ኳኳታ የባዶነት መለያ ነው ! || አሥራደው ከፈረንሳይ

ኳኳታ የባዶነት መለያ ነው ! || አሥራደው ከፈረንሳይ

ሽማግሌዎች አባቶቻችንና አሮጊት እናቶቻችንን፤ ኑሮ አጉብጦ የደቆሳቸው፤ ሥርዓቱ ገፍትሮ ከመንገድ ዳር የጣላቸው አልበቃ ብሎ፤ እኛ ልጆቻቸው በዱላ እራስ እርሳቸውን፤ ጀርባቸውን በአለንጋ የምንተለትል ከሆነ፤ በርግጥም ከዜሮ በታች በእጅጉ ዘቅጠናል፤ መዝቀጥ ብቻ ሳይሆን በጥላቻ ባህር ውስጥ ሰምጠናል። 

ሽማግሌ አባቶቻችንና አሮጊት እናቶቻችንን የማክበር ኢትዮጵያዊ ጨዋነታችን ከውስጣችን ተንጠፍጥፎ ያለቀበት ዘመን ላይ በመድረሳችን፤ ሁላችንም ልናዝን፤ ልንሳቀቅና ልንጨነቅ ይገባል።

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምን፤ ካልፈለግን ላለመውደድ መብቱ አለን፤ እሱም በግድ ውደዱኝ የሚል አይመስለኝም።

በሚጽፋቸውና በሚናገራቸው ሃሳቦች፤ ካልተስማማንና፤ አቅሙ ካለን ደግሞ፤ ምክንያታዊና ሚዛኑን ባለቀቀ መልኩ፤ ሃሳቡን በሃሳብ፤ ጽሁፎቹን በጽሁፎቻችን መሞገት እንችላለን።

ከዚያ ባለፈ፤ የዘጠና አመት አዛውንት ላይ፤ ተንጠራርቶ ምራቅ ለመትፋት መጣደፉ ተመልሶ ታፉ ይሆናል።

ሌላው በደምብ መታወቅ ያለብት፤ በምንም መልኩ፤ አንድን ሰው በሃሳቡ ስላልተስማሙ ብቻ፤ መስደብና ሰብዕናውን መዘንጠል በህግ ያስጠይቃል።

ወንድሜ ክርስቲያን ታደለ ጸጋዬ 

በፖለቲካ አሳበህ ወፍራም እንጀራ ለመብላት፤ የቸኮልክ ጎረምሳ ትመስላለህ ። አልገባህም እንጂ ቢገባህ፤ ይህን አጠያፊ ጽሑፍ ከጻፍክበት ቅጽበት አንስቶ የፖለቲካ ሞት ሞተሃል። መሞት ብቻ ሳይሆን ቀባሪም አጥተሃል።

እኛ ኢትዮጵያውያን፤ ከሁሉም በላይ፤ በዕድሜ ለገፉ ወገኖቻችን የምንሰጠው ትልቅ አክብሮት፤ በማንኛውም የፈረንጅ ሳሙና ተፈግፍጎ የሚታጠ አለመሆኑን አልተረዳህም።

የኛ ሰው ነግ በኔን ያውቃል !! ዛሬ ፕሮፌሰር መስፍንን የዘረጠጠ ነገ ለማን ይመለሳል ?!

ወዳጄ ይኸንን በመናገርህ : ጀግና፤ አዋቂ፤ ስልጡን፤ ደፋር፤ የተማረና አዋቂ የሚልህ ካለ፤ በእርግጥም አሱ ካንተ ያልተሻለ፤ ወይም ያንተው ግልባጭ (ፎቶ ኮፒ) ነው::

በዕድሜ የገፉ አዛውንቶችንና አሮጊቶችን፤ አቅፈንና ደግፈን መጦር ቢያቅተን እንኳን፤ ክብርና ፍቅር አንንፈጋቸው !!

ሰው ከሰብዕናው በታች ዝቅ ሲል ፈጣሪውን ያስቆጣል !

ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ይለምልም !

ፈሪሃ እግዚአብሔርን እንላበስ !

4552FC5A-0AE9-4474-BAEB-C21F646F3990

በሽማግሌ አገር || በመንግስቱ ዘገዬ

በሽማግሌ አገር፤
በትልቅ ሰው ግዛት፤
ባልተጠሩት ድግስ፤
ዘው እያሉ ገብተው፤
ዛፍ ያነገሰውን፤
ዛፍ የሞሸረውን፤ የመልከኛን ድንኳን፤ ዳስ እየሰበሩ፤
በክርፋት እጃቸው፤
በወደል አፋቸው፤
ዋርካና ዝግባውን ፤ ወይራና ግራሩን እየተዳፈሩ፥
ዛፍ መሆን አምሯቸው፤
ትልቅ ዛፍ ይቆረጥ፤
በሚል ምሳር ምላስ፤ ሰርክ እያሽቃረሩ፤
ግራዋና እንባጮ፤
ዛፍ መሆን አምሯቸው ቅጠል ሆነው ቀሩ።

|| ጃኖ መንግስቱ ||

LEAVE A REPLY