የዓለም ባንክ የአንበጣ መንጋን ለመከላከል 500 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አፀደቀ

የዓለም ባንክ የአንበጣ መንጋን ለመከላከል 500 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አፀደቀ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ዓለም ባንክ በአፍሪካ እና በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ ሀገራት የአንበጣ መንጋን ለመከላከል ያስችላቸዋል ያለውንየ500 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ ማፅደቁ ተሰማ።

ከባንኩ የተገኘው ገንዘብ በልገሳ እና በአነስተኛ ወለድ የሚሰጥ ብድር እንደሆነ ያመላከተው መረጃ ፤ በአንበጣ መንጋ ክፉኛ የተጠቁት ጅቡቲ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ዩጋንዳ 160 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር በቅርቡ እንደሚሰጣቸው አረጋግጧል።

ሆልገር ክራይ የተሰኙ የዓለም ባንክ ባለሥልጣን ከተጠቀሱት ሀገራት በተጨማሪ የመን፣ ሶማሊያ እና ሌሎች በችግሩ ተጠቂ የሆኑ ሀገራትም እንደየአስፈላጊነቱ ድጋፍ እንደሚሰጣቸው ለሮይተርስ ገልጸዋል።

ምሥራቅ አፍሪካ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ በአንበጣ መንጋ ክፉኛ የተጠቃ ስፍራ መሆኑን እና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ደግሞ ቀውሱን የከፋ ማድረጉንም ጠቁመዋል።

የአንበጣ መንጋው በ23 የምሥራቅ አፍሪካ፣ መካከለኛው ምሥራቅ እና ደቡብ እስያ አገራት በዚህ ወቅት መከሰቱየተጠቆመ ሲሆን፣ ይህም ባለፉት 70 ዓመታት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ መሆኑን  የጠቆመው የዓለም ባንክ፣ የአንበጣ መንጋው በምሥራቅ አፍሪካ ብቻ የ23 ሚሊየን ገደማ ሰዎችን የምግብ ዋስትና አደጋ ላይ ጥሏል ብሏል።

በመሆኑም አስፈላጊው የመከላከል እርምጃ ካልተወሰደበያዝነው ዓመት ውስጥ ብቻ የቀጠናው አገራት ወደ 8 ነጥብ 5 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ሊያወጣ የሚችል ሰብል ውድምት ሊያጋጥማቸው ይችላል ያለው መረጃ፤ እርምጃው ቢተገበርም እንኳን የቀጠናው አገራት 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ኪሳራ እንደሚያጋጥማቸው ገልጿል።

LEAVE A REPLY