ኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት አያያዝ ቀውስ ውስጥ መሆኗ ተነገረ

ኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት አያያዝ ቀውስ ውስጥ መሆኗ ተነገረ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በ2014 በጀት ዓመትም የዜጎች በሕይወት የመኖር መብት በከፍተኛ አደጋ ውስጥ ወድቋል ብሏል ኮሚሽኑ፤ በዓመቱ ውስጥ የከወናቸውን ስራዎች በተመለከተ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ፡፡

በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት በሁሉም ወገኖች በኩል የጦርነት ህግን ተከትሎ ባለመንቀሳቀስ በተለይ በአማራና በአፋር ክልሎች 403 ንጹሃን ዜጎች ተገድለዋል ብለዋል ዋና ኮሚሽነሩ ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፡፡
በተለይ በትግራይ ታጣቂዎች ሆን ተብሎ በተወሰደ እርምጃ ደግሞ ህፃናት ሴቶች፣ አረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማንን ጨምሮ 346 ንጹሃን ከፍርድ ውጭ መገደላቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በወለጋ ዞኖች ሸኔ የብሔር ማንነትን መሰረት አድርጎ በሚፈፅመው ጥቃትም በተለያየ ጊዜ በ100ዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን እንደተገደሉ የጠቀሱት ኮሚሽነሩ የተጠቃለለ ቁጥር ግን አልገለፁም፡፡

በተለይ በቅርቡ በምዕራብ ወለጋ ዞን በቶሌ ቀበሌና በቄለም ወለጋ የተፈፀመውን ጭፍጨፋ በተመለከተ ኮሚሽኑ ገና በቦታው ተገኝቶ መረጃዎችን ስላላጣራ በጥቃቱ ምክንያት የተገደሉትን ቁጥር ትክክለኛውን አላረጋገጥኩም ብሏል፡፡

በተያያዘ በክልሎች ከሰላምና ፀጥታ ጋር በተያያዘ ሰላም ለማስከበር በሚል ምክንያት በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በጅምላ መታሰራቸውንም ዶ/ር ዳንኤል ተናግረዋል፡፡

በአማራ ክልል ብቻ ከ10,000 በላይ ሰዎች በተለይ የኢ-መደበኛ ታጣቂ ኃይሎች አባል ናቸው የተባሉ እና በክልሉ የሚገኙ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ በምጅላ ታስረዋል ተብሏል፡፡
ኮሚሽነሩ የተጠቀሱትን ጨምሮ ሌሎችም የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዲስተካከሉ ምክረ ሀሳብ እየሰጠን ነው ብለዋል።

LEAVE A REPLY