የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን

ኅዳር 6 ቀን 2013 ዓ.ም.

ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፡ ፀጥታና ደኅንነትን ለማጠናከር ፈጣንና የተቀናጀ እርምጃ አስፈላጊ ነው

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ኅዳር 5 ቀን 2013 ዓ.ም. ሌሊቱን፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በደባጤ ወረዳ ከወንበራ ወደ ቻግኒ በመጓዝ ላይ በነበረ የሕዝብ ማመላሻ አውቶብስ ላይ በተፈጸመው ዘግናኝ ጥቃት የተሰማውን ኃዘን ይገልጻል። ኢሰመኮ በደረሰው መረጃ መሰረት በተመሳሳይ ወቅት በሌሎች የክልሉ ወረዳዎች (ውብጊሽ፣ያምፕ እና ቂዶህ) ጥቃት መሰንዘሩ እና ለጊዜው ሕይወታቸውን ለማዳን የሸሹ ሰዎች መኖራቸው በመነገሩ፣ በአሁኑ ወቅት የሚገመተው የተጎጂዎች ቁጥር 34 ቢሆንም ሊጨምር እንደሚችል ይጠብቃል። የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “ይህ ጥቃት ሁላችንም በጋራ የተሸከምነውን የሰው ሕይወት ክፍያ ዛሬም በአሳዛኝ ሁኔታ የሚያሻቅብ ነው። የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች በፍጥነት ጥቃቱ የበለጠ እንዳይባባስ እርምጃ መውሰዳቸው አበረታች ነው” ብለዋል።

መስከረም 16 ቀን 2013 ዓ.ም. ኢሰመኮ ያወጣውንና በክልሉ የሚከሰቱ ጥቃቶች ተደጋጋሚነትና አስከፊ ባሕሪይ በተለየ ሁኔታ ያሰመረበትን መግለጫ በማስታወስ፣ ዋና ኮሚሽነሩ የሚከተለውን አክለዋል “በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በሲቪል ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ፋታ የማይሰጥ ሆኖ በመቀጠሉ፤ በፌዴራልና በክልሉ መንግሥታት የፀጥታ ኃይሎች መካከል በፍጥነትና ንቁ ሆኖ መጠበቅ ላይ የተመሰረተ የተሻለ ቅንጅት የሚሻ ነው። የፌዴራልና የክልሉ የፀጥታና የፍትሕ አካላት ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በመሆን እነዚህን ጥቃቶች ሊያስቆም የሚችል አዲስ ክልላዊ የፀጥታ ስትራቴጂ ሊነድፉ ይገባል።”

 

LEAVE A REPLY