ የእስር ቤት ቆይታዬን ለጥሞናና እና ለማሰላሰል ስለተጠቀምኩበት፣ የህይወት ዓላማና ግቤ ከመቼውም በላይ ከፍ ሊል ችሏል፡፡

ባልታሰር ኖሮ በተለመደው የዕለት ከዕለት የኑሮና የቢዝነስ ግርግር ተጠምጄ አሳልፈው ነበር… በጥልቀት የማሰብና ሁሉንም ነገር በጥሞና አሰላስዬ፣ አዲስ ግንዛቤና የተሻለ አቋም ለመያዝ አልችልም ነበር፡፡

ለተራዘመ ጊዜ በእስር መቆየቴ ሁሉንም ነገር ከጫጫታው ተነጥዬ በጽሞና ለማሰላሰል፣ የበርካታ ኢትዮጵያውያንን አሳዛኝ ዕጣ ፋንታ፣ አገሬ የምትገኝበትን አደገኛ ሁኔታና አስፈሪ አካሄድ በጥልቀት ለመገምገም የምችልበትን መልካም ዕድል ፈጥሮልኛል፡፡

ቂሊንጦ በነበርኩባቸው ጊዚያት ሁሉንም በእርጋታ ካሰላሰልኩ በኋላም፣ እንደ አንድ ዜጋ አገሬን ከገባችበት ችግር ለማውጣት የራሴን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለብኝ ጽኑ እምነት ይዣለሁ፡፡

የአገሪቱ ኢኮኖሚ ተንኮታኩቶ ለመውደቅ በተቃረበበት በዚህ አደገኛ ወቅት ላይ፣ በተለመደው መልኩ መጓዝ አዋጭ እንዳልሆነ ተገልጾልኛል፡፡ ቀጣይ ጉዞዬም ይህን እውነታ ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን እንዳለበት ወስኛለሁ፡፡

በእስር ላይ በነበርኩበት ጊዜ “ኢትዮጵያ በመስቀለኛ መንገድ ላይ” የሚል ርዕስ ያለው እና አገሪቱን ከተጋረጠባት የውድቀት አደጋ በምን መልኩ ማዳን እንደሚቻል ምክረ ሃሳቦችን ያቀረብኩበትን መጽሐፍጽፌ ያጠናቀቅኩ ሲሆን፣ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ታትሞ በገበያ ላይ ይውላል፡፡

በጅምር የቀሩ እና አዳዲስ ፕሮጀክቶቼን ተግባራዊ ከማድረግ ባለፈ፣ በቀጣይ በማህበራዊ ድረገጾች
አማካይነት በተለይ ለወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል እውቀት ለማካፈል፣ ህይወትን ለማሻሻል የሚያስችል አቅጣጫ ለማመላከትና ድጋፍ ለማድረግ አቅጃለሁ፡፡

ብታውቁኝም ባታውቁኝም፣ በችሎት አዳራሽ እየተገኛችሁ አጋርነታችሁን ስታሳዩኝ፣ በማህበራዊ ድረገጾች ስለእኔ ፍትህ ስትጮሁ፣ ስለእኔ በትጋት ስትጽፉና ስትዘግቡ የኖራችሁ እንዲሁም ቂሊንጦ ድረስ እየመጣችሁ ስትጎበኙኝ የማውቃችሁም የማላውቃችሁም በሙሉ…

እነሆ ከ14 ወራት በኋላ በደልና ጥቃት ቅስሙን ሰብሮት ተስፋ የቆረጠ ሳይሆን ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንካራ ልብ፣ ከምን ጊዜውም የተሻለ ጽኑ መንፈስ የተላበሰ ኤርሚያስ ሆኜ መጣሁላችሁ!

ከወራት በፊት “የማይሰበረው” የተሰኘው የህይወት ታሪኬን የያዘ መጽሐፍ በተመረቀበት ዕለት እስር ቤት ሆኜ የላክሁት ደብዳቤ፣ እስር ቤት ያለው ኤርሚያስ በደል እየቆጠረ የማይቆዝም፣ ጥቃትን ፈርቶ የማይረበሽ ልብ የታደለ፤ በተመታ ቁጥር የሚጠነክር፣ በተገፋ ቁጥር የሚጸና፣ በታጠፈ ቁጥር የሚቀና፣ የማይበገር መንፈስ የተሰጠኝ ሰው እንደነበር ይመሰክራል፡፡

አሁንም ከቂሊንጦ ቅጽር ግቢ የበለጠ ጠንክሮ የወጣ፣ ከመቼውም በላቀ ተስሎ አዲስ ታሪክ ለመስራት የሚያኮበኩብ የበለጠ ጠንካራና ደስተኛ ኤርሚያስ ነው ከእስር ተፈትቶ ወደ እናንተ የመጣው!…

ውድ ወዳጆቼ…

በቅርቡ በመገናኛ ብዙሃን በኩል ብቅ ብዬ ስለሁሉም ነገር በስፋት የምለው ይኖረኛል፡፡ እስካሁን ከጎኔ የነበራችሁ ሁሉ፣ አደጋ ላይ በወደቀው ኢኮኖሚ ሳቢያ ፈተና ውስጥ የገቡ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን ህይወት ለማሻሻል በማደርገው ቀጣይ እንቅስቃሴ ውስጥም ከጎኔ
እንደምትቆሙ ተስፋ አለኝ፡፡

በስተመጨረሻም…

በእስር ባሳለፍኩት ጊዜ ሁሉ የተፋጠነ ፍትህ አገኝ ዘንድ ስለእኔ ድምጻችሁን ከፍ አድርጋችሁ ላሰማችሁና አጋርነታችሁን ላሳያችሁኝ በሙሉ፣ በድጋሜ ከልብ የመነጨ ምስጋናዬን ለማቅረብ እወዳለሁ!!!

ኤርሚያስ አመልጋ
መጋቢት 12 ቀን 2012 ዓ.ም.

አዲስ አበባ

LEAVE A REPLY