ዘማች || በእውቀቱ ስዩም

ዘማች || በእውቀቱ ስዩም

በቀደም እኔና አዩ እራት ለመብላት አበሻ ምግብ ቤት ቁጭ ብለናል፤ አዩ ባልንጀራየ ናት ፤ ለስድስት ወራት ያክል ብንተዋወቅም ሙሉ ስሟን አልነገረችኝም፤ ሙሉ ስሟ “ አያልነሸ” ወይም “ አያንቱ” ሊሆን ይችላል ::

ቅርብ ማዶ ካለው ጠረጴዛ ፊተለፊት ሁለት ፍቅረኛሞች ተቀምጠዋል፤ ሴቲቱ በሰውየው ትከሻ ላይ ዘንበል ብላ ታለቅሳለች ፤ ሰውየው በፈርጣማ ክንዱ አቅፎ እያባበላት ነው፤
“ልጂቱዋ ምን ሆና ነው እምትነፋረቀው?’ አልኳት አስናጋጂቱን::

“ እጮኛዋ ነገ ወደ ኢትዮጵያ ሊሄድ ነው፤ ዘመቻ” አለች አስተናጋጄ ጠረጴዛውን እያስተካከለችኝልኝ ::

“ ይገርማል! ሸገር ፤ መሀል ቦሌ ላይ የሚኖሩ ቤተሰቦችን ማየት የሚፈራ መአት ዲያስፖራ ባለበት አገር እንዲህ አይነት ቆራጥ ማየት ልብ ያሞቃል “ አለች አዩ: :

“ የጠረጴዛው ልብስ በጣም ነው የሚያምረው “ አልኩ ጨዋታ ለማስቀየስ ::

“ አንተ መች ነው እምትዘምተው?”

<ምነው፥ የእዝን ቆሎየን ለመብላት ቸኮልሽ> ልላት ፈልጌ ተውኩት ::

“ እኔኮ ባገሬ ድርሻየን ዘምቻለሁ”

“ መቸ?” ፥ አፋጠጠችኝ

“ትንሽ ቆየት አለ”

“ ባድሜ?”

“አይ! የመሰረተ ትምህርት ዘመቻ”

“ የመሰረተ ትምህርት ዘመቻ ላይ ደርሰህበታል ?’ አለች አይኖቿን በግርምት አፍጥጣ ::

“ ሰባተኛው ዙር ደርሶብኛል ”

“በሕይወትህ ተደባድበህ ታውቃለህ?”

“ተደብድቤ አውቃለሁ፤ አጻፋውን ለመመለስ ግን ጊዜና አጋጣሚው አልፈቀደልኝም ”
“ unbelievable !”

“ ቤተሰቦቼ ባንድ ወገን ደብተራ ባንድ በኩል ቃልቻ ናቸው፤ ለማውጋት እንጂ ለመዋጋት የሚሆን ጂን ያልወረስኩት ለዚያ ይሆናል! ተረጂኝ”

ዝም አለች፤ በፊቷ ሞገስ ለማግኘት አንድ ነገር ለማድረግ ወሰንኩ፤ አስተናጋጂቱን ጠርቼ “ ዘማቹ ሰውየና ሚስቱ ያዘዙት ሂሳብ በኔ ነው “አልኩዋት፤

“ አንድ ጎድን ጥብስ፤ አንድ ክትፎ፤ እና አንድ ሩዝ ባትክልት”

ሰውየው ከራቱ ጋር ደርቦ ስንቁን እንዳዘዘ ገባኝ::

ትንሽ ቆይቶ ፤ ወደ ተቀመጥንበት መጥቶ አመሰገነኝ ፥

“ አንተ መሰዋእት እየከፈልህል እኛ ራት መከፈል አይበዛብንም” አልኩት፤ በውነት ግን ለራት የከፈልኩት ወደ ኢትዮጵያ ቢመነዘር ቆንጆ ቅጥቅጥ ባጃጅ ያስገዛል፤

“ አየ! በእንባ ብዛት ሀሳቤን አስቀየረችኝ እኔማ ልዘምት ወስኘ ነበር” ሲለኝ ምን ልበል፤

በንባ ብዛት ማስቀየር የማልችለውን የጋብዝኩበትን ደረሰኝ እያየሁ ተከዝኩ፤

LEAVE A REPLY