ዋ…..! ትልቅ ሕልም ነበረው || አለምሰገድ ገብረኪዳን

ዋ…..! ትልቅ ሕልም ነበረው || አለምሰገድ ገብረኪዳን

ዋ…..!
ትልቅ ሕልም ነበረው፦ የኢትዮጵያን ሕዝብ በኪነጥበብ ሥራዎች የማረስረስ ሕልም።

ባለፈው ዓመት አጋማሽ አንድ ቀን እንዲህ አለኝ፦
“የሚቀጥለው ዓመት የእኛ ነው”
“ማለት?”
“የኢትዮጵያን ሕዝብ ከገመና እና ከመለከት በበለጠ ድራማ እናስደስተዋለን”
አባባሉ አልገረመኝም። ወደ ቤቱ እንደገባ የፃፈውን ተከታታይ ድራማ አቀበለኝ። አነበብኩት። ተየብኩለት። ነፍሴ እንደንተንጠለጠለ ጨረስኩ። ሥራዎቹን የምተይብለት እኔ ነኝ። እየተሟገትን፣ እየተወያየን (እያስተማረኝ ማለት ይቀላል) ነበር ተይቤ የጨረስኩት።
በዚህ ዓመት (2012 ዓም) ያንን ስራውን ያስኮመኩመናል እንጂ ጭራሽ ይለየናል የሚል ግምት አልነበረኝም።

ባለፈው ዓመት ከዕለታት አንድ ቀን ደግሞ እንዲህ አለኝ።
“እኛኮ መስራት ያለብን ሕፃናቶች ላይ ነው፤ ሕፃናቶችን መቅረፅ አለብን ”
ይህንን ብሎ አልቀረም። ራሱ የፃፈውን ግጥም፤ ጊታር እየተጫወተ ዜማ ሰርቶለት አስደመጠኝ። (ጊታር ይጫወታል፤ ስዕል ይስላል፤ ባለብዙ ክሕሎት ነው)
ከወራት በኋላ በስቱዲዮ የተቀናበረ እና የተቀረፀ ከ15 በላይ የሕፃናት መዝሙር አስደመጠኝ። (ጊልዶ መሰለኝ አቀናባሪው፦ እርግጠኛ አይደለሁም)
በዚህ ዓመት እነዚያን የሕፃናት መዝሙሮች ያስደምጠናል የሚል እንጂ በሞት ይለየናል ብዬ አልገመትኩም። ሞቱን ራሱ አምኜ መቀበል አልቻልኩም።

ታላቅ ሰው፣ ታላቅ ወንድም፤ ታላቅ የኪነጥበብ ሰው ነው ያጣነው!
እንዲህ ዓይነቱን ሰው ማጣት በምን ቃል ሊገለፅ ይችላል!?
በምንም!!
ዋ….አዶኒስ 😭

LEAVE A REPLY