የአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ተማሪ የነበረችውን ወጣት የገደላት ግለሰብ ፍርድ ቤት ቀረበ

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ተማሪ የነበረችውን ወጣት የገደላት ግለሰብ ፍርድ ቤት ቀረበ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ የሆቴልና ቱሪዝም ማኔጅመንት 2ኛ ዓመት ተማሪ የነበረችው ፅጌረዳ ግርማይን በስለት ወግቶ የገደላት ግለሰብ ፍርድ ቤት መቅረቡን የከተማዋ ፓሊስና ዩኒቨርስቲው አስታወቁ።

በዩኒቨርስቲው ተማሪ የሆነው ተጠርጣሪና ሁለት ሌሎች ተማሪዎች ከፅጌረዳ ግድያ ጋር በተያያዘ ማክሰኞ ዕለት በአርባ ምንጭ ፍርድ ቤት ቀርበው የነበረ ሲሆን የ15 ቀናት ቀጠሮ ተሰጥቷቸው በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ መደረጋቸውን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር በድሩ ኢሪጎ ገልጸዋል።

ፅጌረዳ ግርማይ በስለት በተፈጸመባት ጥቃት የተገደለችው ሰኞ ጥር 23/2014 ምሽት በግቢው ቤተ መጻሕፍት አካባቢ መሆኑን በጋሞ ዞን የአርባ ምንጭ ከተማ ፖሊስ ኃላፊ ኮማንደር አዳነ ኦኬ አስረድተዋል።
ግድያው የተፈጸመው ጥር 23/2014 ምሽት አምስት ሰዓት ገደማ ሲሆን፣ ተጠርጣሪው በዩኒቨርስቲው የሆቴልና ቱሪዝም ማኔጅመንት 2ኛ ዓመት ተማሪና ከፅጌረዳም ጋር በአንድ ዲፓርትመንት የሚማሩ እንደነበሩና፣ የነበራቸውን ግንኙነት በተመለከተ የተለያዩ መረጃዎች እየተሰሙ እንደሆነም በድሩ ተናግረዋል።

ፅጌረዳ ከዚህ ቀደም ከተጠርጣሪው ጋር ግንኙነት እንደነበራትና ይህንንም ግንኙነት በማቋረጧ የተነሳ ነው የሚሉ፣ እንዲሁም ተጠርጣሪው ፅጌረዳን ለፍቅር ግንኙነት ፈልጓት ፈቃደኛ ባለመሆኗና ይህንንም እምቢታዋን በበጎ መልክ ባለመውሰድ በስለት ወግቷታል የሚል መረጃን ሰብስብዋል።
የዶርም የምትኖር ጓደኛዋንም ዋቢ አድርገው በድሩ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ተጠርጣሪው ለፍቅር ግንኙነት እንደሚፈልጋት እና ፅጌረዳም እምቢተኝነቷን እንደገለጸች፣ ከዚያ በኋላም ምንም አይነት ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልነበረችም ብለዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ከአካባቢው ፖሊስ የተገኘው መረጃ የጥቃቱ ሰለባና ተጠርጣሪው የፍቅር ግንኙነት እንደነበራቸው ያመለክታል።

ይህንንም ተከትሎ ተጠርጣሪው እና ስልክ ደውለዋል የተባሉት ሁለት ተማሪዎች በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ በድሩ አስረድተዋል።

በወቅቱም ፅጌረዳ ወደ አርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል በአስቸኳይ እንድትደርስ ቢደረግም ህክምና እየተደረገላት ህይወቷ አልፏል። በነገታው ጥር 24/2014 ዓ.ም አስከሬኗ ወደ ትውልድ ቦታዋ ወልቃይት አዲ ረመፅ ተሸኝቷል።

የፅጌረዳ ግድያ ከብሔሯ/ከማንነቷ ጋር የተያያዘ እንደሆነ በተለያዩ ማኅበራዊ የትስስር ገጾች ላይ መነሳቱን ጠቅሶ ቢቢሲ ለዳይሬክተሩ ጥያቄ አቅርቦ የነበረ ሲሆን፤ ጉዳዩ የፖለቲካ ባይሆንም እንኳን ፖለቲካዊ ትርጉም እንዲሰጠው የሚሞክሩ ይኖራሉ ለዚህ ትርጓሜ መስረት የለውም ሲሉ በድሩ አስረድተዋል።

LEAVE A REPLY