የአውሮፓ ሕብረት በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ በእጅጉ አሳስቦኛል አለ

የአውሮፓ ሕብረት በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ በእጅጉ አሳስቦኛል አለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በአሁኑ ሰዐት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ በእጅጉ እንዳሳሰበው የአውሮፓ ሕብረት ባወጣው መግለጫ ላይ ይፋ አደረገ።
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ የጠቆመው  መግለጫው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ፓርቲዎችና ጎረቤት ሀገራት ውጥረት ለመቀነስ መጣር እንዳለባቸውም ምክር ለግሷል።
መግለጫው አክሎ ሁሉም ቡድኖች ግጭት ቀስቃሽ ቃላት መጠቀም ማቆም እንዳለባቸው፣ ከዚህ በተጨማሪም ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን መግታት እንደሚጠበቅባቸው አስታውሶ፤ይህ መሆን ካልቻለ ግን ጉዳቱ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናውም ጭምር እንደሚሆን አሳስቧል።
ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ሀገር ዐቀፍ ውይይቶች እንደሚያስፈልጉ ያመላከተው የሕብረቱ ም/ፕሬዝዳንትና የውጭ ጉዳዮች ከፍተኛ ተወካይ በሆኑት ጆሴፍ ቦሬል አማካይነት የወጣው መግለጫ፤ በዚህ ውይይት ላይ ሁሉም የፖለቲካ ተዋናዮች ተሳታፊ እንዲሆኑ መልእክት አስተላልፏል።
ለኢትዮጵያ ሕዝብ መፃዒ ተስፋና ብልፅግና ብሔራዊ መግባባት እንጂ ግጭት መፍትኄ ሊሆን እንደማይችል ያሳወቀው የአውሮፓ ሕብረት ፤ የኢትዮጵያን ለውጥ ለመደገፍ ቁርጠኛ አቋም እንዳለውም አስታውቋል።
የሰብዓዊ መብትና የሕግ የበላይነት መከበር በተያዘው ዓመት የሚካሄደው ምርጭ ነፃ፣ ተዓማናኒና ፍትሀዊ እንዲሆን ያግዛል ያለው መግለጫ፤ ምንም ኤንኳ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ፓርቲዎችንም ሆነ የጎረቤት ሀገራትን ስም ባይጠቅስም በፌዴራል መንግሥትና በትግራይ ክልል ገዥ ፓርቲ ሕወሓት መካከል ያለው ውጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቷል ብሏል።

LEAVE A REPLY