2 ሺኅ ኢትዮጵያውያን አይሁዶች ወደሀገሯ እንዲገቡ እስራኤል ፍቃድ ሰጠች

2 ሺኅ ኢትዮጵያውያን አይሁዶች ወደሀገሯ እንዲገቡ እስራኤል ፍቃድ ሰጠች

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || እስራኤል 2 ሺኅ ቤተ እስራኤላውያን ወደ ሀገሯ እንዲገቡ መፍቀዷ ተነገረ። ውሳኔው ከ10 ዓመት በላይ የዘለቀውን የቤተ እስራኤላውያኑን ጥያቄ ምላሽ የሰጠ ነው ተብሎለታል።

ኢትዮጵያውያኑ ወደ እስራኤል ለመጓዝ ለዓመታት ሲጠባበቁ ከነበሩት ወደ 8 ሺኅ የሚጠጉ የአይሁድ እምነት ተከታዮች መካከል መሆናቸው ታውቋል።
ቤተ እስራኤላውያኑ፤ እስራኤል የመኖር መብት ጥያቄያቸው ለዓመታት ሲነሳ ቆይቷል። ለአብዛኞቹ አይሁዳውያን የእስራኤል ዜግነት የማግኘት መብት የሚሰጠው ሂደት ለእነሱ ሳይሠራ መሰንበቱ ይታወሳል።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1980ዎቹ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሚሥጥራዊ ተልዕኮ ወደ እስራኤል ሲወሰዱ፤ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን የአይሁድ እምነት ተከታዮች ያኔ ከሄዱት ቤተ እስራኤላውያን ጋር የደም ትስስር ነበራቸው።
 ከዛ በኋላ ግን ወደ እስራኤል መሄድ የተፈቀደላቸው ጥቂቶቹ ብቻ መሆናቸውን ተከትሎ፣ አሁን ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን አይሁዶች በጎንደር እና አዲስ አበባ በሚገኙ ማቆያዎች ይገኛሉ።
እነዚህ ኢትዮጵያውያን ወደ እስራኤል እንዲሄዱ መፈቀድ አለበት ወይስ የለበትም? የሚለው እስራኤል በሚኖሩ ቤተ እስራኤላውያን ሳይቀር መከፋፈል ፈጥሯል።
አንዳንድ ቤተ እስራኤላውያን፤ ኢትዮጵያውያን የእምነቱ ተከታዮች እስራኤል የመኖር መብት አላቸው ሲሉ፤ ሌሎች ደግሞ አይሁዳዊ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያን ናቸው በማለት ሐሳቡን ውድቅ ማድረጋቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
ከወር በፊት በስደተኞች ጉዳይ ሚንስትርነት የተሾሙት ትውልደ ኢትዮጵያዊት ኒና ታማኖ-ሻታ፤ 2 ሺኅ ቤተ እስራኤላውያን ወደ እስራኤል እንዲገቡ በመፈቀዱ ደስታቸውን ገልጸው በትዊተር ገጻቸው “በጣም ደስ ብሎኛል” ሲሉም አስነብበዋል። እኚህ ሚኒስትር እስከ ቀጣዩ ዓመት ማገባደጃ ድረስ ቤተ እስራኤላውያንን ወደ እስራኤል ለመውሰድ ቃል ገብተው ነበር።

LEAVE A REPLY