ሃይማኖቱን እንኳ ተዉለት! || ዮናስ ዘውዴ ከበደ

ሃይማኖቱን እንኳ ተዉለት! || ዮናስ ዘውዴ ከበደ

በዓለም ከድካም በቀር ምንም ላልተረፈው፤ የዕለት ተዕለት ሕይወቱን ለማሸነፍ ብርቱ ትግል ለሚያደርገው፤ መሠረታዊ የሚባሉ ነገሮችን ለሟሟላት ብቻ ሲለፋ ዘመኑን ለሚፈጀው፤ ቢከፋው፣ ቢያዝን፣ ቢመረው በምድር ምንም መጽናኛ ለሌለው፣ ለዚህ ምስኪን ሕዝብ… ልቡ ሲበርደው፤ አንጀቱ አልችል ሲለው የሚጽናናበትን ሃይማኖት እንኳ ተዉለት እንጂ።

በብዙ መከራ ውስጥ ለሚያልፍ፤ ከፀሐይ በታች ሁሉም ዓይነት የመከራ ዶፍ ለዘነበበት፤ አለኝ ብሎ የሚማጸንበትን፣ ይኽን ዓለም የሚንቅበትን፤ የተጓደለበትን ምድራዊ ፍትሕ በትዕግሥት እንዲያሳልፍ ምክንያት የሆነውን እምነቱን እንዴት አይተዉለትም?

እንደ ሕዝብ ከቀዬው ተፈናቅሏል፣ በቋንቋው ተሰዷል፣ በሰውነቱ ተጎሳቁሏል፣ በቅድመ አያቶቹ ታሪክ ምንም የማያውቀው ሰው፤ ላልነበረበት ጊዜ በመካካሻነት በጠላትነት እየተፈራረጀ እንዲኖር ተፈርዶበታል። ይኽ በሕዝቦች መካከል የተዘራ እንክርዳድ ነው። በፓለቲካው ዓለም በጸብ ለሚነግዱ አካላት ይኽ እንክርዳድ እንደ ትልቅ የኃይል መሣርያ በማገልገል ዘልቋል።

ሃይማኖት ግን መነካት የሌለበት እሳት ነው። ሃይማኖት የምትጫወትበት ምድራዊ እሳት አይደለም። ለሚያምኑት የመለኮት እሳት ነው። ከቅጽሩ ወዳልተቀደሰ የፖለቲካ ሜዳ ልታወጣው ብትሞክር ቅድሚያ የሚፈጅህ አንተኑ ነው። ሃይማኖት ሀገር እንደ ሀገር እንድትቀጥል ሕዝብን ከሕዝብ አንድ አድርጎ አያይዞ በኅብረት አቆይቷል።

ፈርሀ እግዜርም ከትውልዱ ላይ እንዳይጠፋ ግብረገብን በማሥረጽ “moral compass” ሆኖ ያገለገለውም ሃይማኖት ነው። ኅሊናውን በጥላቻ የታወረ ሰው ሊገድልህ ቢመጣ ቢያንስ “በእግዜር፥ በጌታ፣ በማርያም፥ በአሏህ፥ በዋቃ… ብቻ በፈጠረህ!” ትለዋለህ። እንደ ሕዝብ ተከባብረን የኖርነው የሠለጠነ ሕግና ሥርዓት ስላለን አልነበረም። ይልቁንም በፈጠረን አምላክ በኩል አንድ እንደሆንን ስለሚሰማን ነበር። እንደ ሕዝብ የሥልጣኔ ታሪክ ቢኖረንም ቅርብ ጊዜ ያስተናገድናቸው ቀውሶችና የሰማናቸው ዜናዎች ባለአእምሮዎች ለመሆን ብዙ እንደሚቀረን፤ ሥልጡን ነን ብለን የምንመጻደቀውን ያህል ሥልጡን እንዳልሆንን ይናገራሉ። የትምህርት፣ የጤና፣ የፍትሕ… ሥርዓቶቻችን በስብራት የተሞሉ ናቸው። ምንን ተማምነን ምንን እንደምናፈርስ አናውቅም።

በርሀብ ብዛት ከአንጀቱ የተጣበቀ ሆዱ እስኪቀደድ ድረስ እያከከ የፒያሳን ወርቅ ቤቶች ያለስርቆት ውልብታ ደክሞት የሚደገፍ የ’ኔ ቢጤና ምንዱባን ያላጣነው በእንተ ስማ ለማርያም ብሎ የሚላስ የሚቀመስ በማምሻ እንደማያጣ ተስፋ ስለሚያደርግ ነው። እንጂማ የሚበላው ያጣ ሕዝብ መሪውንም እስከ መብላት ይደርሳል።

የሃይማኖትን አንድነትን የነጠቅከውን ሕዝብ በምን አንድ ታደርገዋለህ? ነገ ከነገ ወዲያ የእንትን ክልል እግዜር ከእንትን ክልል እግዜር ጋር ኅብረት እንደሌለው በግልጽ የሚሰበክበት ጊዜ ይመጣል። የሃይማኖት አንድነትን ማዳከም (ሲዳከምም በዝምታ ማየት) እያደር ቅጥ ላጣ ዓለማዊነት፣ ግብረሰዶማዊነት… አውሮፓ እየተሰቃየ ላለበት የስመ ሥልጣኔ በሽታና ውጥንቅጥ ሁሉ በር እንደመክፈት ነው። በቀሪው ዓለም ሲቀደስባቸው የነበሩ ትላልቅ ካቴድራሎች መጠጥ ቤትና የምሽት ጭፈራ ቤቶች ሆነዋል።

በክርስትና ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና።
አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችንም በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ነን። (ገላ. 3፥27-28) ክርስቶስ በሞቱ ያላስታረቀው የለም። አንድ በየቀኑ በአባታችን ሆይ ጸሎቱ “ይቅር በለን… እኛም የበደሉንን ይቅር እንደምንል” እያለ የሚጸልይ ሰው እንዴት እና ከመቼው ? የሀጢአት ማወራረድ ውስጥ ይገባል?

በክርስቶስ ስም የተመሠረተች ቤተ ክርስቲያንን ለመከራ አዲስ አይደለችም። የመከራ ዘመናቶች አሏት። ነገር ግን ክርስትና ሥር የሚሰደው ደግሞ በመከራ ውስጥ ነው። ሊቁ ጠርጡለስ “The blood of the Martyrs is the seed of the church” ይላል። ሰማዕታት የቤተ ክርስቲያን ምርጥ ዘር ናቸው። በዚህ ሁሉ መሃል ግን ቤተ ክርስቲያንን የነኳት ኔሮን እና ማርከስ ኦሬሊየስ የት ናቸው?

ቤተ ክርስቲያን ግን ይኸው አለች። ትኖራለችም። ይኽች ቤተ ክርስቲያን በየሆስፒታሉ ለወደቁ ሕሙማን፣ በየወኅኒው ለታሰሩ፣ አርሰው ዝናምን ለሚጠብቁ፣ በስደት በሰው ሀገር ላሉ፣ ለአእዋፋትና ለአራዊት፣ ይልቁንም ደግሞ ስለአገር ሰላም ሌሊት ተቀን የምትጸልይና የምትማልድ እመቤት ናት። በደመራ ዕለት እኔ በጥምቀት ዕለት ብቻ ሳይሆን በመከራዋ ቀን የሚመጡላት እልፍ ልጆች አሏት። ኖረው ብቻ ሳይሆን ሞተው የሚያከብሯት አዕላፍ ልጆች አሏት። የድረሱልኝ ጥሪዋን ሰምተው ልጅ የእናቱን ድምፅ ሰምቶ እንደሚገሰግስ በጓቿ ድምፃን ሰምተው በቅጥር ግቢዋ ይሰበሰባሉ። በክንፎቿ ይጋረዳሉ ይጋርዱማል።

ቤተ ክርስቲያን ሆይ እንደ አንድ ዜጋ በአንቺ ወቅታዊ ጉዳይ ከመጨነቅ የሚይዘኝ ነገር የለም። እናም ስለሰላምሽ እጸልያለሁ!

አገሬ ሆይ እንደ አንድ ከምድርሽ እንደ በቀለ ዜጋ በአንቺ ወቅታዊ ጉዳይ ከመተከዝ የሚይዘኝ ነገር የለም። እናም ስለሰላምሽ አጥብቄ አነባለሁ !

LEAVE A REPLY