የጨዋታ ፍቅር (ዳዊት ከበደ ወየሳ) ||ከማለፉ ሁለት ቀን በፊት||

የጨዋታ ፍቅር (ዳዊት ከበደ ወየሳ) ||ከማለፉ ሁለት ቀን በፊት||

ጋዜጠኛ ደዊት ከበደ ወየሳ በኢትዮጰያ የፕሬስ 
ነፃነት ትግል ከፍተኛ አሰተዋፆ ያበረከተ ከመሆኑም 
በላይ በፐሬስ ክስ በእስር የሚሰቃዬና 
ቤተሰቦቻቸውን በትነው በስደት  ለሚንከራተቱ 
ጋዜጠኞች ድጋፍ እንዲያገኙ በብቱ ከሚለፉ 
ወገኖች ግንባር ቀደም ነበር። ዳዊት ከሚኖርበት 
አትላንታ ግዛት ወደ አዲስ አበባ በገባ በጥቂት 
ቀናት ወስጥ ህይወቱ አልፏል። ይህ በፌስቡክ ገጹ 
ከማለፉ ሁለት ቀናት በፊት ያጋራው ጸሀፍ ነው። 
ነፍስህ ትረፍ ወዳጅዓለም

አዲሳባ ከገባሁ 2ኛ ቀኔ ተቆጥሯል። ባለኝ አጭር ጊዜ ማድረግ የሚገባኝን አደርግና ያልተስተካከለውን እንቅልፍ በማታ እሸኘዋለሁ። እናም ዛሬ በ’እለተ መድሃኔአለም ስለሆነ ነው መሰለኝ፤ የቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ከርቀት እየሰማሁ፤ ሰመመናዊ እንቅልፍ እንደገና ወሰደኝ።

ከዚያ ደግሞ… የውሾች ድምጽ፣ የልጆች ጫጫታ፣ የመኪና ጥሩንባ ከሰመመን ቀሰቀሰኝ። ጊዜያዊ ግርግር መስሎኝ ተመልሼ ልተኛ ስል እንቅልፍ እምቢ አለኝ። የማያቋርጥ የወንድ ልጆች ጫጫታ፤ “ያዘው፣ ስጠው… አቀብለው” የሚሉ ድምጾች ሳያቋርጡ ይሰማሉ። እየተጨናበስኩ አይኔን ከፈትኩ። ጨለማው ገና አልገፈፈም፤ ብርሃኑም አልፈነጠቀ… ጎህ በመቅደድ ላይ ነው።

ካለሁበት 3ኛ ፎቅ ላይ ሆኜ ወደ ውጭ ስመለከት፤ መንገዱ ተወሯል። መጀመሪያ ግራ ተጋባሁ፤ መንገዱ ላይ ልጆች ይሯሯጣሉ። ኳስ ጨዋታ ላይ ናቸው። ስልኬን አነሳሁና መቅረጽ ጀመርኩ። በወጣቶቹ ሁኔታ ተገርሜ፤ በመንገድ ላይ ጨዋታው ደግሞ አዝኜ… እንደገና ወደመኝታዬ ተመለስኩ።

(ንጋት ላይ ኳስ ሲጫወቱ ያነሳሁትን ቪዲዮ ማያያዝ ስላስቸገረኝ ለጊዜው ትቼዋለሁ።)

+++++++++++++++++++++

ቀደም ሲል ያስነበብኩትን ወግ ለናንተ ካጋራኋቹህ በኋላ፤ “ፊጋ የት ነው?” ያላችሁኝ ሰዎች አላቹህ። ‘እኔም እንደናንተ አላውቀውም ነበር። አሁን እንደተረዳሁት ከሆነ ግን ከድሮው ጉርድ ሾላ ገባ ብሎ የነበረው ሰፈር ነው። አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ከፍየል ቤት ወረድ ብሎ… ይሉታል’ ብለውኛል ሰዎች። ይሄ ሰፈር የድሮ ስሙ ምን እንደነበር እኔም አላውቀውም። አንድ የማውቀው ነገር ቢኖር ፊጋ የሚባለው ሰፈር በትላልቅ ህንጻዎች የተሞላ፤ ሰፊ መንገድ ያለው፤ ትልቅ የአዲስ አበባ ውስጥ ከተማ ነው… በሚል ልለፈው።
የፊጋ መንገድ

(ዳዊት ከበደ ወየሳ)

አገር ቤት እንደገባቹህ ድካም እና እንቅልፍ ቢፈራረቅባቹህ አይገርምም። እናም በፊጋ መንገድ ላይ የነበረው ኳስ ጨዋታ እና ስፖርት እንደቀጠለ ነው። ይህ የብዙሃን ስፖርት ውሎ፤ ከአንዳንድ ጓደኞቼ ጋር የነበረኝ ቀጠሮ አራዘመው። ምክንያቱም የፊጋ መንገድ ከላይ እና ከታች ካሉት መብራቶች ጀምሮ ዝግ ነው። ከቤቱ ወጥቶ ወደላይም ሆነ ወደ ታች የሚሄድ ሰው ያለው የመጀመሪያ አማራጭ በ’እግሩ መኳተን ይሆናል። ይህ ደግሞ ለጊዜው ተመራጭ ባለመሆኑ ሳልወድ ከቤት ቆየሁ።

እየቆየሁ ስመጣ… የመንገዱ ላይ ጨዋታ እየደራ መጣ። በነገርዎ ላይ… ይህ የፊጋ መንገድ በግራ እና በቀኝ በያንዳንዱ ረድፍ አራት አራት መኪና በመደዳ የሚያሳልፍ ነው። በመንገዱ ላይ ድንጋይ እንደ ጎል ተቀምጦ ጨዋታው ደራ። እግር ኳስ ብቻ ሳይሆኑ ቮሊቦል የሚጫወቱ፤ ገመድ የሚዘሉ፤ ባይስክል የሚጋልቡ፤ ወዲያ እና ወዲህ የሚሯሯጡ ወጣት ስፖርተኞችን ከላይ ወደታች እያየሁ፤ በስልክ ደግሞ ከጓደኞቼ ጋር ማውራት ቀጠልኩ።

“አታውቅም እንዴ?”
“ምኑን?” ጥያቄውን በጥያቄ መለስኩለት።
“እሁድ እሁድ እኮ የፊጋ መንገድ ይዘጋል።”
“ህጋዊ ነው እንዴ?”
“አዎ እስከ 6 ሰአት ወይም እስከ እኩለ-ቀን ድረስ ይኸው ሁኔታ ይቀጥላል።”
“እንደዛ ነው እንዴ?” ጥያቄ አበዛሁበት።

እናም ትንሽ እንደቆየሁ የተባለው ነገር ሆነ። ቀትር 6፡00 ሰአት ላይ… ፖሊስ የሞተረኛ ጥሩንባ እየነፋ መጣ። የጥሩንባውን ድምጽ የሰሙ ወጣቶች ገለል ገለል ማለት ጀመሩ። መንገድ መሃል ያስቀመጡትን ድንጋይ እያነሱ፤ ኳሳቸውን እያነጠሩ አካባቢውን ያጠሩት ጀመር። የፖሊሱ ዶቅዶቄ ወደላይ መጥቶ ወደ ታች ሲመለስ በተመሳሳይ መልኩ ጥሩንባውን እያንባረቀባቸው ነበር። በሁለተኛው የሞተረኛ ጉዞ መገዱ ከመንገድ ላይ ስፖርተኞች እየጠራ እየጠራ መጣ። ቀስ በቀስ መንገዱ ከስፖርተኞች ነጻ ሆነና፤ ከላይም ከታችንም ያሉት የመንገድ መብራቶች አረንጓዴ አበሩ።

(በነገርዎ ላይ በሁለቱ መብራቶች መካከል ያለው፤ ወይም እሁድ ጠዋት የሚዘጋው መንገድ 2.5 ኪሎ ሜትር ወይም ከአንድ ማይል በላይ ርዝመት አለው)

ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ መንገዱ እንደወትሮው በመኪና ተሞላ። ጓደኞቼም ነጻ ሆነው መኪና እየነዱ ወጣሁ። እኔም ፊጋን ለቅቄ ወጣሁ። እስከማታ ድረስ አልመለስም። መልካም ሰንበት።

LEAVE A REPLY