ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አሕመድ የህዳሴው ግድብ ውሃ ሙሌትን አስመልክቶ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት...

ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አሕመድ የህዳሴው ግድብ ውሃ ሙሌትን አስመልክቶ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላለፉ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የታላቁ የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌትን በማስመልከት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዕለቱ ሃገራችን በታላቅ ጉጉት ለመስማት የምትጠብቀውን ብስራት የምትሰማበት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በተጨማሪም የኢትዮጵያውያን የዓመታት ልፋት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ የደረሰበትና የህዳሴው ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት የተጠናቀቀበት ታሪካዊ ዕለት እንደሆነም ገልጸዋል።
“በጋራ ጥረት ግድቡን እዚህ ደረጃ ስላደረስነው እንኳን ደስ አለን ፤ በዚህ ዕለት ኢትዮጵያውያን ዳግም ሃገር ተኮር ሥራ ሠርቶ እንዴት ማሳካት እንደሚቻል አውቀናል። የግድቡን ግንባታ ማንም ባላመነብን ወቅት በራሳችን አቅም ላይ እምነት ኖሮን ማሳካት መቻላችንም ይበልጥ አስደሳች ነው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያውያን መልዕክት አስተላልፈዋል።
“አንዳንዶች በህዳሴው ግድብ ላይ ሙጭጭ ማለታችን የታችኛውን የተፋሰሱን ሃገራት ለመጉዳት በማለም የተሠራ ሥራ ይመስላቸዋል።  ግድቡ የዚህ ትውልድ መለያ ማህተም፣ ሠርቶ የማሳካት ትዕምርትና የዘመናት ቁጭታችን መልስ ማግኘቱን የምናበስርበት ፋና ነው” ያሉት ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ “አንገታችንን ሊያስደፉ ሲከጅሉን ለነበሩ ሁሉ የጫኑብን የድህነትና የኋላ ቀርነት ሸክም አሽቀንጥሮ ለመጣል መቁረጣችንን ጮክ ብለን የምንናገርበት ድምጻችን ነው” ብለዋል።
ግድቡ ከእንግዲህ በሁለት እግራችን ለመቆም እንደማይሳነን ወደከፍታው ለማቅናት የመታጠፊያ ነጥባችን መሆኑን ዓለም በትክክል ይረዳል ብለው እንደሚያምኑ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አሁን ላይም ማንንም ሳናስቸግርና ማንንም ሳንጎዳ የመጀመሪያውን ዙር ውሃ መሙላት ችለናል ሲሉ ሴኬቱን ለሀገራቸው ዜጎች አብስረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ለህዳሴው ግድብ ስኬት ከመዋጮ ጀምሮ በሙያቸው፣ በጉልበታቸውና በእውቀታቸው እንዲሁም በዓለም አቀፉ መድረክ በተደረገው ድርድር ለተሳተፉ አካላት እንዲሁም ለቀድሞዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ከፍ ያለ ምስጋናን በመልዕክታቸው ላይ አስተላልፈዋል።

LEAVE A REPLY