ቃልኪዳን ነበረን || ወሰንሰገድ ገብረኪዳን

ቃልኪዳን ነበረን || ወሰንሰገድ ገብረኪዳን

ቃልኪዳን ነበረን – በደም የፀደቀ – በግብር የደመቀ፣
እንኳንስ ያገሩን – የአፍሪካን ወንበዴ – በፅናት ያረቀ፣
ቃል-ኪዳን ነበረን – የማይነቃነቅ፣
ዓለምን ያስቀና – እያደር የሚደምቅ!

በሠላሙ ጊዜ – በአንድ ጋቤጣ እየጠጣን “ስዋ”
ቃልኪዳን ነበረን – አብረን ልንሰዋ!
“አደይ ማርያም” ብለን – አብረን ተገባብዘን፣
በአንድ ትሪ በልተን – በአንድ ዋንጫ ጠጥተን፣
በሐቅ ያደመቅነው – ቃልኪዳን ነበረን!

የክፉ ቀን ጓድህ – የክፉ ቀን ጓዴ፣
በእምነት ተቆላልፈው – ክንድህና ክንዴ፣
በፍቅር ተጋምደን – በፅናት የቆምን – አልነበርንም እንዴ!?

ምነው በለሊቱ – በድቅድቅ ጨለማ – በድንገት ከዳኸኝ፣
አንተ አለኸኝ ብዬ -የእግዜር ዕንቅልፍ ወስዶኝ፣
አድብተህ እንደ አውሬ – እንደ እባብ ነደፍከኝ፣
እንዳይሆን አድርገህ ልቤን ሸቀሸቅከኝ!

“አገር አማን ብዬ – ወገን አለኝ ብዬ – ሳሸልብ ጠብቀህ፣
ማተብህን ጥለህ – እምነቴን በጥሰህ፣
ስታዘንብ ጥይት በሰውነቴ ላይ፣
በስተመጨረሻ – ዐይቼህ ነበረ – በቁም ስትሰቃይ፣
ይብላኝ እንጂ ለአንተ – እኔ እንደታመንኩት፣
ነፍሴ ከመውጣቷ – ከማለፌ በፊት፣
እንደተለመደው – ቃል እንደገባሁት፣
“ኢትዮጵያ ወይም ሞት!” – ብዬ ነው የሞትኩት!

ሀገር አልከዳሁም – ወገን አልከዳሁም
ቃል አላፈረስኩም!
ስሄድ እንኳ ከዓለም “ኢትዮጵያ ወይም ሞት” ማለት አልረሳሁም!
“ኢትዮጵያ ወይም ሞት!!

LEAVE A REPLY