አብዬ ሰይፉ – የምናብ ምጥቀት ምሳሌ || በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር)

አብዬ ሰይፉ – የምናብ ምጥቀት ምሳሌ || በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር)

ገጣሚ ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው (እኛ ተማሪዎቻቸው አብዬ ሰይፉ እንላቸዋለን) ካስተማሩኝ መምህራን መካከል በቀጥተኛነታቸውና በምናብ ጥልቀትና ምጥቀታቸው ላለፉት ሰላሳ አመታት በምሳሌነት ስጠቅሳቸው ኖሬያለሁ፤ ወደፊትም፡፡

አንድ ቀን እያስተማሩ ሀይለኛ ዝናብ ዘነበ፡፡ የጣራው ጩኸት አላሰማም አለ፡፡ (ትምህርቱ የመጨረሻው ፎቅ ላይ ነበር)፡፡ ማስተማር አቁመው በመስኮት ፊት ለፊት መመልከት ያዙ፡፡ ተማሪው እርስ በርሱ ጨዋታ ያዘ፡፡ ዝናቡ አባራ፡፡ አብዬ ሰይፉ ዞር አሉና፣
‹‹ልጆች››
ጸጥ አልን፡፡
‹‹ዝናብ አያሳዝናችሁም?››
ዝም፡፡
‹‹እኔ በጣም ያሳዝነኛል፡፡ ከሰማየ ሰማያት ተምዘግዝጎ ሲመጣ ሰው እርጉሙ ድንጋይ አንጥፎ ይጠብቀዋል፡፡ አየወረደ ፍጥፍጥ! እኔ በጣም ያሳዝነኛል፡፡››

አንድ ቀን ደግሞ ወደ ክፍል ገቡ፡፡ ፊታቸው ጠቁሯል፡፡ ደንግጠዋል፡፡

‹‹ልጆች፣ ዛሬ ማስተማር አልችልም፡፡ ተረብሻለሁ፡፡ አንዱ መሀል አስፋልት ላይ አይኔ እያየ ዳጣት፡፡ መሀል አስፋልት ላይ ወድቃ ስመለከት መኪናዬን ዳር አቁሜ ላነሳት ወደ አስፋልቱ መሀል ስገባ አንዱ ጎረምሳ ሲበር መጥቶ ዳጣት!››
ተማሪው አዘነ፡፡ ደነገጠ፡፡
እሳቸው ቀጠሉ፣ ‹‹አስፋልቱን ደም አስመስሎት ነጎደ፡፡ ምንም አልመሰለው፡፡ እንዴት ሰው ጽጌረዳ ይደፈጥጣል፡፡ ምን የመሰለችውን የጽጌረዳ አበባ ዳጣት፡፡ ውበትን አይኔ እያየ ዳጣት፡፡ ይሄ ወጣት በቃ ለምንም አይመለስም፡፡ ይቅርታ አድርጉልኝ ማስተማር አልችልም፡፡›› ብለው ወጡ፡፡ (በአንዱ ግጥም መጽሀፋቸው ውስጥ ለዛች ጽጌረዳ ግጥም ጽፈውላታል)፡፡

የአብዬ ሰይፉ ምናብ፣ የሰውን ልጅ አስፋልት ሲያነጥፍ ዝናብን አለማሰቡ እርጉምነቱን፣ አበባን መዳጡ ጭካኔውን አሳይቷቸዋል፡፡ እኔ ዛሬ ህልፈታቸውን ስሰማ በጣም ያዘንኩት፣ ባለፉት አመታት በሀገራችን የሰው ልጅ በወገኑ ላይ የፈጸመውን የጭካኔ ተግባር ሲመለከቱ በሰው ልጅ እርጉምነት ምን ያህል እንደተሰቃዬ በማሰብ ነው፡፡

አብዬ ሰይፉ ለቋንቋ አጠቃቀም ያላቸው ጥንቃቄ ወደር የለውም፤ የእሳቸው ከዘመነኞቻቸውም ይልቃል፡፡ በአማርኛ መሀል እንግሊዘኛ በፍጹም አይደባልቁም፡፡ ተማሪ ሲደባልቅም አያልፉም፡፡

መጀመሪያ ቀን ክፍል ሲገቡ፣ ‹‹እስቲ ስማችሁን በብጣሽ ወረቀት ጻፉና ስጡኝ›› አሉ፡፡
ሰጠናቸው፡፡ ይዘው ወጡ፡፡
በሚቀጥለው ቀን ክፍል እንደገቡ፣ ‹‹በድሉ ዋቅጅራ ማነው›› አሉ፡፡
‹‹እኔ ነኝ፡፡›› እጄን አወጣሁ፡፡
‹‹ስምህን አማርኛ አልጽፍ ብሎህ ነው በእንግዚዘኛ የጻፍከው?››
ያኔ ነው በእንግሊዘኛ መጻፌ ትዝ ያለኝ፡፡ ዝም አልኩ፡፡
‹‹በል እንካ፣ በአማርኛ ሞክረውና እምቢ ካለህ በእንግዚዘኛ ትጽፈዋለህ፡፡››
ተቀብዬ በአማርኛ ጽፌ ሰጠኋቸው፡፡ እኔም በአማርኛ መሀል እንግሊዘኛ እንደማያልፉ ስላወቅኩና ንግግራቸው ደስ ስለሚለኝ፣ ገብተው ስም ሲጠሩ ሁሉም ተማሪ፣ ‹‹አቤት›› ሲል እኔ ‹‹የስ›› እላቸው ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ስሜን ሲጠሩ ‹‹በድሉ የስ›› እያሉ ነበር፡፡ እኔም ‹‹የስ›› እላቸው ነበር፡፡ ተማሪ ይስቃል፤ እሳቸው ትምህርታቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ቂም የለ፤ በውጤት መጉዳት – ማስፈራራት የለ፡፡ ግሩም መምህር ነበሩ፡፡ ከትምህርታቸው በላይ ከህይወታቸው የተማርኩ ይመስለኛል፡፡
እግዚአብህር ነፍስዎን በአጸደ ገነት ያኑራት፡፡

የተፈጥሮ ባላደራ

ሰሞኑን የተበላውን ይመስል፤
ሙት እህል፤
ጣእሙን ረስታዋለች፤
ድካሙን ብቻ ይዛ የቀረች፤
የተፈጥሮ ባላደራ፤
ህይወትን የማስቀጥል፣ ማስቀጠል ስራ፡፡
————-
(ሰይፉ መታፈሪያ፣ ውስጠት፣ ግጥሙን ካነበብኩት እና በልቤ ከያዝኩት 20 አመት ገደማ ስለሆነው የቃላት ግድፈት ካደረግሁ ይቅርታ)

LEAVE A REPLY